የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) የፖለቲካ ኦፊሰር አቶ በቴ ኡርጌሳ በትውልድ ከተማቸው መቂ ውስጥ ተገድለው አስክሬናቸው ተገኘ።

ለደኅንነታቸው ሲባል ስማቸው እንዲገለጽ ያልፈቀዱ የአቶ በቴ ኡርጌሳ የቅርብ ጓደኛ ለቢቢሲ እንደተናገሩት አቶ በቴ በኦሮሚያ ክልል ምሥራቅ ሸዋ ዞን በምትገኘው መቂ ከተማ የተገደሉት ትናንት ማክሰኞ ሚያዚያ 1/2016 ዓ.ም. እኩለ ሌሊት ላይ ነው።

ፓርቲያቸው የኦሮሞ ነጻነት ግንባር የፖለቲካ ኦፊሰሩን ግድያን አረጋግጦ ምርመራ እንዲደረግ ጠይቋል። የፓርቲው የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ለሚ ገመቹ በፌስቡክ ገጻቸው ላይ “በቴ የሆነውን ማመን አቅቶኛል” ሲሉ ጽፈዋል።

አቶ በቴ የካቲት አጋማሽ ላይ በቁጥጥር ስር ውለው ለሁለት ሳምንታት ያህል በእስር ከቆዩ በኋላ በ100 ሺህ ብር የገንዘብ ዋስትና የተለቀቁት ከአንድ ወር ገደማ በፊት የካቲት 30/2016 ዓ.ም. ነበር።

ቢቢሲ ያነጋገራቸው የፖለቲከኛው የቅርብ ጓደኛ እንደሚሉት፤ አቶ በቴ በመቂ ከተማ አርፈው ከነበረበት የሆቴል ክፍል ውስጥ እንዲወጡ ከተደረጉ በኋላ ተገድለው አስክሬናቸው መንገድ ላይ ተጥሎ ተገኝቷል።

የአቶ በቴ ኡርጌሳ ላይ ግድያውን ማን እንደፈጸመው እንደማያውቁ የገለጹት እኚህ ግለሰብ፤ በአሁኑ ወቅት በመቂ ከተማ የቴሌኮም አገልግሎት በመቋረጡ ተጨማሪ መረጃ ማግኘት አዳጋች እንደሆነባቸው ጨምረው ተናግረዋል።

አቶ በቴ አመራር የሆኑበት የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) ዛሬ [ሐሙስ] ከዕኩለ ቀን በኋላ ግድያውን በተመለከተ ባወጣው መግለጫ፣ አቶ በቴ በትውልድ ስፍራቸው መቂ ውስጥ መገደላቸውን አረጋግጧል።

ጨምሮም ፓርቲው የአቶ በቴ ኡርጌሳን ግድያ ዙሪያ ያለውን ሁኔታ በራሱ ማጣራት እንደሚያደርግ አመልክቶ፤ የሰብአዊ መብት ድርጅቶች ገለልተኛ እና ሚዛናዊ ምርመራ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርቧል።

የአቶ በቴን ግድያ በተመለከተ የኦሮሚያ ክልል መንግሥት ረቡዕ ምሽት ላይ ባወጣው መግለጫ፣ ምንም እንኳን መንግሥት ከአቶ በቴ ኡርጌሳ ጋር የፖለቲካ ልዩነት ቢኖረውም ከግድያ ጋር የሚያያይዘው ነገር እንደሌለ ገልጿል።

መግለጫው በፖለቲከኛው ላይ የተፈጸመውን ግድያ አውግዞ፣ በወንጀሉ ዙሪያ አስፈላጊው ምርመራ ከተደረገ በኋላ ውጤቱ ለሕዝብ እንደሚገለጽም አስታውቋል።

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ዋና ኮሚሽነር ዳንኤል በቀለ (ዶ/ር) በአቶ በቴ ግድያ ዙሪያ ገለልተኛ ምርመራ እንዲደረግ ጥሪ አቅርበዋል።

ዋና ኮሚሽነሩ በኤክስ ገጻቸው የፖለቲከኛውን ገዳዮች ለፍርድ ለማቅረብ የፌደራለ እና የኦሮሚያ ክልል ባለሥልጣናት ፈጣን፣ ገለልተኛ እና ሙሉ ምርመራ እንዲያደርጉ ኢሰመኮ ይጠይቃል ብለዋል።

ለአቶ በቴ ቅርበት ያላቸው ሌላ ጓደኛ ለቢቢሲ እንደተናገሩት ፖለቲካኛው ወደ መቂ የተጓዙት ከከተማዋ አቅራቢያ ያላቸው የፓፓያ እርሻ ለመመልከት ነበር።

አክለውም የአራት ልጆች አባት የሆኑት የአቶ በቴ መገደል ለቤተሰባቸው ከተነገረ በኋላ የቤተሰብ አባላት ግድያው ወደተፈጸመባት መቂ ከተማ ዛሬ ጠዋት አቅንተዋል ብለዋል።

አቶ በቴ በፖለቲካ ተሳትፏቸው ምክንያት በተደጋጋሚ ለእስር ሲዳረጉ የቆዩ ፖለቲከኛ ሲሆኑ: ከጥቂት ሳምንታት በፊትም ከአንድ ፈረንሳይዊ ጋዜጠኛ ጋር በአዲስ አበባ በቁጥጥር ስር ውለው ነበር።

አቶ በቴ ኡርጌሳ ሐሙስ የካቲት 14/2016 ዓ.ም. ከፈረንሳዊው ጋዜጠኛ አንቷን ጋሊንዶ ጋር በአዲስ አበባ ስካይ ላይት ሆቴል እየተነጋገሩ ሳለ በቁጥጥር ስር ውለው ከሁለት ሳምንታት እስር በኋላ ተለቀዋል።

በወቅቱ መንግሥት የ“አፍሪካ ኢንተለጀንስ” ጋዜጠኛው እና የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) የፖለቲካ ኦፊሰር በቁጥጥር ስር የዋሉት “ከፋኖ እና ኦነግ ሸኔ ጋር በመተባባር ሁከት እና ብጥብጥ ለማስነሳት በመንቀሳቀሳቸው ነው” ብሎ ነበር።

በኦሮሞ ፖለቲካ ውስጥ ጉልህ እንቅስቃሴ በማድረግ የሚታወቁት እና በፓርቲያቸው ውስጥ በከፍተኛ ኃላፊነት ላይ የነበሩት አቶ በቴ ከዚህ ከቀደምም ለተደጋጋሚ እስር ሲዳረጉ ቆይተዋል።

በ2013 ዓ.ም. አጋማሽ ላይ በኦሮሚያ ክልል ቡራዩ ከተማ በቁጥጥር ስር የሚገኙ የኦነግ ከፍተኛ አመራሮችን ለመጠየቅ በሄዱበት ተይዘው ረዘም ላለ ጊዜ በእስር መቆየታቸው ይታወሳል።

አቶ በቴ በቡራዩ በእስር በነበሩበት ወቅት አያያዛቸው የሰብዓዊ መብትን ያከበረ አይደለም በማለት ለቀናት የረሃብ አድማ በማድረጋቸው ከፍተኛ የጤና መቃወስ አጋጥሟቸው ነበር።

የአቶ በቴን ግድያ በተመለከተ መቂ ከተማ ወደሚገኙ የከተማው ፖሊስ እና ባለስልጣናትን ለማነጋገር ያደረገውን ጥረት በስልክ አገልግሎት መቋረጥ ምክንያት ሊሳካ አልቻለም።

የኦሮሞ ነጻነት ግንባር ፓርቲ ኃላፊዎችንም ለማግኘት ያደረግነው ጥረት ስልክ ባለመነሳቱ ሊሰምር አልቻለም።  ዘገባው የቢቢሲ ነው፡፡

selegna

By selegna

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *