በባሕርዳር ከተማ ቀበሌ 14 ሶላት ሰግደው ሲመለሱ የነበሩ አራት የአንድ ቤተሰብ አባላት መጋቢት 29/2016 ዓ.ም. ማንነታቸው ባልታወቁ ታጣቂዎች መገደላቸውን የአማራ ክልል የእስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት ገለጸ።

ከቤተሰቡ አባላት ጋር የነበሩ አንድ ጎረቤትም በዚሁ ጥቃት መገደላቸውን የከተማው የእስልምና ጉዳዮች ምክር ቤት የፋይናንስ አስተዳዳሪ ኃላፊ አቶ አሊ ጌታሁን ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ጥቃቱን የፈጸመው አካል እስካሁን እንደማይታወቅ የገለጹት አቶ አሊ ሟቾቹ “ገንዘብ ስጡን የሚሉ ማስፈራሪያዎች ይደርሷቸው እንደነበር” የአካባቢው ነዋሪዎች እንደነገሯቸው ገልጸዋል።

በባለፉት ወራት በእስልምና እምነት ተከታዮች ላይ የሚደርሱ ጥቃቶች እየተበራከቱ እንደሆነ ለቢቢሲ የተናገሩት አቶ አሊ፣ ከቀናት በፊት በጎንደር እንዲሁ የተወሰኑ ሰዎች መገደላቸውን ጠቅሰዋል።

በተለያዩ አካባቢዎች ገንዘብ ክፈሉ እየተባሉ የሚታገቱ የዕምነቱ ተከታዮች ቁጥርም ጨምሯል የሚሉት ኃላፊው፣ በክልሉ ወረታ አካባቢ ገንዘብ አልከፍልም ያለ አንድ ግለሰብ አሰቃቂ ጥቃት እንደተፈጸመበት አንስተዋል።

በክልሉ በባለፉት ስምንት ወራት ከ80 በላይ ሙስሊሞች መገደላቸውንም የአማራ ክልል የእስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት ሰኞ ማምሻውን ባወጣው መግለጫ አመልክቷል።

በክልሉ በመከላከያ እና በፋኖ ታጣቂዎች መካከል እየተካሄደ ያለው ግጭት የእስልምና እምነት ተከታዮችን በከፋ አደጋ ላይ መጣሉን ይኽው መግለጫ ያስረዳል።

“ግጭቱ ሕዝባችንን የከፋ ዋጋ እያስከፈለ ስለሆነ በዋናነት በሙስሊሞች ላይ እየደረሰ ያለዉ ግፍ፣ መፈናቀል፣ ዘረፋ፣ መታገት እና መገደል ከጊዜ ጊዜ እየተባባሰ በመሄድ ላይ ነዉ” ብሏል።

በክልሉ የሚታገቱ፣ የሚሰወሩ እንዲሁም የሚገደሉ ንጹኃን ዜጎች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መሆኑን የጠቆመው መግለጫው፣ የችግሩ መክፋት “ሕዝቡን በተለይም ሙስሊሙን ማኅበረሰብ መከራ ውስጥ ጨምሮታል” ብሏል።

ምክር ቤቱ በመግለጫው እሁድ ዕለት ታጣቂዎች በሞጣ ከተማ አንድን ወጣት አግተው ቤተሰቦችን በማስፈራራት ሦስት መቶ ሺህ ብር ከተቀበሉ በኋላ በአሰቃቂ ሁኔታ ገድለው መጣላቸውንም ጠቅሷል።

ከቀናት በፊት፣ በጎንደር ከተማ ማክሰኝት አካባቢ አራት ሙስሊሞች መገደላቸውን እንዲሁም ቢቢቸና ከተማ ደግሞ ባልና ሚስት “ለመንግሥት ግብር ከፈላችሁ ተብለው” መገደላቸውንም ጠቅሷል።

በክልሉ ከተገደሉት በተጨማሪ 47 ሰዎች መታገታቸውን፣ በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ሙስሊሞች ደግሞ መፈናቀላቸውን እንዲሁም ከ260 በላይ ዝርፊያዎች ተፈጽመዋል ብሏል።

በክልሉ እየተፈጸመ ያለውን ዝርፊያ፣ ስቃይ፣ እንግልት መገደል እና መፈናቀልንም በጽኑ እንደሚያወግዝም መግለጫው አትቷል።

“ይህ ሰላማዊ ዜጎች ላይ ያነጣጠረ ግፍ እና ግድያ ለዘመናት አብሮ እና ኅብረት ፈጥሮ የኖረዉን የሕዝባችንን አብሮነት ለማናጋት የታሰበ ስለሆነ በጋራ እንታገለው” ሲልም ጥሪውን አስተላልፏል።

እነዚህንም ጥቃቶች ለማስቆም መንግሥት፣ የክልሉ ሕዝብ የሌላ እምነት ተከታዮች፣ የሃይማኖት አባቶች እና ጉዳዩ የሚመለከታቸው አካላት በሙሉ የበኩላቸውንም እንዲያደርጉም መግለጫው ጠይቋል።

በባሕር ዳር ከተማ ስለተፈጸመውም ሆነ የክልሉ እስልምና ጉዳዮች ምክር ቤት ስለጠቀሳቸው ጥቃቶች የክልሉ መንግሥት እስካሁን ያለው ነገር የለም።   ዘገባው የቢቢሲ ነው፡፡

selegna

By selegna

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *