ኢትዮጵያ ራሷን ነጻ አገር ብላ ካወጀችው ሶማሊላንድ ጋር በፈረመችው የባህር የመግባቢያ ስምምነት ከሶማሊያ ጋር ቁርሾ ውስጥ ገብታለች።

በሁለቱ አገራት መካከል ያለው ግንኙነት መቃቃር ተካሮም ሶማሊያ በሞቃዲሾ ተቀማጭ የሆኑትን የኢትዮጵያ አምባሳደር ሙክታር ሞሐመድ ዋሬ አገሪቷን ለቀው እንዲወጡ አዛለች።

ከዚህም በተጨማሪ በሶማሊላንድ እና በከፊል ራስ ገዟ ፑንትላንድ ውስጥ የሚገኙት የኢትዮጵያ ቆንስላ ጽሕፈት ቤቶችም እንዲዘጉ ሶማሊያ ውሳኔ አስተላልፋለች። ሶማሊያ በውስጥ ጉዳዬ ጣልቃ እየገባች ነው ስትል ከከሰሰቻት ኢትዮጵያም አምባሳደሯን “ለአጠቃላይ ምክክር” ጠርታለች።

ኢትዮጵያ ከዚህ ቀደም ሶማሊያ የምታቀርበውን የግዛት ሉዓላዊነት መጣስ ክስ ውድቅ ብታደርግም በአሁኑ የዲፕሎማሲ ግንኙነት ላይ የሰጠችው አስተያየት የለም።

ለሁለቱ አገራት ውዝግብ መነሻው ምንድን ነው?

በያዝነው ዓመት ታኅሳስ መጨረሻ አካባቢ ኢትዮጵያ ራሷን በነጻ አገርነት ካወጀችው ሶማሊላንድ ጋር የወደብ የመግባቢያ ስምምነት መፈረሟን ተከትሎ ነው የሁለቱ አገራት ግንኙነት መቃቃር የተከሰተው።

አሳሪ ያልሆነው የመግባቢያ ስምምነት ኢትዮጵያ ለወደፊቱ የባህር ኃይል ሰፈር ማቋቋም የሚያስችላትን 20 ኪሎ ሜትር የሚሸፍን የባህር ጠረፍ ለማግኘት የሚያስችላት ነው።

ይህም የመግባቢያ ስምምነት ሶማሊላንድን የግዛቷ አካል አድርጋ የምትቆጥረውን ሶማሊያን አስቆጣ። ስምምነቱን እንደ ወረራ ያየችው ሶማሊያ የሰላም ማነቆ ስትልም ጠራችው።

ኢትዮጵያ በምላሹ ለሶማሊላንድ የአገርነት እውቅና በመስጠትም ከዓለም የመጀመሪያዋ አገር እንደምትሆንም የሶማሊላንድ ባለስልጣናት ገልጸዋል።

ሶማሊላንድ ራሷን በነጻ አገርነት ካወጀች አስርት ዓመታት ተቆጥረዋል። ከሶማሊያ ከተገነጠለች ከ30 ዓመታት በላይ ቢሆንም ነጻ አገርነቷ በአፍሪካ ኅብረትም ሆነ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዕውቅና አልተሰጠውም።

የኢትዮጵያ ባለስልጣናት ለሶማሊላንድ ዕውቅና እንደሚሰጡም በይፋ አልገለጹም። ይልቁንም እንደ ኢትዮጵያ አየር መንገድ ባሉ አትራፊ ተቋማት ድርሻ እንደሚሰጡ ተናግረዋል።

የሁለቱን አገራት ውጥረቶች ለማርገብ የተደረጉ ጥረቶች ነበሩ?

የሶማሊያን የግዛት አንድነት እንዲከበር በጠየቁት የአፍሪካ ኅብረት፣ አሜሪካ እና ሌሎች በርካታ የምዕራባውያን አገራትም የመግባቢያ ስምምነቱ ቅሬታ ማስከተሉ አልቀረም።

ቀጠናዊ ድጋፍን ለማግኘትም የሶማሊያው ፕሬዚዳንት ሐሰን ሼክ መሃመድም ዲፕሎማሲያዊ ጉብኝቶችን ወደ ኤርትራ እና ግብጽ አድርገዋል።

ሁለቱ አገራት በአሁኑ ወቅት ከኢትዮጵያ ጋር የሻከረ ግንኙነት ያላቸው ናቸው። የሁለቱን አገራት ውጥረት ለማርገብ ዲፕሎማሲያዊ ጥረቶች የነበሩ ቢሆንም የመግባቢያ ስምምነቱ በይፋ እንዲቀለበስ ሶማሊያ ያቀረበችው ጥያቄ እስካሁን ምላሽ አላገኘም።

ኢትዮጵያ ለምን የባህር መዳረሻ አስፈለጋት?

ወደ 120 ሚሊዮን ሕዝብ ያላት ኢትዮጵያ ባህር በር አልባ ከሆኑ በርካታ ሕዝብ ካላቸው የዓለማችን አገሮች አንዷ ናት።

ከ90 በመቶ በላይ የሚሆነው የአገሪቱ ዓለም አቀፍ ንግድ የሚከናወነው አነስተኛ በሆነችው ጎረቤቷ ጂቡቲ በኩል ነው። ከዚህም ጋር ተያይዞ የአዲስ አበባ ባለስልጣናት ዘላቂነት እንደሌለው አድርገው ይመለከቱታል። የሶማሊላንድ የባህር በር መግባቢያ ስምምነት ከመፈረሙ በፊት የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ የባህር በር መዳረሻ ለአገሪቱ “የህልውና ጉዳይ” ነው ሲሉም ተናግረው ነበር።

ኢትዮጵያ የባህር በር ለማግኘት አማራጭ ሰላማዊ መንገዶችን ታያለች ይህ ካልተሳካ “ኃይል እንጠቀማለን” ማለታቸው በቀጠናው ውጥረት እንዲፈጠር ምክንያት ሆኗል።

ኢትዮጵያ ባህር በር አልባ ብትሆንም የባህር ኃይል የመገንባት ፍላጎት አላት። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አገሪቷ ከአየር እና ከምድር ጦሯ ጋር የተስተካከለ የባህር ኃይል ማቋቋም አለባት ሲሉም ከስድስት ዓመት በፊት ተናግረው ነበር።

የአሁኑ የሶማሊያ እርምጃዎች ወደየት ያመራሉ?

ሶማሊያ የኢትዮጵያ ዲፕሎማቶችን ማባረሯ በሁለቱ አገራት መካከል ያለውን ውጥረት ለማባበሱ ማሳያ ነው።

ውሳኔው የተገለጸው ኢትዮጵያ የሶማሊያ አካል እና ከፊል ራስ ገዝ የሆነችውን የፑንትላንድ ባለስልጣናት ካስተናገደች ከአንድ ቀን በኋላ ነው።

ፑንትላንድ በቅርቡ የሶማሊያ መንግሥት ባደረገው ሕገ መንግሥት ማሻሻያ ምክንያት ውዝግብ ውስጥ ገብታለች።

ባለፈው ሳምንት የሶማሊያ የፌደራሉ ፓርላማ የሕገ መንግሥት ማሻሻያዎችን ያጸደቀ ሲሆን ከዚህም መካከል በቀጥታ ምርጫ ፕሬዚዳንት እንዲመረጥ እና ፕሬዚዳንቱ የአገሪቱን ጠቅላይ ሚኒስትር እንዲሾሙ የሚያስችል ሥልጣንን አካቷል። ይህ የአስተዳደር ማሻሻያ በፑንትላንድ ግዛት በኩል ተቀባይነት አላገኘም።

ከአውሮፓውያኑ 1990ዎቹ ጀምሮ ከፊል የራስ ገዝ አስተዳደር ያላት ፑንትላንድ ከፌደራሉ የሶማሊያ ሥርዓት እወጣለሁ ብላለች። ይህ ብቻ ሳይሆን ብሔራዊ ሕዝበ ውሳኔ እስኪደረግ ድረስም ራሷን እንደምታስተዳድርም ገልጻለች።

በእነዚህ ውዝግቦች መካከልም የፑንትላንድ ልዑካን ወደ አዲስ አበባ ያደረጉት ጉዞ በሶማሊያ ባለስልጣናት ዘንድ ተቀባይነት አላገኘም።

ኢትዮጵያ በአጸፋው ምን ዓይነት እርምጃ ትወስዳለች የሚለው ግልጽ ባይሆንም በአሁኑ ወቅት አገራቱ ግጭት ውስጥ የሚገቡ አይመስሉም።

ሆኖም በአሁኑ ወቅት የሁለቱ አገራት ግንኙነት መሻከር በአፍሪካ ቀንድ ጽንፈኝነትን ለመታገል የሚደረገው ትግል ላይ ተጽዕኖ ሊያሳድር ይችላል ተብሏል።

በሁለቱ አገራት መካከል ያለውን መቃቃር አልሻባብ አዳዲስ ተዋጊዎችን ለመመልመል ሊጠቀምበት እንዲሁም የደኅንነት ስጋቶችን ሊጨምር ይችላል የሚል ስጋትን አጭሯል።

ኢትዮጵያ በሶማሊያ ላለው በአፍሪካ ኅብረት የሚመራው የሰላም አስከባሪ ተልዕኮ ወታደሮችን ከሚልኩ አገራት አንዷ ናት።

የሰላም አስከባሪው በያዝነው የአውሮፓውያኑ ዓመት መጨረሻ የጸጥታውን ኃላፊነት ለሶማሊያ መንግሥት በማስረከብ ከአገሪቱ ይወጣል ተብሎም ይጠበቃል። ሆኖም በሁለቱ ጎረቤታሞች አገራት ያለው ውጥረት ሽግግሩን ሊጎዳው ይችላል እየተባለ ነው።    ዘገባው የቢቢሲ ነው፡፡

selegna

By selegna

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *