በአማራ ክልል የተከሰተውን አለመረጋጋት ተከትሎ በቁጥጥር ስር የዋሉት የክልል እና የፌደራል ምክር ቤት አባላት እና ፖለቲከኞች ከስድስት ወራት እስር በኋላ ዛሬ ለሁለተኛ ጊዜ ፍርድ ቤት ይቀርባሉ።

ግለሰቦቹ በ2015 ዓ.ም. ማብቂያ ላይ በአማራ ክልል ከተጣለው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ጋር በተያያዘ በቁጥጥር ስር ከዋሉ በኋላ ክስ ሳይመሠረትባቸው ለስድስት ወራት በእስር ላይ ቆይተው ባለፈው ሳምንት ለመጀመሪያ ፍርድ ቤት ቀርበዋል።

የፍትሕ ሚኒስቴር ባለፈው ሳምንት ረቡዕ መጋቢት 18/2016 ዓ.ም. የአማራ ክልል፣ የአዲስ አበባ እና የፌደራል ምክር ቤቶች አባል በሆኑት በአቶ ዮሐንስ ቧያለው፣ በዶ/ር ካሳ ተሻገር እና በአቶ ክርስቲያን ታደለ ላይ ክስ መሥርቷል።

በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ችሎት የሕገ መንግሥት እና የሽብር ወንጀል ችሎት የቀረበው የዐቃቤ ሕግ ክስ የሚመለከተው 52 ግለሰቦችን ነው።

ዐቃቤ ሕግ የወንጀል ሕጉን እና የፀረ ሽብር አዋጅን ጠቅሶ የመሠረተው የክስ የተከፈተው የአማራ ክልል ምክር ቤት አባል በሆኑት በአቶ ዮሐንስ ቧያለው ስም ነው።

ከ52ቱ ተከሳሾች መካከል 14ቱ ባለፈው ሳምንት በነበረው የችሎት ውሎ ፍርድ ቤት ተገኝተው ክሳቸውን ተቀብለዋል። ቀሪ ሰላሳ ስምንቱ ተከሳሾች ፍርድ ቤት አለመቅረባቸውን ከተከሳሽ ጠበቆች አንዱ የሆኑት አቶ ሄኖክ አክሊሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ዐቃቤ ሕግ ክስ ከተመሠረተባቸው 52 ግለሰቦች መካከል፤ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባሉ አቶ ክርስቲያን ታደለ፣ የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት አባሉ ዶ/ር ካሳ ተሻገር እንዲሁም የተቃዋሚው የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትሕ (ኢዜማ) ሊቀመንበር ዶ/ር ጫኔ ከበደ ይገኙበታል።

ከዚህ በተጨማሪም በአማራ ክልል እየተካሄደ ባለው የትጥቅ እንቅስቃሴ ውስጥ ተሳታፊ የሆኑት አቶ እስክንድር ነጋ እና ዘመነ ካሴ ደግሞ ፍርድ ቤት ካልቀረቡት 38 ተከሳሾች መካከል ናቸው።

ቢቢሲ የተመለከተው እና በ68 ገጾች የተዘጋጀው የዐቃቤ ሕግ የክስ ሰነድ በተከሳሾቹ ላይ አራት ክሶችን አቅርቧል።

የመጀመሪያው እና በሁሉም ተከሳሾች ላይ የቀረበው ክስ የወንጀል ሕጉን እና የሽብር ወንጀልን ለመቆጣጣር እና ለመከላከል የወጣውን አዋጅ በመተላለፍ የተፈጸመ “ወንጀልን” የሚመለከት ነው።

የዐቃቤ ሕግ የክስ ሰነድ ተከሳሾቹ፤ “የፖለቲካ ርዕዮተን በኃይል ለማስፈጸም በማሰብ” ተሰብስበው ስለመደራጀታቸው ያትታል።

ከዚህ በተጨማሪም፤ “[ተከሳሾቹ] የአማራ ርስት ናቸው የሚሏቸውን መሬቶች በወታደራዊ ኃይል ለማስመለስ እና አገርን ‘በአማራ እሳቤ ብቻ መገዛት አለባት’ በሚል” ስምምነት ላይደ ደርሰዋል ሲል ይከስሳል።

የክስ ሰነዱ ተከሳሾች በወንጀሉ ላይ አላቸው ያለውን ተሳትፎ በዝርዝር አብራርቷል።

በዚህ መሠረት አንደኛ ተከሳሽ አቶ ዮሃንስ ቧያለው፤ “የታጠቁ ቡድኖች የሚያከናውኑትን የሽብር ድርጊት በፖለቲካ አቀናጅ እና አመራር ሰጪነት ለመምራት. . . የሽብር ድርጊት ለሚፈጽም ቡድን ራሱን አመራር አድርጎ [ሰይሟል]” ሲል የዐቃቤ ሕግ የክስ ሰነድ ያመለክታል።

ተከሳሹ “ለተለያዩ የቡድኑ አባላት አመራር መሆኑን በመግለጽ ትዕዛዞችን በመስጠት [አስፈጽሟል]” ሲል ክሱ ያክላል።

በሥልጣን ላይ ያለውን ብልጽግና ፓርቲ ወክለው የአማራ ክልል ምክር ቤት የገቡት አቶ ዮሐንስ፤ “በምርጫ ሥርዓት የተዋቀረ መንግሥታዊ ሥርዓት በኃይል እርምጃ እንዲፈርስ በማሰብ” መመሪያ ሰጥተዋል በሚልም በዐቃቤ ሕግ ተከስሰዋል።

የዐቃቤ ሕግ ክስ አቶ ዮሐንስ በምዕራብ ጎጃም ዞን፤ “የመንግሥትን መዋቅር በማፍረስ በቀበሌ በማዋቀር እንዲረከብ እና ወረዳዎችን ደግሞ ይህ ታጣቂ ቡድን እንዲረከብ” ትዕዛዝ ሰጥተዋል ይላል።

“የመከላከያ ሠራዊት እንቅስቃሴን ለመገደብ” እና “ማኅበራዊ አገልግሎቶች እንዲቋረጡ” በሞጣ እና በደጀን በኩል ዋናው የአስፋልት መንገድ እንዲዘጋ “ለታጣቂው ቡድን አመራሮች መመሪያ የሰጠ እና ያስፈጸመ” መሆኑን ክሱ ላይ ተጠቅሷል።

አቶ ዮሐንስ “30 የሳተላይት ስልኮችን በድበቅ ወደ አገር ውስጥ በማስገባት ለሽብር ቡድን አባላት እንዲከፋፈል” ማድረጋቸውን የክስ ሰነዱ ያስረዳል። በዐቃቤ ሕግ ክስ መሠረት ተከሳሹ ይህን ያደረጉት፤ “የሚያስተባብረው የሽብር ቡድን አባላት እርስ በራሳቸው መገናኘት እንዲችሉ ነው” ብሏል።

አቶ ዮሐንስ ለታጣቂዎች አቀረቡት የተባለው ግን የሳተላይት ስልኮችን ብቻ አይደለም። ተከሳሹ “ጋሸና አካባባቢ ላሉ የታጣቂ ቡድኖች ሁለት ሺህ የክላሽ እና የመትረየስ ተተኳሽ ያቀረበላቸው” መሆኑን ዐቃቤ ሕግ በክሱ ላይ ገልጿል።

አቶ ዮሐንስ ቧያለው በቁጥጥር ስር ከመዋላቸው በፊት ባሉት ጊዜያት አባል የነበሩበት የብልጽግና መንግሥት ላይ ትችቶችን ሲያቀርቡ ነበር። የቀድሞው ባለሥልጣን ለመጨረሻ ጊዜ ይዘውት የነበረው የመንግሥት ኃላፊነት የውጭ ጉዳይ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተርነት ነው።

የውጭ ጉዳይ ኢንስቲትዩትን ለአንድ ዓመት ከስምንት ወር ከመሩ በኋላ ከሁለት ዓመታት በፊት ሚያዚያ 2014 ዓ.ም. ከሥልጣን መነሳታቸው ይታወሳል። አቶ ዮሐንስ የብልጽግና ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል ነበሩ።

ብልጽግናን ከመሠረቱት ፓርቲዎች አንዱ የሆነው የአማራ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (አዴፓ) ምክትል ሊቀመንበር እና የፓርቲውን ዋና ጽህፈት ቤትንም በኃላፊነት መርተዋል።

አቶ ዮሐንስ ከሌሎች በእሳቸው መዝገብ ከተካተቱ ሌሎች ተከሳሾች በተለየ ሁኔታ ተጨማሪ ክሶች ቀርበውባቸዋል። ይህም ክስ፤ የጦር መሳሪያ አስተዳደር እና ቁጥጥር አዋጅን ተላልፈዋል የሚል ነው።

የዐቃቤ ሕግ የክስ ሰነድ “ተከሳሽ ጦር መሳሪያ ለመያዝ የጸና ፈቃድ ሳይኖረው. . . አንድ ካዝና (ካርታ) እና ሁለት የሽጉጥ ጥይቶችን ይዞ የተገኘ በመሆኑ በፈጸመው የጸና ፈቃድ ሳይኖረው የጦር መሳሪያ ይዞ በመገኘት ወንጀል ተከስሷል” ይላል።

ሌላኛው እና በአቶ ዮሐንስ ላይ የቀረበው ክስ ደግሞ፤ “የቴሌኮም መሳሪያ ለመያዝ ፈቃድ ሳይኖረው. . . የቴሌኮም መሳሪያ ይዞ መገኘት” የሚል ነው። የዐቃቤ ሕግ ክስ አቶ ዮሐንስ በታኅሣሥ 9/2015 ዓ.ም. በባሕር ዳር ከተማ ሁለት ቱራያ የሳተላይት ስልኮችን ይዘው መገኘታቸውን ያትታል።

በአቶ ዮሐንስ ስም በሚጠራው የክስ መዝገብ ሁለተኛ ተከሳሽ ሆነው የቀረቡት የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄን (አብን) ወክለው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል የሆኑት አቶ ክርስቲያን ታደለ ናቸው።

የዐቃቤ ሕግ ክስ አቶ ክርስቲያን “ራሱን በአመራር ሰጪነት በመሰየም ሽብር ኃይሉን በማደራጀት ይሄው ኃይል የአገር መከላከያ ላይ ጥቃት እንዲያደርስ ትዕዛዝ ሲሰጥ እና ሲያስፈጽም [ነበር]” ይላል።

አቶ ክርስቲያን በቋሪት እና ደጋ ዳሞት አካባቢ ለሚንቀሳቀስ “የሽብር ኃይል አስተባባሪዎችን”፤ “መከላከያ ሠራዊቱ ትክክለኛ ስላልሆነ እንዲያጠቁት፣ ይህን ማድረግ ሕገ መንግሥታዊ መብት መሆኑን በማሳሰብ ጥቃት እንዲፈጸም ትዕዛዝ በመስጠት [አስፈጽሟል]” ሲል ዐቃቤ ሕግ ከሷል።

አቶ ክርስቲያን እንደ አንደኛ ተከሳሽ ሁሉ የጦር መሳሪያ አስተዳደር እና ቁጥጥር አዋጅን በመተላለፍ ሁለተኛ ክስ ተመስርቶባቸዋል።

አቶ ክርስቲያን የጦር መሳሪያን ለመያዝ ፈቃድ ሳይኖራቸው አንድ ታጣፊ ክላሽ ከነ ካርታው እና 30 የክላሽ ጥይት በቤታቸው ይዘው መገኘታቸውን ዐቃቤ ሕግ በክስ ሰነዱ ላይ አስፍሯል።

ሌላኛው የምክር ቤት አባል ዶ/ር ካሳ ተሻገርም በተመሳሳይ በዚሁ የክስ መዝገብ ውስጥ ተካትተዋል።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክር ቤት አባል የሆኑት ዶ/ር ካሳ ያለመከሰስ መብታቸው የተነሳው ባለፈው የካቲት አጋማሽ ላይ ነበር።

ባለፈው ዓመት ነሐሴ ላይ በቁጥጥር ስር ዋሉት ዶ/ር ካሳ፤ “የታጠቁ ቡድኖች የሚያከናውኑትን የሽብር ቡድን በፖለቲካ አቀናጅ እና አመራር ሰጪነት ለመምራት [ወስኗል]” የሚል ክስ ቀርቦባቸዋል።

ከዚህ በተጨማሪም የዐቃቤ ሕግ የክስ ሰነድ ተከሳሹ “[በአማራ] ክልል በትጥቅ የተደገፈ ትግልን ጨምሮ ዘርፈ ብዙ ትግል እንዲደረግ በክልሉ የሚንቀሳቀሱ ታጣቂዎች የሚመሩበት ሰነድ [አዘጋጅቷል]” ይላል። ዐቃቤ ሕግ ዶ/ር ካሳ አዘጋጁት ያለው ሰነድ፤ “የጉሬላ ውጊያ መሠረታዊ መርሆዎች እና ጦርነት እና የጦርነት ስትራቴጂ” የሚል መሆኑን በክሱ ላይ ጠቅሷል።

የኢዜማ ሊቀመንበር ሆኑት ዶ/ር ጫኔ ከበደ ደግሞ ከአራተኛ ተከሳሽ ጋር በመሆን “በአማራ ክልል በትጥቅ የተደገፈ የሽብር ድርጊት የሚፈጽም ቡድንን ለመምራት እንዲሁም የሽብር ድርጊቱን አገራዊ ለማድረግ. . . የኢትዮጵያውያን አንድነት ግምባር (ኢአግ) የተባለ የኅቡዕ ድርጅት በማቋቋም [መርተዋል] በሚል ተከስሰዋል።

የዐቃቤ ሕግ የክስ ሰነድ ዶ/ር ጫኔ እና በአራተኛ ተከሳሽነት የተጠቀሱት አቶ በላይ አዳሙ፤ “በጋራ ላቋቋሙት ኅቡዕ ቡድን አመራር በመሆን ቡድኑ የሚመራበትን ስትራቴጂዎችን በመቀየስ እና አቅጣጫ በመስጠት የሽብር ድርጊት ሲያስፈጽሙ [ነበር]” ይላል።

ለሁለት ዓመት ያህል ገደማ በእስር ላይ ቆይተው ታኅሣሥ 2014 ዓ.ም. ከእስር የተፈቱት አቶ እስክንድር ነጋም በዚሁ የክስ መዝገብ ተካትተዋል። የቀድሞው የባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ፓርቲ ፕሬዝዳንት አቶ እስክንድር “የአማራ ሕዝባዊ ግንባር” የተባለ “የሽብር ቡድን” ማቋቋማቸውን ዐቃቤ ሕግ በክሱ ላይ አስፍሯል።

ስድስተኛ ተከሳሽ ሆነው በሌሉበት ክስ የተመሰረተባቸው አቶ እስክንድር ራሳቸውን የዚህ ግንባር መሪ በማድረግ መሰየማቸውንም ዐቃቤ ሕግ አስታውሷል።

ተከሳሹ “በአማራ ክልል ተበታትነው ያሉ የሽብር ቡድኖችን በአመራሮቻቸው አማካኝነት በአንድ ወታደራዊ ዕዝ ስር ለመሰብሰብ እና መጠነ ሰፊ ጉዳት ለማድረስ እንዲመቸው የአማራ ሕዝባዊ ግንባር ኮማንድ ፖስት የመሠረተ እና የመራ” መሆኑን ዐቃቤ ሕግ በክሱ ላይ አትቷል።

ሰባተኛ ተከሳሽ ሆነው የቀረቡት አቶ ዘመነ ካሴም እንደ አቶ እስክንድር ሁሉ ለወራት ያህል በእስር ላይ ቆይተዋል። ባለፈው ዓመት ግንቦት ወር ከእስር የተፈቱት አቶ ዘመነ “መንግሥትን በኃይል እርምጃ ከሥልጣን ለማስወገድ በማሰብ የአማራ ሕዝባዊ ኃይል የሚል የሽብር ቡደን በማቋቋም” ክስ ተመስርቶባቸዋል።

አቶ ዘመነ ራሳቸውን የቡድኑ መሪ አድርገው በመሰየም በአማራ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች ያሉ “የክልሉ የፀጥታ አስከባሪ አካላት እና የአገር መከላከያ ሠራዊት ላይ ጥቃት እንዲፈጸም ያስተባበረ የመራ እና ያስፈጸመ” መሆኑን የክስ ሰነዱ ያትታል።

“የሽብር ወንጀል ድርጊት” በመፈጸም የተከሰሱ ሌሎች ተከሳሾች “የወንጀል ተሳትፎም” ዐቃቤ ሕግ የክስ ሰነዱ ላይ በዝርዝር አስፍሯል።

ከዚህ በተጨማሪም ዐቃቤ ሕግ ተከሳሾች ፈጸሙት ባለው “የወንጀል ድርጊት” ምክንያት ደረሰ ያለውን ጉዳት ዘርዝሮ አቅርቧል።

በዚህም “በክልሉ የፀጥታ አካላት እና ሰላማዊ ሕዝብ ላይ ጥቃት በመፈጸም እና በማስፈጸም በጥቃቱ ከ1,100 በላይ የፀጥታ እና የሲቪሎች ላይ የሞት ከ600 በላይ በፀጥታ እና በሲቪሎች ላይ ከባድ እና ቀላል የአካል ጉዳት [አድርሰዋል]” ብሏል።

ከዚህ በተጨማሪም በአማራ ክልል የተለያዩ ከተሞች ማረሚያ ቤቶች ላይ በፈጸሙት ጥቃት 5,689 ታራሚዎችን “እንዲያመልጡ” ማደረጋቸውን ዐቃቤ ሕግ ገልጿል። በማረሚያ ቤቶቹ ላይ 123.5 ሚሊዮን ብር ገደማ ጉዳት መድረሱንም አክሏል።

ከ90 በላይ የመንግሥት እና የግለሰብ ተሽከርካሪዎች “እንዲዘረፉ እና እንዲወድሙ [አድርገዋል]” የተባሉት ተከሳሰሾቹ፤ “ከ9ሺህ ኩንታል በላይ የአፈር ማዳበሪያ የዘረፉ እና እንዲዘረፍ ያደረጉ” መሆናቸውን በክስ ሰነዱ ላይ አስፍሯል።

ዐቃቤ ሕግ በተከሳሾቹ ላይ ባቀረበው ክስ “በሕዝብ እና የድርጅት ተቋማት ላይ ጥቃት በማድረስ” ከ48 ቢሊዮን ብር በላይ ንብረት “የዘረፉ፣ ያወደሙ፣ እንዲወድሙ እና እንዲዘረፉ ያደረጉ” መሆናቸውን ጠቅሷል።

በዚህም ምክንያት “ተከሳሾች በዋና ወንጀል አድራጊነት በቀጥታ እና በተዘዋዋሪ ተካፋይ በመሆን በፈጸሙት የሽብር ድርጊት ወንጀል” ተከስሰዋል።   ዘገባው የቢቢሲ ነው፡፡

 

selegna

By selegna

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *