የኢትዮጵያ እና የኤምሬትስ አየር መንገድ አውሮፕላኖች ባለፈው እሁድ በሶማሊያ የአየር ክልል ላይ ከመጋጨት ለጥቂት መትረፋቸው ተገለጸ።

ነጻ አገርነቷን ያወጀችው የሶማሊላንድ ሲቪል አቪዬሽን እና ኤርፖርቶች ባለሥልጣን ሁለቱ አውሮፕላኖች አየር ላይ ሊጋጩ ተቃርበው የነበረው በሶማሊያ የአየር ትራፊክ ተቆጣጣሪዎች አሻሚ እና የተሳሳተ ትዕዛዝ ነው ብሏል።

እንደ ባለሥልጣኑ መግለጫ እሁድ መጋቢት 15/2016 ዓ.ም. ምሽት ላይ በሶማሊያ የአየር ክልል ውስጥ ሲበሩ የነበሩት አውሮፕላኖች ሳይጋጩ የቀሩት የሶማሊላንድ የአየር ትራፊክ ተቆጣጣሪዎች እና የኢትዮጵያ አየር መንገድ አብራሪዎች በወሰዱት “ፈጣን እና ትክክለኛ እርምጃ” ነው።

የበረራ መቆጣጠሪያ ድረ-ገጽ በሆነው ፍላይትራዳር24 ላይ መመልከት እንደሚቻለው ክስተቱ ባጋጠመበት ወቅት የኢትዮጵያ አየር መንገድ ቦይንግ 737 ማክስ 8 አውሮፕላን ከአዲስ አበባ ወደ ሕንዷ ቤንጋሉሩ በ37ሺህ ጫማ ከፍታ ላይ ሲበር ነበር።

በተመሳሳይ ሰዓት የኤምሬትሱ ቦይንግ 777 አውሮፕላን መነሻውን ናይሮቢ ኬንያ አድርጎ ወደ ዱባይ በተመሳሳይ 37ሺህ ጫማ ከፍታ ሲበር ይታያል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ የበረራ ቁጥር ኢቲ690 በሶማሊያ የአየር ክልል ሲበር ከነበረበት 37ሺህ ጫማ ምሽት 21፡43 (ሌሊት 6፡43) ሲል በጥቂት ደቂቃዎች ውስጥ ከፍታውን በፍጥነት ጨምሮ ወደ 39ሺህ ጫማ ከፍ አድርጓል።

በዚህም ምክንያት በሁለቱ የመንገደኞች አውሮፕላኖች መካከል ሊከሰት ይችል የነበረን አሰቃቂ አደጋ ለማስቀረት ችሏል።

የሶማሊላንድ ሲቪል አቪዬሽን እንዳለው ይህ በአውሮፕላኖቹ መካከል አደገኛ አደጋ ሊያጋጥም የነበረው የሶማሊያ የአየር ትራፊክ ተቆጣጣሪዎች ለአብራሪዎች አሻሚ የሆነ ትዕዛዝ በመስጠታቸው ነው ሲል ከሷል።

ቢቢሲ ክስተቱን በተመለከተ ለኢትዮጵያ እና ለኤምሬትስ አየር መንገዶች ያቀረበው ጥያቄ እስካሁን ምላሽ አላገኘም።

የሶማሊያ ሲቪል አቪዬሽን በበኩሉ በጉዳዩ ላይ አስተያየት አልሰጥም ብሏል።

የሶማሊያ አየር ትራፊክ ተቆጣጣሪዎች በአገሪቱ የአየር ክልል ላይ ለሚያልፉ አብራሪዎች አሻሚ የሆነ ትዕዛዝ በመስጠት አውሮፕላኖችን አደጋ ላይ ሲጥሉ ይህ ለመጀመሪያ ጊዜ አይደለም።

ቅዳሜ የካቲት 16/ 2016 ዓ.ም. ከዶሃ ወደ ኡጋንዳ ሲበር የነበረ የኳታር አየር መንገድ አውሮፕላን ከፍታውን እንዲጨምር በሞቃዲሾ የአየር ትራፊክ ተቆጣጣሪዎች ከተነገረው በኋላ ከኢትዮጵያ አውሮፕላን ጋር ለመጋጨት ተቃርቦ እንደነበረ መዘገቡ ይታወሳል።

የሶማሊላንድ ሲቪል አቪዬሽን ሁለቱ አውሮፕላኖች ከመጋጨት የተረፉት በሁለቱ አውሮፕላኖች ላይ የተገጠመው የግጭት መከላከያ ሥርዓት ማስጠንቀቂያ በመስጠቱ ነው ብሎ ነበር።

የሶማሊያ አቪዬሽን ባለሥልጣን በበኩሉ በሁለቱ አውሮፕላን መካከል የነበረው የከፍታ ርቀት የአደጋ ስጋት የሚያስከትል አልነበረም ሲል አስተባብሎ ነበር።

ሶማሊያ ይህን ትበል እንጂ ክስተቱን ተከትሎ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ባወጣው መግለጫ ከአዲስ አበባ ወደ ዱባይ ሲበር በነበረው የአውሮፕላኑ ከፍታ ላይ የኳታር አውሮፕላን መቅረቡን አረጋግጦ፤ ክስተቱን በተመለከተ ተጨማሪ ምርመራ እና የእርምት እርምጃ እንዲወሰድ ለሶማሊያ የሲቪል አቪዬሽን ሪፖርት መደረጉን ገልጿል።

ምንም እንኳ አየር መንገዱ ዘግይቶ ቢያስተባብልም የአየር መንገዱ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ መስፍን ጣሰው ከክስተቱ በኋላ የኢትዮጵያ አውሮፕላኖች በሶማሊያ የአየር ክልል መብረር አቁመዋል ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረው ነበር።

ከሶማሊያ ተነጥላ ነጻ አገርነቷን ካወጀች ከሦስት አስርት ዓመታት በላይ የሆናት የሶማሊላንድ ሲቪል አቪዬሽንም በኤክስ ገጹ መላው ዓለም የሞቃዲሾ የአየር ትራፊክ ተቆጣጣሪዎች እውቀት እና ልምድ አናሳ መሆን ለአየር ትራንስፖርት ደኅንነት አደጋ መሆኑን መገንዘብ አለበት ብሏል።   ዘገባው የቢቢሲ ነው፡፡

selegna

By selegna

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *