በኢትዮጵያ ባለሀብቶች በተለያዩ ቦታ ለሚገኙ ታጣቂዎች የገንዘብ ድጋፍ እያደረጉ ነው ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ወቀሱ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ “ከተማኝ ግብር ከፋዮች” ጋር ባደረጉት እና ባለፈው ሳምንት ማብቂያ በመንግሥት መገናኛ ብዙኃን በተላለፈ ውይይት ላይ ባለሀብቶች ታጣቂዎችን በገንዘብ ባለመደገፍ እንዲተባበሩም ጠይቀዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከባለብቶች በሚደረግላቸው ድጋፍ የታጣቂ ቡድን መሪዎች ከፍተኛ መጠን ያለው ንብረት እና ገንዘብ እያገኙ እንደሆኑንም ተናግረዋል።

“አንዳንድ በተለያዩ ቦታ የሚታገሉ ሰዎች እስከ 10 ቤት በአባቱ፣ በወንድሙ ያለው ሰው አለ። በረሃ ታጋይ፣ አታጋይ የሚባሉ ሰዎች በጣም ሃብታሞች ናቸው። እዚያ ተቀምጦ መነገድ የሚችሉ ከሆነ ሰላም ጋር ምን አመጣቸው። ሰላም ከሆነ ንግድ የለም ማለት ነው” ሲሉ ተደምጠዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ባለሀብቶች ታጣቂዎችን ይደግፋሉ የሚለውን ክስ ለማጠናከር ምሳሌ ሲያቀርቡ “በቅርቡ እንኳን አምስት ሚሊዮን ዶላር መጥቶ በአንዱ ባንክ ይዘናል። ከፍተኛ ብር ነው የሚንቀሳቀሳው” ብለዋል።

ባለፈው ቅዳሜ መጋቢት 14/2016 የተላለፈው እና 1 ሰዓት ከ20 ደቂቃ በፈጀው ውይይት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ታጣቂዎችን በመደገፍ ባለሀብቶችን ላይ ወቀሳ ሰንዝረዋል።

“ሃብታሞች ደግሞ ማወቅ መላቅ ስለሚመስላቸው እዚህም ይጫወታሉ፣ እዚያም ይጫወታሉ። እዚህ እኛን የተከበራችሁ ይላሉ እዚያ እናንተ ጀግና ይላሉ። ሰዎቹ እየተታለሉ አገር ያምሳሉ ወጣቶችም ያልቃሉ” ሲሉ ተናግረዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንደማስረጃ ያነሱት ሌላ ጉዳይ ደግሞ ከአገር የሚወጡ ባለሀብቶችን ነው።

“አንዱ ማስረጃ፣ የሆኑ የሆኑ ሰዎች ጠፍተው ይሄዳሉ። ለምድን ነው እገሌ የጠፋው ጥሩት ወደ አገሩ ይመለስ ሲባል አይፈልግም፤ ያደረጋቸው የገንዘብ ዝውውሮች ይታወቃሉ ብሎ ስለሚያስብ አይፈልግም” ብለዋል።

ቀጥለውም ጠቅላይ ሚኒስትሩ “እኔ የማረጋግጥላችሁ ከዚህ በኋላ የኢትዮጵያን መንግሥት በሽፍነት ወይም በአማጺ መንገድ መጣል ሳይሆን መነቅነቅ አይቻልም” ብለዋል።

የውጪ ዜጎች ንብረት ማፍራት እና የችርቻሮ ንግድ መብት

ጠቅላይ ሚስትር ዐቢይ መንግሥታቸው ለውጭ አገራት ዜጎች ንብረት የማፍራት መብትን እንደሚሰጥም ይፋ አድርገዋል።

በኢትዮጵያ የውጭ አገራት ዜግነት ያላቸው ሰዎች በሙሉ በተለይ የማይንቀሳቀስ ንብረት እንዲያፈሩ ሕግ አይፈቅድም።

በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ የሥልጣን ዘመን የወጣው የፍትሃ ብሔር ሕግ የውጭ አገር ዜጋ በኢትዮጵያ ቋሚ ንብረት እንዲያፈራ አይፈቅድም። ሆኖም በ2012 ዓ.ም. የወጣው የኢንቨስትመንት አዋጅ ይህንን ሕግ ቀይሮ ለውጭ ዜጎች ንብረት የማፍራት መብትን በከፊል ፈቅዷል።

አዋጁ ከፍተኛ መጠን ያለው ኢንቨስትመንት ባለቤት የሆኑ የውጭ ዜጎች ቋሚ ንብረት የማፍራት መብትን ቢፈቅድም መሬትን በባለቤትነት እንዳይዙ ከልክሏል።

ይህንን አዋጅ ተከትሎ የወጣው ደንብ ደግሞ ቢያንስ 10 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር በሥራ ላይ ያዋለ የውጭ ዜጋ መኖሪያ ቤት መግዛት እንደሚችል ይገልጻል።

ሆኖም ይህ ሕግ እንደሚቀየር የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ሕጉ ሊወጣ የመጨረሻው ምዕራፍ ላይ መድረሱንም አመልክተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይወጣል ያሉት አዲስ ሕግ ቀደሞ ከነበረው በምን እንደሚለይ ግን ዝርዝር መረጃ አልሰጡም።

በተመሳሳይ ለውጭ ኩባንያዎች ዝግ የነበረው የችርቻሮ ንግድ ዘርፍ ክፍት እንደሚሆን ጠቅላይ ሚኒስትሩ አንስተዋል።

ልክ እንደ ቋሚ ንብረት ሁሉ በኢትዮጵያ የውጭ አገራት ኩባንያዎች በችርቻሮ ንግድ እንዳይሰማሩ በሕግ ተከልክለው ቆይቷል።

በ2012 ዓ.ም. የወጣው የኢንቨስትመንት አዋጅን ተከትሎ ይፋ የተደረገው ደንብ የችርቻሮ ንግድን ለአገር ውስጥ ባለሀብት ብቻ ይፈቅዳል።

ይህ ሁኔታ ግን በቅርቡ እንደሚቀየር ጠቅላይ ሚኒስር ዐቢይ ከከፍተኛ ግብር ከፋዮች ጋር በነበራቸው ውይይት ወቅት ተናግረዋል።

በችርቻሮ የሚሸጥ “ሱቅ ኢትዮጵያ አይገባም ታውቃላችሁ። ማሰራጨት ስለማይፈቀድ። አሁን ግን እንፈቅዳለን” ሲሉ ተናግረዋል።

እነዚህን ሰፊ የንግድ ሰንሰለት ያላቸውን የንግድ ተቋማት ለማስተናገድ የሚያስችል የገበያ ማዕከላትም እየተዘጋጁ ነው ብለዋል።

የአዲስ አበባ ሰፈሮች ፈረሳ

በአዲስ አበባ በተለይም ፒያሳ እና አከባቢው ለዘመናት የቆዩ ቤቶች እና የንግድ ተቋማት በቅርቡ መፈርስ ጀምረዋል። ይህንንም በተመለከተ በማኅበራዊ ትስስር ገጾች የድጋፍ እና ተቃውሞ አስተያየቶች ሲደመጡ ተሰምቷል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩም ይህንኑ ጉዳይ አንስተዋል።

“አዲስ አበባ ላይ ትልቁ ችግር እና ድህነት ያለው ማዕከል ላይ ነው። መርካቶ፣ ፒያሳ፣ ሜክሲኮ፣ የሚባለው [አከባቢ] ነው. . . ዋናው ችግር ያለው እዚያ ነው” ያሉት ዐቢይ “ዋናውን ችግር ደፍረን ብናፈርሰው በአምስት ዓመት ከተማው ምን እንደሚሆን ታዩታላችሁ” ብለዋል።

ቀጥለው “በዚህ ሂደት ውስጥ በግለሰብ ደረጃ አጥሬ ተነካ ብለው የሚያዝኑ ደርጅቶች ሊኖሩ ይችላሉ” ብለዋል። ግለሰቦች ብቻ ሳይሆኑ የመንግሥት ባለሥልጣናት እና ተቋማትም ቅሬታ እንዳለባቸውም ጠቅሰዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ መንግሥታቸው በያዘው ዕቅድ እንደሚገፋበት የገለጹ ሲሆን “ጩኸቱ ብዙ ነው ጨክነን ካላፈረስን ግን አገር አይሠራም. . . በአንድ ዓመት ውስጥ የአዲስ አበባን ለውጥ እናየዋለን” ብለዋል።

ባለሀብቶች “ከሃሜት ወጥተው” በትዕግስት እንዲጠብቁም ጠይቀዋል::     ዘገባው የቢቢሲ ነው፡፡

selegna

By selegna

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *