የብሔራዊ ተሃድሶ ኮሚሽን ኮሚሽነር አምባሳደር ተሾመ ቶጋ “በግል ምክንያት” በፈቃዳቸው ከኃላፊነታቸው ለቀቁ።

በኮሚሽነሩ ምትክ የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ የውጭ ፖሊስ አማካሪ አቶ ተመስገን ጥላሁን መተካታቸውን ኮሚሽኑ አስታውቋል።

የቀድሞው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ እና ዲፕሎማት አምባሳደር የነነበሩት ተሾመ ቶጋ ኮሚሽኑን እንዲመሩ የተሾሙት ባለፈው ዓመት ጥር 2015 ዓ.ም. ነበር።

አምባሳደር ተሾመ ያለፈውን አንድ ዓመት የቀድሞ ተዋጊዎችን መልሶ ለማደራጀት የሚያስፈልገውን ገንዘብ ከለጋሽ አካላት ለማሰባሰብ ጥረት ሲያደርጉ ነበር።

ከእነዚህ ጥረቶች መካከል በቅርቡ የአውሮፓ ኅብረት ተዋጊዎችን ለመበተን እና መልሶ ለማቋቋም ማስፈጸሚያ 16 ሚሊዮን ዩሮ መለገሱ ተገልጿል። ከኅብረቱ በተጨማሪ አምባሳደር ተሾመ ደጅ የጠኑባቸው ሌሎች ለጋሽ አካላትም የገነዘብ ድጋፎችን አድርገዋል።

ነገር ግን እነዚህ ድጋፎች ለፕሮግራሙ ማስፈጸሚያ ያስፈልጋል ከተባለው ገንዘብ አንጻር እዚህ ግባ የሚባል እንዳልሆነ ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ወገኖች ይገልጻሉ።

በሰባት ክልሎች የሚገኙ 371,971 የቀድሞ ተዋጊዎችን መልሶ ለማቋቋም ከ760 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር በላይ እንደሚያስፈልግ ኮሚሽኑ ከ20 ቀናት በፊት አስታውቆ ነበር።

ኮሚሽኑ በመጀመሪያው ዙር 75 ሺህ የቀድሞ ተዋጊዎችን ከትግራይ ክልል መልሶ እንደሚያቋቁምም ገልጿል።

ባለፈው ዓመት ኅዳር ወር ላይ በሚኒስትሮች ምክር ቤት በወጣ ደንብ የተቋቋመው ብሔራዊ ተሃድሶ ኮሚሽን የተሰጠው የሥራ ዘመኑ ሊጠናቀቅ የቀረው ስምንት ወራት ብቻ ነው።

በማቋቋሚያ ደንቡ መሠረት የኮሚሽኑ የሥራ ጊዜ ሁለት ዓመት ሆኖ እንደ አስፈላጊነቱ በሚኒስትሮች ምክር ቤት ሊራዘም ይችላል።

ኮሚሽኑ የሥራ ጊዜው ሊጠናቀቅ ወራት ቢቀሩትም ፕሮግራሙን ከሦስት ወራት በኋላ በሰኔ 2016 ዓ.ም. እንደሚጀምር እና ለሁለት ዓመት እንደሚቆይ ኮሚሽኑ ይፋ አድርጎ ነበር።

አምባሳደር ተሾመ ከኃላፊነት የለቀቁት ኮሚሽኑ በዚህ አጣብቂኝ ውስጥ እያለ ነው።

ኮሚሽኑ የአምባሳደር ተሾመን መልቀቅ አስመልክቶ በፌስቡክ ገጹ እንዳጋራው “በግል ጉዳያቸዉ ምክንያት በኮሚሽነርነት ላለመቀጠል ያቀረቡት ጥያቄ ተቀባይነት በማግኘቱ ከመጋቢት 3 ጀምሮ ለቀዋል” ብሏል።

የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ የውጭ ፖሊስ አማካሪ ሚኒስትር ዲኤታ የሆኑት አቶ ተመስገን ጥላሁን ከትናንት ሐሙስ መጋቢት 13/2016 ዓ.ም. ጀምሮ ኮሚሽነር ሆነው መሾማቸውን ተቋሙ አስታውቋል።

አምባሳደር ተሾመ ወደ ዲፕሎማሲው ዘርፍ ከተቀላቀሉ በኋላ በበቤልጂየም እና ቻይና የኢትዮጵያ አምባሳደር ሆነው አገልግለዋል።

ከ1997 እስከ 2002 ዓ.ም. ድረስም የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባኤ ነበሩ። ከዚህ በተጨማሪም የወጣቶች፣ ባህል እና ስፖርት እንዲሁም የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ሚኒስትር ሆነው ሰርተዋል።

አዲሱ ተሿሚ አቶ ተመስገን በበኩላቸው በአምቦ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካል ሳይንስ እና ዓለም አቀፍ ግንኙነት መምህር ነበሩ። በሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ከዓለም አቀፍ ግንኙነት ዳይሬክተርነት እስክ አማካሪነትም ሰርተዋል።

አቶ ተመስገን ለአምስት ዓመታት ያህል የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽንን በምክትልነት መርተዋል። የብሔራዊ ተሃድሶ ኮሚሽን ኮሚሽነር ሆነው እስከ ተሾሙበት ድረስም በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት የጠቅላይ ሚኒስትሩ የውጭ ፖሊሲ አማካሪ ሆነው እየሰሩ ነበር።

አዲሱ ተሿሚ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በፖሊታክ ሳይንስ እና ዓለም አቀፍ ግንኙነት የመጀመሪያ ዲግሪ በዓለም አቀፍ ግንኙነት ደግሞ ሁለተኛ ዲግሪ አላቸው።

ከዚህ በተጨማሪም የብሔራዊ ተሃድሶ ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር በነበሩት ዶ/ር አትንኩት መዝገበ ምትክ ደግሞ አቶ ተስፋዓለም ይህደጎ ተተክተዋል።

በኮሚሽኑ ማቋቋሚያ ደንብ መሠረት የተሃድሶ ኮሚሽኑ ዋና ኮሚሽነር እና ምክትሎችን የሚሾሙት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ናቸው።

selegna

By selegna

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *