የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ባጋጠመው የሲስተም ችግር ወቅት ገንዘብ የወሰዱ ወይም ያስተላለፉ ግለሰቦች እስከ መጪው ቅዳሜ መጋቢት 14/ 2016 ዓ.ም. ድረስ ካልመለሱ ፎቷቸውን እና ማንነታቸውን በመገናኛ ብዙኃን ይፋ እንደሚያደርግ አስታወቀ።

ባንኩ ገንዘቡን ተመላሽ በማያደርጉ ሰዎች ላይ በሕጋዊ ሂደቱ ተገቢ ውሳኔ እስኪገኝ ድረስ ፎቶግራፋቸውን እና ዝርዝር ማንነታቸውን የሚገልጹ መረጃዎች “ባንኩ በመረጠው የብዙኃን መገናኛ መንገድ ለሕዝብ ይፋ አድርጋለሁ” ሲል አሳስቧል።

ገንዘብ የወሰዱ ወይም ወደተለያዩ ሂሳቦች ያስተላለፉ ግለሰቦች በአቅራቢያቸው ወደሚገኙ የባንኩ ቅርንጫፎች በመቅረብ እንዲመልሱም የመጨረሻ ጥሪውንው ዛሬ ሐሙስ መጋቢት 12/2016 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ አስተላልፏል።

ነገር ግን ይህ ሳይሆን ገንዘቡን በተቀመጠው ጊዜ ገደብ ተመላሽ የማያደርጉ ግለሰቦች ላይ የተለያዩ እርምጃዎችን እወስዳለሁ ሲል አስጠንቅቋል።

የሚወስዳቸው እርምጃዎች ደረጃ በደረጃ እና በተከታታይ ጠንከር ያሉ እንደሆኑ ባንኩ ገልጾ፣ ለሕግ አካላት ማሳወቅ አንዱ እንደሚሆንም ገልጿል።

“ከሕግ አካላት ጋር በመተባበር የግለሰቦችን ስም ዝርዝር በየቅርንጫፎች እና እንደሁኔታው ግለሰቦቹ ሊታወቁ በሚችሉበት አካባቢ ይፋ በማድረግ ቀጣይ ሕጋዊ እርምጃዎችን” እንደሚከተሉ አስታውቋል።

በተጨማሪም “ከፍትህ አካላት እና ጉዳዩ ከሚመለከታቸው ተቋማት ጋር በመተባበር ተገቢውን የወንጀል፣ የፍትሐ ብሔር እንዲሁም አስተዳደራዊ እርምጃዎች እንዲወሰዱ እንደሚያደርግም” አሳስቧል።

የባንኩ ፕሬዝዳንት አቤ ሳኖ ረቡዕ ዕለት ለቢቢሲ ኒውስ ዴይ የራሳቸው ያልሆነን ገንዘብ የወሰዱ ደንበኞች እስከ ሳምንቱ መጨረሻ ድረስ ካልመለሱ ማንነታቸውን ለፖሊስ እንደሚያሳውቁ ተናግረው ነበር።

“በዲጂታል ነው ዝውውር የፈጸሙት። ደንበኞቻችን ስለሆኑ እናውቃቸዋለን። የፈጸሙት ተግባር በሕግ ያስጠይቃቸዋል። ለፖሊስ ማንነታቸውን እናሳውቃለን” ብለዋል።

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከገንዘብ ዝውውር ሥርዓቱ ማሻሻያ ሂደት ጋር በተያያዘ አርብ መጋቢት 6/2016 ዓ.ም. ምሽት ችግር ባጋጠመው ወቅት በርካታ ደንበኞች በሂሳባቸው ካለው ገንዘብ በላይ ዝውውር ማድረጋቸው ይፋ መደረጉ ይታወሳል።

የባንኩ ፕሬዝዳንት እንደሚሉት ከሆነ አብዛኞቹ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች የሆኑ ደንበኞች የተከሰተው ችግር ሲያጋጥም ባንኩ የሳይበር ጥቃት የደረሰበት መስሏቸው ገንዘብ ቢያዘዋውሩ ማንነታቸው የሚታወቅ አልመሰላቸውም ነበር።

አቶ አቤ “አሁን የፈጸሙት የገንዘብ ዝውውር በመታወቁ የወሰዱትን ገንዘብ በራሳቸው እየመለሱ ያሉ አሉ” ብለዋል።

በተፈጠረው ችግር ወቅት የማይገባቸውን ገንዘብ የወሰዱ ደንበኞቹ እስከ ሳምንቱ መጨረሻ ድረስ እንዲመልሱ የጠየቁት አቤ ሳኖ፤ ይህ ካልሆነ ግን ክስ ተመስርቶ ግለሰቦቹን ማንነት ለፖሊስ አሳልፎ እንደሚሰጥ አስጠንቅቀዋል።

ማንነታቸውን ለፖሊስ አሳልፋችሁ መስጠታችሁ ከደንበኞቻችሁ ጋር ያላችሁን ግንኙነት አያበላሽባችሁም ወይ ተብለው የተጠየቁት አቤ ሳኖ፤ “ከሌቦች ጋር ስለምን ዓይነት ግንኙነት ነው የምናወራው?” ብለው ጠይቀው፤ “በሂሳባቸው የሌላቸውን ገንዘብ ነው የወሰዱት። የራሳቸው ያልሆነን ገንዘብ እንደወሰዱ በጣም እርግጠኛ ነን” ሲሉ መልሰዋል።

ንግድ ባንክ ምን ያክል ገንዘብ ተወሰደበት?

ባንኩ አርብ መጋቢት 6/2016 ዓ.ም. ምሽት ላይ የሲስተም ችግር በገጠመው ወቅት የተወሰደበት ገንዘብ 2.4 ቢሊዮን ብር (40 ሚሊዮን ዶላር) መሆኑን አሶሺየትድ ፕሬስ (ኤፒ) ዘግቦ ነበር።

ባንኩ የተወሰደበትን ትክክለኛ የገንዘብ መጠን በቢቢሲ የተጠየቁት ፕሬዝዳንቱ የኦዲት ምርመራው ባለመጠናቀቁ የተወሰደውን ገንዘብ መጠን አሁን ላይ አይታወቀም ብለዋል።

“ገና ኦዲት እየተደረገ ነው። ዝውውሩ ውስብስብ ነው። ጤናማ የሆነ ዝውውር የፈጸሙ እንዳሉ ሁሉ፤ የሌላቸውን ገንዘብ ያወጡም አሉ። ስለዚህ ማጣራት ይጠይቃል። ይህ ደግሞ ጊዜ ይፈልጋል። ምናልባት በዚህ ሳምንት መጨረሻ እንጭርሳለን ብለን እንጠብቃለን” ብለዋል።

የባንኩ ፕሬዝዳንት ጨምረው እንደተናገሩት የሲስተም ብልሽት በደረሰ ወቅት 10 ሺህ የሚሆኑ ግለሰቦች የገንዘብ ዝውውር ማድረጋቸውን ተናግረዋል።

አቤ ሳኖ ሰኞ ዕለት ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ አርብ ሌሊት ከ490 ሺህ በላይ “ጤናማ እና ጤናማ ያልሆኑ” የገንዘብ ዝውውሮች መከናወናቸውን ተናግረው ነበር።

ከገንዘብ መክፈያ ማሽኖች በጥሬ ወጪ ከተደረገው በላይ ትልቁን ድርሻ የሚይዘው ከአንድ ሂሳብ ወደ ሌላ የተደረገ ዝውውር መሆኑን መሆኑንም አቤ ጨምረው ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ባሉት ደንበኞች፣ ቅርንጫፎች እና ሃብት መጠን በአገሪቱ ካሉ ባንኮች ጋር ሲነጻጸር ትልቁ ነው።   ዘገባው የቢቢሲ ነው፡፡

selegna

By selegna

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *