በኢትዮጵያ መንግሥት የፀጥታ ኃይሎች ጥቃት እንደተፈጸመባቸው የተዘገበው የአፍሪካ ልማት ባንክ የምሥራቅ አፍሪካ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር አብዱል ካማራ፤ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ጋር ተገናኝተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ፤ ዛሬ የካቲት 29/2016 ዓ.ም. ጠዋት ከአፍሪካ ልማት ባንክ ኃላፊው ጋር ተገናኝተው መወያየታቸውን ያስታወቁት በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው ላይ ከፎቶዎች ጋር አያይዘው በለጠፉት መልዕክት ነው።

በመልዕክታቸው፤ “ኢትዮጵያ ከአፍሪካ ልማት ባንክ ጋር ያላት አጋርነት ውጤታማ ሆኖ ቀጥሏል” ያሉት ዐቢይ፤ ከዶ/ር አብዱል ጋር የነበራቸው ውይይት ባንኩ “በኢትዮጵያ በሚያካሂዳቸው ፕሮጀክቶች” ላይ ያተኮረ እንደሆነ ገልጸዋል።

በተጨማሪም ጠቅላይ ሚኒስትሩ የአፍሪካ ልማት ባንክ ፕሬዝዳንት ዶ/ር አኪንውሚ አዴሲና “የኦባፌሚ አዎሎው የአመራር ሽልማትን” ማግኘታቸውን በመጥቀስ የ“እንኳን ደስ ያለህ” መልክዕታቸውን አስተላልፈዋል።

በዛሬ ጠዋቱ ውይይት ላይ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የማክሮ ኢኮኖሚ አማካሪ አምባሳደር ግርማ ብሩ እንደተሳተፉ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በገጻቸው ላይ በለጠፏቸው ፎቶዎች ላይ ታይቷል።

በተጨማሪም በጠቅላይ ሚኒስትር ልዩ ጽህፈት ቤት ኃላፊ ሳንዶካን ደበበ አቅራቢነት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ለዶ/ር አብዱል የአንገት ሀብል ሲያበረክቱላቸው የሚያሳይ ሌላ ፎቶ ተለጥፏል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ለዶ/ር አብዱል ያጠቁላቸው ሀብል የኢትዮጵያ ካርታ የተቀረጸበት ነው።

ይህ ሀብል የተበረከተላቸው የአፍሪካ ልማት ባንክ የምሥራቅ አፍሪካ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር አብዱል፤ ባለፈው ኅዳር ወር ላይ በኢትዮጵያ መንግሥት የፀጥታ ኃይሎች እስር እና አካላዊ ጥቃት ከደረሰባቸው የባንኩ ሠራተኞች አንዱ እንደሆኑ የኬንያው “ዴይሊ ኔሽን” ጋዜጣ ዘግቦ ነበር። ዶ/ር አብዱል የደረሰባቸውን ጥቃት የሚያሳይ ፎቶም በማኅበራዊ ትስስር ገጾች ሲዘዋወር ነበር።

የባንኩ ሠራተኞቹ ላይ በተፈጸመው “ከሕግ ውጪ” የሆነ እስር እና አካላዊ ጥቃት ምክንያት ዓለም ዓቀፍ ሠራተኞቹን ከኢትዮጵያ አስወጥቶ እንደነበር ይታወሳል።

ነገር ግን ባለፈው ጥር ወር ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በኢትዮጵያ መንግሥት ስም በባንኩ ሠራተኞች ላይ ለደረሰው አካላዊ ጥቃት እና የዲፕሎማሲያዊ መብት ጥሰት “መደበኛ ይቅርታ” በማቅረባቸው ሠራተኞቹን ወደ ኢትዮጵያ ለመመለስ መወሰኑን አስታውቋል     ዘገባው የቢቢሲ ነው፡፡

selegna

By selegna

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *