የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች በሀገር ውስጥ የተመረቱ ምርቶችን ቅድሚያ ሰጥተው እንዲገዙ ውሳኔ መተላለፉን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ተመስገን ጥሩነህ ተናገሩ።

ውሳኔው የተላለፈው የሚኒስትሮች ምክር ቤት ለሁለት ቀናት ባካሄደው የ2016 ዓ.ም. የሁለተኛው ሩብ ዓመት የሥራ አፈጻጸም ግምገማ ላይ ነው።

ማክሰኞ የካቲት 26/2016 ዓ.ም. መካሄድ በጀመረው ግምገማ በሦስት ዘርፎች ሪፖርቶች መቅረባቸውን አቶ ተመስገን ጥሩነህ ከብሔራዊ የቴሌቪዥን ጣቢያ ጋር በነበራቸው ቆይታ ገልጸዋል።

የሚኒስትር መሥሪያ ቤቶቹ ሪፖርቶች የቀረቡት በአስተዳደር እና ፍትሕ፣ በማኅበራዊ እና በኢኮኖሚ ዘርፎች ተከፋፍለው ነው።

የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪን በተመለከተ የገቢ ምርቶችን መተካት እና ኤክስፖርትን ማስፋት እንደሚገባ በግምገማው ላይ መነሳቱን አቶ ተመስገን ለኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን ተናግረዋል።

ከሁለት ዓመት በፊት በተጀመረው “ኢትዮጵያ ታምርት” ንቅናቄ “በርካታ ምርቶች” መመረታቸውን የጠቆሙት አቶ ተመስገን፤ “የሀገር ውስጥ ምርትን በሀገር ውስጥ የመጠቀም ዝንባሌው እና ተነሳሽነቱ ይቀራል” ብለዋል።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ አክለውም “በርካታ ምርቶች እየተመረቱ እንደሆነ ተገምግሟል ነገር ግን እነዚህን ምርቶች መጠቀም ላይ ያለው ፍላጎትም፤ አሠራርም ክፍተት አለበት። ይሄን ፈጥነን ማሻሻል አለብን ተብሏል፤ ውሳኔም ተሰጥቶበታል” ሲሉ ተናግረዋል።

አቶ ተመስገን ተላለፈ ያሉትን ውሳኔ ሲያስረዱ፤ “የትኛውም የመንግሥት መሥሪያ ቤት ኢትዮጵያ ያመረተችውን ምርት ቀድሞ መግዛት አለበት። ይሄን ካጣ ብቻ ወደ ውጭ እና ወደ ዓለም ገበያ መሄድ አለበት” ብለዋል።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ “የመንግሥት መሥሪያ ቤቶችን ጭምር ሕግ አሻሽለንም ቢሆን በቅድሚያ የሀገር ውስጥ ምርት እንዲገዙ [እና] እንዲጠቀሙ እንደ መንግሥት ይሄንን ማበረታታት አለብን” ሲሉም አክለዋል።

ይህ ውሳኔ የተላለፈው በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ መሆኑን የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ አቶ መላኩ አለበል ለኢቢሲ ገልጸዋል።

አቶ መላኩ “ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትሩ አቅጣጫ የተሰጠው በሀገር ውስጥ ያሉ ምርቶች ቅድሚያ ተሰጥቷቸው ግን በውድድር ለመንግሥት ግዢ መቅረብ አለባቸው የሚለው በልዩ ትኩረት አቅጣጫ የተሰጠበት እና የተገመገመ [ጉዳይ] ነው” ብለዋል።

ሌሎች ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶች ፍላጎታቸውን ለኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ማቅረብ እንዳለባቸውም አቶ ተመስገን ጠቁመዋል።

አቶ ተመስገን “[አንድ መስሪያ ቤት] ይሄንን ማስመረት እፈልጋለሁ የሚል ሃሳብ ካለው ያንን ሃሳብ ለኢንዱስትሪ ሚኒስቴር በቅድሚያ ማቅረብ አለበት እንጂ በቀጥታ ከዓለም ገበያ ገዝቶ ወደ ማሟላት መሄድ እንደሌለበት አቅጣጫ ተቀምጧል” ሲሉ ውሳኔውን በዝርዝር አብራርተዋል።

የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ በበኩላቸው ውሳኔው፤ “ለአምራች ኢንዱስትሪዎች ተጨማሪ ገበያ እንዲያገኙ በማድረግ በኩል ከፍተኛ አስተዋጽዖ” እንደሚያበረክት ተናግረዋል።

የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ አስተዳደር የገቢ ዕቃዎችን በሀገር ውስጥ ምርት ለመተካት እንደሚሰራ የመንግሥት ባለሥልጣናት በተደጋጋሚ ሲናገሩ ይደመጣሉ።

ነገር ግን አሁንም በወጪ እና በገቢ ንግድ መካከል ያለው አለመመጣጠ ከፍተኛ ነው። ባለፈው የ2015 በጀት ዓመት ከወጪ ንግድ ኢትዮጵያ ያገኘችው 3.64 ቢሊዮን የአሜሪካን ዶላር ሲሆን ወደ ሀገር ውስጥ ለገቡ ሸቀጦች ደግሞ 15 ቢሊዮን ዶላር ወጪ አድርጋለች።    ዘገባው የቢቢሲ ነው፡፡

selegna

By selegna

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *