አግአዚ* በሚኖርበት አካባቢ ሕብረተሰቡ የሚገለገልባቸው የግብርና ዕቃዎችን ያዘጋጃል።

የስምንት ልጆች አባት የሆነው ይህ ባለ እጅ፣ የዶለዶመ ማረሻ የሚስል፣ እናቶች እና ሴት ልጆች የሚያጌጡበት የወርቅ እና የብር ጌጣጌጥ የሚሠራ፣ አብያተ ክርስቲያናት እና ካህናት የሚገለገሉባቸው ቁሶች የሚሠራ ባለሙያ ነው።

ይህ የእጅ ሙያው ግን ነቀፋን፣ መገለል እና መገፋትን እንጂ ምስጋናን አላስገኘለትም።

አግአዚ አንድ ቀን አራት ወጣቶች መንገድ ላይ ይዘውት “ቡዳ ነህ” በማለት እንዳንገላቱት፣ እንደደበደቡት እና ንብረቱን እንደዘረፉት ያስታውሳል።

“አራት ወጣቶች ‘እናቴን እና እህቴን በልተሃቸዋል’ በማለት ደብድበው ሞቷል ብለው ጥለውኝ የሄዱበት ቀን አለ” ይላል።

ያኔ ልብሱን፣ ሞባይሉን እና ኪሱ ውስጥ የነበረ 15 ሺህ ብር እንደወሰዱበት እና ከ170,000 ብር በላይ እንደጠፋበት ይናገራል።

እርሱ ብቻ ሳይሆን ልጆቹም ቢሆኑ በሚማሩበት ትምህርት ቤት የሚቀርባቸው ስላጡ ቤታቸውን ጥለው በመሄድ ሰው ቤት ተጠግተው እየኖሩ ነው።

የእሱ ዓይነት የመገለል ዕጣ የደረሳቸው ልጆቹ “አሁን ትምህርት አያውቁም” ይላል።

“ሕብረተሰቡ እነዚህ ቀጥቅጠው የሚያድሩትን የቡዳ ልጆች ናቸው በሚል አብረዋቸውን መቀመጥ አይደልጉም። መምህሩም ‘እናንተ ምንድን ናችሁ?’ ሲል ያሳቅቃቸዋል።”

አግአዚ የደረሰበትን እንግልት እና ስም ማጥፋት ሸሽቶ ከትውልድ አገሩ ተፈናቅሎ፣ አሁን ቤቱ ፈርሶ መሬቱን ትቶ፣ ወልዶ የሳመበትን ቀየውን ጥሎ በመሰደድ በረሃብ እና በችግር እየኖረ መሆኑን ይናገራል።

አቶ አግአዚ ከ2011 ዓ.ም. ጀምሮ በሚኖርበት እንደርታ ወረዳ ‘ቡዳ ነህ’ በሚል ተደጋጋሚ ክስ ተከሶ፣ እሱም ለፖሊስ ‘ሰው በልተሃል እየተባልኩ በደል እየተፈጸመብኝ ነው’ ሲል አመልክቶ ያውቃል።

ያገኘው መልስ ግን “ባህላዊ አስተሳሰብ ነው” የሚል ብቻ ነው።

ይህ ታሪክ የእርሱ ብቻ አለመሆኑን ሲናገርም “በዚህም ምክንያት በግፍ የተገደሉ፣ አስከሬናቸው ያልተገኘ ብዙ ሰዎች” መኖራቸውን በመጥቀስ ነው።

“. . . እግዚአብሔር ሁላችንን እኩል ፈጠረን እያሉ የሚሰብኩት ቄስ ሳይቀር ባለቤቴን ‘በላህብኝ’ ብለው ‘ልማድህን አቁም’ ብለው አግልለውኛል። በእዚህ ምክንያትም ከምወዳት የእናቴ ታቦት ተገልያለሁ” በማለት ጫናው ማኅበራዊ ሕይወቱንም እንዳመሳቀለው ያስረዳል።

‘ቡዳ ተብለው ሐይቅ ውስጥ ያሰመጧቸው ልጆች’

የትግራይ ዕደ-ጥበብ ባለሙያዎች ማኅበር ሙያተኞቹ በክልሉ በተለያዩ አካባቢዎች እየደረሰባቸው ያለው ግፍ እየተባባሰ መምጣቱን ይገልጻል።

ይህም ከመፈናቀል፣ ስም ከማጥፋት እና ከማስፈራራት እስከ ግድያ ይደርሳል።

ማኅበሩ ያካሄደው ጥናት እንደሚያመለክተው በሕንጣሎ ወረዳ ውስጥ መፈናቀሉ ብሶ ይታያል። ባለፉት አራት ዓመታትም ሁኔታው በከፍተኛ ደረጃ ጨምሯል።

እነዚህ ሰዎች በብዛት የሚሰደዱት እንደርታ ወረዳ አካባቢ ወደ የምትገኘው ምላዛት ከተማ ሲሆን፣ ወደ መቀለ እና ሌሎች አካባቢዎችም እንደሚሄዱ ጥናቱ ያመለክታል።

የትግራይ ዕደ ጥበብ ባለሙያዎች ማኅበር ሊቀመንበር የሆኑት አቶ በርሀ አብርሃ የዕደ ጥበብ ባለሙያዎች ብረት ቀጥቅጠው ከማረሻ ጀምረው የዕለት ከዕለት መገልገያዎችን እንዱሁም ወርቅ እና የመሳሰሉትን በማንጠር ጌጦችን እንደሚሠሩ ይጠቅሳሉ።

“ነገር ግን ‘ባለ እጅ ነው። ወደ አራዊትነት ይቀየራል። ቡዳ ነው’ እየተባለ ሰው እየተገደለ ነው፤ ከቤተ ክህነት እና ከማኅበራዊ ሕይወት እየተገለለ ነው” ሲሉ የሚደርስባቸውን ይገልጻሉ።

አክለውም በተለያዩ መስኮች እንግልት ቢደርስባቸውም መንግሥት ትኩረት ስላልሰጠው ሰው እየሞተ ነው። “በዚህ ሳቢያም ነገሮች እየተድበሰበሱ ‘ዝም በሉ’ እየተባለ ፍትህ ሳያገኝ ቆይቷል” ይላሉ አቶ በርሀ።

ቢቢሲ አቶ በርሀን ደውሎ በሚያነጋግርበት ወቅት በሕንጣሎ ወረዳ ሕንጣሎ መንደር ውስጥ ‘ቡዳ ናችሁ’ በሚል ጥቃት የደረሰባቸውን ሰዎች ጉዳይ ይዞ ፍርድ ቤት ቀርቦ ነበር።

ብዙ የእጅ ጥበብ ባለሙያዎች በሚደርስባቸው በደል እና መገለል እንዲሁም ሞትን ለማምለጥ ሲሉ ሙያቸውን ትተው በሌላ ዘርፍ ለመሰማራት ሲገደዱ፣ ሌሎች ደግሞ ማንነታቸውን ደብቀው እየኖሩ ናቸው።

የሚደርስባቸው ጥቃትም እድሜ እና ጾታን እንደማይለይ በምሳሌ ያስረዳሉ።

“ለምሳሌ እንትጮ ውስጥ ከፍተኛ ግፍ ተፈጽሞባት በህክምና ላይ የምትገኝ አንዲት ሴት አለች። በሕንጣሎ ወረዳ ህጻናት ቡዳ ናችሁ ተብለው ሐይቅ ውስጥ ተከተው ተገድለዋል። ሕብረተሰቡ ይህን እየፈጸመ ያለው ‘ወንድሜን/እህቴን በልተዋል’ በሚል ነው።”

ግን እንደሚባለው እነዚህ የዕደ-ጥበብ ሙያተኞች ሌሎች ሰዎች ላይ ጉዳት ሊያደርስ የሚችል የተለየ ኃይል አላቸው ወይ? ቢቢሲ አቶ በርሀን የጠየቀውው ጥያቄ ነው።

“በፍፁም! ሁሉም ሰው እኩል ነው፤ የእጅ ጥበብ ባለሙያዎች ደክመው የሚበሉ ስለሆኑ ቅናት ነው። ወደ አውሬነት የተቀየረ ሰው አምጣልኝ ብትለው አያመጣልህም እንዲሁ ይባላል ነው የሚባለው” በማለት አባባሎቹ እውነት እንዳልሆኑ ያስረዳሉ።

የትግራይ የእጅ ባለሙያዎች ማኅበር እየተፈጸመ ላለው ጥቃት የኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን አማኞችን ዋና ተጠያቂ ያደርጋል።

በአንዳንድ የጸበል ቦታዎች የሚያጠምቁ የሃይማኖት መሪዎች “እከሌ የሚባል ባለ እጅ ይዞሃል፣ እከሌ የሚባል ቡዳ በልቶሻል” እያሉ የእጅ ጥበብ ባለሙያዎችን የጥቃት እና የሞት ሰለባ እንዲሆኑ እያደረጉ ናቸው ሲል ይከሳል።

“ይህንን ጥሰት ከሚፈጽሙት ሰዎች ውስጥ 99% የሚሆኑት ክርስቲያን ነን የሚሉ ናቸው” ይላሉ አቶ በርሀ።

በሰሜን ምዕራብ ዞን የሽሬ እንዳሥላሴ ሀገረ ስብከት ዋና ሥራ አስኪያጅ እና የመንበረ ሰላማ ከሳቴ ብርሃን ትግራይ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስትያን ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባል የሆኑት ንቡረ እድ ተስፋይ ተወልደ በዕደ ጥበበኞች ላይ እየደረሰ ያለው ስም ማጥፋት ተቀባይነት የለውም ይላሉ።

በማኅበረሰቡ ውስጥ “ሰው ይበላሉ፥ ሰው ይገድላሉ” የሚለው አባባል ሃይማኖታዊ መሠረት እንደሌለውም ያብራራሉ።

“እኛ እንደ ማኅበረሰብ የምንሰማቸው ለዘመናት ሲነገሩ የቆዩ አባባሎች አሉ። ይሁን እንጂ ‘ቀን ሰው ሆነው ሌሊት. . . ጅብ ሆነው ተመልሰው ሰው ይሆናሉ’ የሚለውን አባባል የሚደግፍ መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ አንዳች ነገር የለም።”

‘ቡዳነት’ ምንድን ነው?

አንድን ነገር ላይ አተኩሮ በመመልከት የሰውን ውስጣዊ መንፈስ ማየት ይቻላል በሚል እምነት አተኩሮ የሚያየውን ሰው ‘ቡዳ! እንዲህ አድርገህ አትየኝ’ የሚል ሰው ብዙ ነው።

የሥነ ልቦና ባለሙያዎች የቡዳን በተመለከተ ያለው አመለካከት በሰዎች አእምሮ ውስጥ የስሜት መቃወስን የሚያመለክት እንደሆነ ይገልጻሉ።

የሆነ ሰው ይቀናብኛል የሚል ስጋት፣ ፍራቻና ጭንቀት ያለው ሰው የሚፈጥረው የስሜት መቃወስ እንደሆነም ያስረዳሉ።

አንድ ሰው በድንገት ችግር ውስጥ ሲገባ፣ ይቀኑብኛል ብሎ በሚያስባቸው ሰዎች ያሳብባል። ስለዚህ ‘ቡዳ’ ብለው በሚጠሯቸው ሰዎች ላይ የሚደርሰው ጥቃት በሌላ ሰው ላይ የማሳበብ መንገድ እንደሆነ ይጠቁማሉ።

የፎክሎር እና የአንትሮፖሎጂ ምሁራንም ‘ቡዳን’ በተመለከተ ያለው እሳቤ የማኅበራዊ ልማዶች አካል ነው ይላሉ።

በኢትዮጵያ እና በኤርትራ ማኅበረሰብ ውስጥ፣ ‘ቡዳነት’ ከቤተሰብ ወደ ቤተሰብ በዘር ይተላለፋል የሚል ሰፊ እምነት አለ።

ይህ እምነት በስፋት ከመዘርጋቱ የተነሳ ሕብረተሰቡ ከቡዳ ይከላከላሉ ወይም ይፈውሳሉ የሚላቸውን እንደ እጽዋት፣ ስራስር፣ ነጭ ሽንኩርት፣ ጤና አዳምና የጅብ ቆዳ የመሳሰሉ ነገሮችን ይታጠናል፤ ከቤቱ ደጃፍ ላይም ይሰቅላል።

የአንትሮፖሎጂ ተመራማሪ የሆኑት አድማሱ አበበ (ዶ/ር) ‘ቡዳነት’ ከባህል፣ ከማኅበራዊ፣ ከሃይማኖት እና ከሙያ ጋር ትስስሮች ቢኖሩትም “ሰው ሰውን ይበላል” የሚለው ሀሳብ ሳይንሳዊ ሥነ-አመንክዮ የለውም ይላሉ።

“እነዚህ ሰዎች በድንገት ሲያዩህ ልጆችህ ወይም ከብቶችህ ይሞታሉ፥ ሰው ይበላሉ የሚል ባህል ውስጥ ስር የሰደደ አስተሳሰብ አለ። አንድ ሰው በድንገት በሌላ በሽታ ቢሞት እንኳ እነዚህ ‘ቡዳዎች’ የሚባሉት በሚኖሩበት አካባቢ አልፎ ከነበረ ቡዳ በልቶታል ይባላል።

“በዚህም ቡዳ ነው የተባለውን ሰው እየመቱ የዶሮ ኩስ እና ጎማ እያጠኑ አቅላቸውን አስተው ያስለፈልፏቸዋል። ከዚያምም በጭንቀት ቡዳ የተባለውን ስም ስለሚጠራ የተጠራው ሰው ሰለባ ይሆናል” ሁኔታውን ያስረዳሉ።

ሌሎች መንስኤዎች እና ውጤቶች

በዚህ ዘርፍ የሚሳተፉት አብዛኞቹ ወርቅ አንጣሪዎች፣ ሸክላ ሠሪዎች፣ የቆዳ እና የእጅ ባለሞያዎች መሆናቸውን አንትሮፖሎጂስት አድማሱ አበበ (ዶ/ር) ይናገራሉ።

በእነዚህ ሙያተኞች ላይ የሚደርሰው መገለል ከማኅበራዊ ክፍፍል፣ ከኢኮኖሚ እና ከባህል ጋር የተሳሰረ እንደሆነም ያስረዳሉ።

እነዚህ አንጥረኛ፣ ባለ እጅ ፣ ቡዳ . . . የሚል የተለያየ ስም የሚሰጣቸው የእጅ ባለሞያዎች ከሚያጋጥሟቸው ችግሮች መካከል አንዱ ሀብት ማፍራት ሲሆን፣ አብዛኞቹ ለም ባልሆኑ አካባቢዎች የተበታተነ አሰፋፈር እንዳላቸውም ጨምረው ይገልጻሉ።

“እነሱ የሚኖሩት ጫካ ውስጥ ወይም ለእርሻ የማይመች ወይም ገደላማ በሆኑ አካባቢዎች ነው። ይህም አንድ ላይ ተባብረው የሚገጥማቸውን ችግር እንዳይመክቱ ያግዳቸዋል። መሬት ስለሌላቸው አያርሱም። ስለዚህ የሚተዳደሩት በዕደ ጥበብ ሥራቸው ብቻ ነው። ስለዚህ በገበያ፣ በትምህርት እና በሌሎች ዘርፎች እኩል ተጠቃሚ አይሆኑም” ይላሉ።

ቀደም ባሉት ጊዜያት ሕብረተሰቡ ይጠቀምባቸው የነበሩት የእነዚህ የእጅ ባለሙያዎች ምርቶች በዘመናዊ ቁሳቁሶች እየተተኩ በመሆናቸው በአሁኑ ጊዜ ለከፍተኛ ኢኮኖሚያዊ መገለል ተዳርገዋል።

ሌላው ማኅበራዊ መገለል ከሌላው የሕብረተሰብ አካል ጋር ጋብቻ መመሥረት አለመቻላቸው ከአካባቢያቸው ሕዝብ ጋር ያላቸውን ግንኙነት እንዳዳከመው ምሁሩ ያስረዳሉ።

“አስከሬናቸው ከሌሎች ጋር አብሮ የማይቀበርባቸው አጋጣሚዎች ሳይቀር አሉ። በእቁብ ያላቸው ተሳትፎም በጣም ውስን በመሆኑ መገለሉን ከፍተኛ ያደርገዋል።”

በሌላ በኩል ከሃይማኖት ጋር ይተሳሰራል የሚለው አድማሱ ለእነዚህ የእጅ ባለሞያዎች የተሰጣቸው የተሳሳተ አመለካከት እንዳለ ይጠቁማል። “ንጹህ አይደሉም፣ በሃይማኖት የተከለከሉ ምግቦችን ይመገባሉ ይባላሉ። ለምሳሌ ቆዳ የሚያለፉ በአለባበሳቸው ይጸየፏቸዋል።”

በመሆኑም በእነርሱ ላይ የሚደርሰው ጥቃት በባህላዊ እና በሃይማኖት ላይ የተመሠረተ አመለካከት በመሆኑ አንድ ቦታ ላይ አለመኖራቸው ለጥቃት ያጋልጣቸዋል ሲሉ ያስረዳሉ።

ምን ሊደረግ ይችላል?

ላለፉት 15 ዓመታት በትግራይ የዕደ-ጥበብ ባለሙያዎች ላይ የሚሰነዘረው ስም ማጥፋት እና ጥቃት ጎልቶ እየታየ ከፍተኛ መዘዝ እያስከተለ መሆኑን ከክልሉ የእጅ ባለሙያዎች ማኅበር ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

ሰዎች ለዓመታት ያፈሩት ንብረት እና ከብት ጥለው እየተፈናቀሉ መሆናቸው እንዳሳሰባቸው አቶ በርሀ ይናገራሉ።

በመሆኑም “መንግሥት ሕይወታቸውን እንዲመሩ እና ደኅንነታቸው እንዲጠበቅ ማድረግ አለበት፤ ነገር ግን የዜጎች ደኅንነት እየተጠበቀ አይደለም” ይላሉ።

ንቡረ እድ ተስፋዬም ኋላቀር እምነት በቤተ ክርስቲያን እና በማኅበረሰቡ ኑሮ ላይ ከፍተኛ ጉዳት እንዳደረሰ ያምናሉ።

“እምነታችንን አዳክመውታል። ብዙ ደም አፍስሷል። ደም በፈሰሰ ቁጥር ደግሞ ማኅበራዊ ግንኙነታችን እየተዳከመ እንደጠላት እንድንተያይ አድርጎናል። በጥበብ እንዳናድግም አድርጓል። የተለየ ማረሻ፣ ማጭድ፣ እህል መውቂያ መፍጠር’ኮ እንችል ነበር።”

በማንኛውም ጊዜ የፖለቲካ ለውጥ ሲመጣ ጥበቃ የሚሰጠው አካል ስለሚዳከም ቀድሞ ጥቃት የሚደርስባቸው እነዚህ የሕብረተሰብ ክፍሎች እንደሆኑ አንትሮፖሎጂስት አድማሱ አበበ ያስገነዝባሉ።

በትግራይ መንበረ ሰላማ በትግራይ የእጅ ባለሞያዎች ላይ እየደረሰ ያለውን መድሎ በማውገዝ ውሳኔ ማሳለፉን ንቡረ እድ ተስፋይ ተናግረዋል።

“ከሃይማኖት አንፃር ሲታይ ትክክል ስላልሆነ መንግሥት የፀጥታ ኃይሎችን እንዲያግዝ፣ ሰፊ የወንጌል ትምህርት እንዲሰጥ፣ እነርሱም ወደ ቀያቸው ተመልሰው በፈለጉበት በሰላም እንዲኖሩ፣ ለቤተ ክርስቲያን አገልግሎትም እንዳይከለከሉ ለማስተማር ደብዳቤ ለሁሉም አካል ተበትኗል።”

ይህ እስከሚሆን ግን አቶ አግአዚ ከሥራው እና ከኑሮው ርቆ፣ ልጆቹም ከቀያቸው እና ከትምህርት ርቀው የሚቆዩበት ቀናት እየተቆጠሩ ነው።

“ልጄን ወደ ትምህርት ቤት መላክ ስላለብኝ አንድ ጎረቤቴን እባክህ ልጄ ብለህ አስመዝግበው ብየው አስመዝግቦት አሁን ትምህርት ጀምሯል። ልጆቼ ደግሞ ተምረው የአስተሳሰብ ለውጥ ማምጣት የሚችሉ መሪዎች እንዲሆኑ እመኛለሁ” ሲል ያለውን የሩቅ ተስፋ ይገልጻል።       ዘገባው የቢቢሲ ነው፡፡

selegna

By selegna

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *