በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ሞጃ እና ወደራ ወረዳ ሰኞ የካቲት 11/2016 ዓ.ም በአንድ አይሱዙ የጭነት ተሽከርካሪ ላይ በተፈጸመ የድሮን ጥቃት በርካታ ሰዎች መገደላቸውን የዐይን እማኞች እና የአካባቢው ነዋሪዎች ለቢቢሲ ተናገሩ።

ከወረዳው ዋና ከተማ ሰላ ድንጋይ ወጣ ብላ ከምትገኝ ሳሲት ከተባለች አነስተኛ ከተማ የተነሳው ተሽከርካሪው ጋውና መውረጃ ልዩ ስሙ ፈላ መገንጠያ በተባለ አካባቢ ሲደርስ ጥቃቱ እንደተፈጸመበት አራት የቢቢሲ ምንጮች ተናግረዋል።

ስማቸው ለደኅንነታቸው ሲሉ እንዳይጠቀስ የጠየቁ የቢቢሲ ምንጮች በተሽከርካሪው ውስጥ ከ50 በላይ ተጓዦች እንደነበሩ ገምተዋል።

ተሽከርካሪው ተሳፋሪዎችን እያወረደ እያለ ጥቃቱ መፈጸሙን ለቢቢሲ የተናገሩ አንድ የዐይን እማኝ፤ ለክርስትና የወጡ 16 የቅርብ ዘመዶቻቸው መገደላቸውን ገልጸዋል።

“እኔ የማውቃቸው ብቻ የእኔ ቤተሰቦች የሆኑ የአባቴ ወገኖች እና የእናቴ ወገኖች ከ16 ሰው በላይ ሰዎች አልቀዋል… ” ሲሉ የሟቾችን ቁጥር “30 ይደርሳል” ብለዋል።

ጥቃቱ ከረፋዱ 5፡00 እስከ 6፡00 ባለው ጊዜ እንደደረሰ የተናገሩት የአካባቢው ነዋሪዎች ክስተቱን “እልቂት” ሲሉ ነው የገለጹት።

ከሟቾቹ ውስጥ አክስታቸው እና አጎታቸው እንደሚገኙበት የተናገሩ ሌላ የአካባቢው ነዋሪ በጥቃቱ “ሙሉ ቤተሰቦች” እንደተገደሉ ተናግረዋል።

አጠቃላይ የሟቾቹን ቁጥር “30 ይሆናሉ” ያሉ ምንጮች፤ በአያቱ እቅፍ ውስጥ ነበር የተባለው “ክርስትና የተነሳው ህጻን” ጉዳት ሳይደርስበት በሕይወት መትረፉንም ተናግረዋል።

ይህንም አንድ ሌላ የሟቾች ዘመድ ለቢቢሲ አረጋግጠዋል።

“እሱን [ህጻኑን] እግዚአብሔር አተረፈው፤ ምንም አልተነካም” በማለት እናት እና አባቱን ጨምሮ የህጻኑ ሙሉ ቤተሰብ በጥቃቱ መገደላቸውን ገልጸዋል።

በጥቃቱ የተገደሉ ሠዎችን ማንነት የሚጠቅሱ አንድ የኃይማኖት አባት ድምጽ እና ጥቁር ጭስ አይተው ጥቃቱ ወደ ተፈጸመበት ስፍራ ማቅናታቸውን ይናገራሉ።

“ለቅሶ በሆነ ጊዜ፣ ክርስትና በሆነ ጊዜ የዘመድ መኪና እየያዘ ይሄዳል” ሲሉ በአካባቢው ሠው በጭነት ተሽከርካሪ መጓዙ የተለመደ መሆኑን ጠቅሰው ተሽከርካሪው የክርስትና ተጓዦቹ የቤተሰብ ንብረት እንደሆነ ተናግረዋል።

በአካባቢው ሲደርሱም ከህጻናት እስከ አረጋዊያን አስከሬን ማየታቸውን ለቢቢሲ ገልጸዋል።

ጥቃቱ ባጋጠመበት ስፍራ ወዲያውኑ እንደደረሱ የሚናገሩት ሌላ እማኝ “ከፍተኛ አደጋ” ሲሉ ጥቃቱን ይገልጻሉ። በርካታ የቆሰሉ ሰዎች እንዳሉም ተናግረዋል።

የቆሰሉ ሰዎች “20 ይደርሳሉ” ያሉት የኃይማኖት አባቱ፤ ቁስለኞቹ ጋውና እና ሳሲት ጤና ጣቢያዎች መወሰዳቸውን ተናግረዋል።

ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈቀዱ አንድ የጋውና ጤና ጣቢያ ባለሙያ 18 የቆሰሉ ሰዎች ወደ ጤና ጣቢያው ለሕክምና እንደመጡ ለቢቢሲ አረጋግጠዋል። የተሽከርካሪውን ሹፌር ጨምሮ ሦስቱ ቁስለኞች ወዲያ ሕይወታቸው እንዳለፈም ባለሙያው ተናግረዋል።

“ሹፌሩን ጨምሮ እኛ ጋር ሲመጡ በጣም አስጊ ሁኔታ ውስጥ ነበሩ። ያው የተቻለንን ለማገዝ ሞከርን። ህጻናትም አሉ፤ ሹፌሩም አለ። እነሱ ወዲያው ነው ሕይወታቸው ያለፈው” ብለዋል።

ከ15ቱ ቁስለኞች ውስጥ አራቱ ለሪፈራል ሕክምና ወደ ደብረ ብርሃን መጓዛቸውን የተናገሩት ባለሙያው፤ ቀሪዎቹ በጤና ጣቢያው ሕክምና እየተከታተሉ መሆኑን ተናግረዋል።

ጥቃቱ የደረሰበት ስፍራ ላይ በመንግሥት ኃይሎች እና በፋኖ ታጣቂዎች መካከል ውጊያ እንዳልነበረ የአካባቢው ነዋሪዎች ተናግረዋል።

ሆኖም ከጥቃቱ በፊት ባሉ ቀናት ከሰሜን ሸዋ ዞን ዋና ከተማ ደብረ ብርሃን በ72 ኪሎ ሜትር.ሜ ርቀት ላይ በምትገኘው ሰላ ድንጋይ ከተማ የመንግሥት ኃይሎች እየገቡ ነበር ተብሏል።

በከተማዋ በሁለቱ ወገኖች መካከል ሰኞ ዕለት “ከባድ ውጊያ” እየተደረገ ነበር ያሉት ምንጮች፤ በአካባቢው የነበሩ የፋኖ ታጣቂዎች ከከተማ ወደ ገጠራማ አካባቢዎች መውጣታቸውን ገልጸዋል።

አንድ ነዋሪ የድሮኑ ጥቃቱ የደረሰበት አካባቢ ውጊያ ከነበረበት በግምት 23 ኪሎ ሜትር ገደማ ርቀት አለው ብለዋል።

በአካባቢው ውጊያ ባለመኖሩ ጥቃቱን “ድንገተኛ ነው” ያሉት የሃይማኖት አባት፤ እስከ ከሰዓት 8፡30 ድረስ በጥቃቱ የተገደሉ ሰዎችን አስከሬን ማንሳት የተቻለ ቢሆንም፣ ሟቾቹን ለመለየት ግን አዳጋች እንደነበር አመልክተዋል።

የሟቾች አስከሬን ክፉኛ በመጎዳታቸው ለማንሳት አስቸጋሪ ስለነበረ “በሻርፕ እና በብርድ ልብስ” ተጠቅልሎ እንዲነሱ ተደርገዋል ብለዋል።

ጥቃቱ ከደረሰ በኋላ አስከሬን ለማንሳት ወደ ስፍራው ያቀኑ ሰዎች “እኛም ላይ ጥቃቱ ይደርሳል” በሚል ስጋት ላይ እንደነበሩ ነዋሪዎች ተናግረዋል።

“ድሮኑ እየዞረ” ነበር ያሉ አንድ ነዋሪ፤ “አስከሬን ለማንሳትም በጣም ተቸግረው [ነበር]፤ ከአንድ ሰዓት በላይ ሰው እየተበታተነ፤ ድሮኗ ስትሄድ ነው ማንሳት የተቻለው። ቁስለኞችንም ቶሎ ለማንሳት ችግር እንደነበር ነው [የሰማሁት]” ብለዋል።

የሟቾች ቀብር በዚያው በጥቃቱ ዕለት ሰኞ የካቲት 11 እና በማግስቱ ማክሰኞ ቁራ ሰራ ማሪያም፣ ተክለ ሃይማኖት፣ ዋሻ ማሪያም በተባሉ አብያተ ክርስቲያናት መፈጸሙንም ተናግረዋል።

አብዛኞቹ የጥቃቱ ሰለባዎች ዘመዳሞች በመሆናቸው ሐዘኑ ብርቱ እንደሆነ የተናገሩ አንድ የሟች ዘመድ፤ በአካባቢው ፍርሃት ነግሷል ብለዋል።

“. . .የሟች እህታቸው ራሷን ስታ ነው እስካሁን ድረስ ያለችው። ሐዘኑን መቋቋም በጣም አስቸጋሪ ነው። እንደዚህ ዓይነት ነገር በአገራችን ታይቶ ስለማይታወቅ ሕዝቡ ላይ መደናገጥ ተፈጥሯል። በአሁኑ ሰዓትም መከላከያ መስመሩን ይዞ በአካባቢው ላይ እየተንቀሳቀሰ ነው። እና ሕዝቡም ከቤቱ እየወጣ አይደለም” ሲሉ እንቅስቃሴ እምብዛም ነው ብለዋል።

ቢቢሲ ከአካባቢው አስተዳደር አስተያየት ለማግኘት ጥረት ቢያደርግም፤ የወረዳው አስተዳዳሪዎች አካባቢውን ለቀው ከወጡ መቆየታቸውን እና በአካባቢው ፋኖ ለረጅም ወራት እንደነበር ሰምቷል።

በአማራ ክልል ውስጥ እየተካሄደ ባለው ግጭት ምክንያት እየተፈጸሙ ያሉ የሰው አልባ አውሮፕላኖች (ድሮን) ጥቃቶች እንዳሳሰቡት የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ከዚህ ቀደም መግለጹ ይታወሳል።

ኮሚሽኑ ከጥቂት ወራት በፊት ባወጣው መግለጫ በአማራ ክልል እየተካሄዱ ያሉ የድሮን ጥቃቶች እና ሌሎች ግጭቶች በክልሉ ሕዝብ ላይ የሚያደርሱት አውዳሚ ጉዳት በእጅጉ አሳስቦኛል ብሏል።

በድሮን በሚፈጸሙ ጥቃቶች እየደረሱ ያሉ ጉዳቶችን በተመለከተ ከመንግሥት በኩል በይፋ የተባለ ነገር ባይኖርም፣ የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ ከወራት በፊት ሠራዊታቸው ድሮኖችን በሰላማዊ ሰዎች ላይ እንደማይጠቀም ገልጸው ነበር።

ወራት ያስቆጠረው በአማራ ክልል እየተካሄደ ያለው ግጭት የተቀሰቀሰው መንግሥት የክልል ልዩ ኃይሎችን በማፍረስ መልሶ ለማደራጀት እና ሌሎች ታጣቂዎችን ትጥቅ ለማስፈታት መወሰኑን ተከትሎ ነበር።

የተለያዩ የአገር ውስጥ እና ዓለም አቀፍ ተቋማት ሁለቱ ተፋላሚ ወገኖች ወደ ድርድር እንዲመጡ እና በውይይት ችግራቸውን እንዲፈቱ ጥሪ እያቀረቡ ቢሆንም፣ እስካሁን የተጀመሩ እንቅስቃሴዎች ስለመኖራቸው የሚጠቁሙ መረጃዎች የሉም።

ካለፈው ዓመት ማብቂያ ወዲህ ባለፉት ስድስት ወራት በአማራ ክልል ውስጥ በመንግሥት ኃይሎች እና በፋኖ ታጣቂዎች የሚካሄደው ግጭት የቀጠለ ሲሆን፣ በዚህም ሳቢያ በነዋሪዎች ላይ ጉዳት እየደረሰ መሆኑ በተደጋጋሚ ተዘግቧል።

ከግጭቱም ጋር ተያይዞም በሰላማዊ ሰዎች ላይ ከሕግ ውጪ የሚፈጸሙ ግድያዎች አሳሳቢነቱ መቀጠሉን የተለያዩ ሰብዓዊ መብት ድርጅቶች እየገለጹ ይገኛሉ።

በፋኖ ታጣቂዎች እና በመንግሥት ኃይሎች መካከል እየተካሄደ ያለው ግጭት መቀጠሉ ያሳሰባቸው የተለያዩ ወገኖች ሰላማዊ መፍትሄ እንዲፈለግ ጥሪ ቢያቀርቡም ቀውሱ በአሁኑ ጊዜ እየተባባሰ ይገኛል።  ዘገባው የቢቢሲ ነው፡፡

selegna

By selegna

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *