የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት በዲፕሎማሲያዊ ውጥረት ላይ ያሉትን ሶማሊያ እና ኢትዮጵያን ጉዳይ እንደሚያነሳ ተጠቆመ።

ኢትዮጵያ ነጻ አገርነቷን ካወጀችው ሶማሊላንድ ጋር በተፈራረመችው የመግባቢያ ስምምነት ሳቢያ የተፈጠረውን ውዝግብ ዛሬ የካቲት 11/ 2016 ዓ.ም. ከሚያነሳቸውን ጉዳዮች አንዱ እንደሚሆን ምክር ቤቱ በድረ-ገጹ አስፍሯል።

በአጠቃላይ የሶማሊያ ጉዳይን በአጀንዳነት የያዘው የፀጥታው ምክር ቤት ጉባዔ መጀመሪያ ሊካሄድ የነበረው የካቲት 8/2016 ዓ.ም. ነበር። ነገር ግን ‘አፍሪካን ስሪ’ (ኤ3) በመባል የሚታወቁት የፀጥታው ምክር ቤት ሦስቱ የአፍሪካ አገራት እና ጋያና ጉዳዩ ከአፍሪካ መሪዎች ጉባዔ በኋላ ሊታይ ይገባል በሚል ያቀረቡትን ጥያቄ ተከትሎም ለዛሬ የተራዘመው።

በሳምንቱ መጨረሻ ቅዳሜ እና እሁድ የተደረገው የኅብረቱ የመሪዎች ጉባኤ በሁለቱ አገራት መካከል በተፈጠረው ውዝግብ ላይ አዎንታዊ ውጤቶች ሊያስገኝ ይችላል የሚሉ ግምት ቢኖሩም ሁለቱ አገራት ከፀጥታ ጋር በተያያዘ ውዝግብ ውስጥ ገብተዋል።

ከሁለቱ አገራት ግንኙነት መሻከር በኋላ የአፍሪካ ኅብረት መሪዎች ጉባኤን ለመታደም ወደ አዲስ አበባ አቅንተው የነበሩት የሶማሊያው ፕሬዝዳንት ሐሰን ሼኽ መሐመድ የኢትዮጵያ የፀጥታ ኃይሎች ጉባኤው ወደሚካሄድበት ስፍራ እንዳልገባ ለመከልከል ሞክረዋል ብለዋል።

በፕሬዝዳንቱ የሚመራው የሶማሊያ ልዑክ በኅብረቱ ጉባዔ ላይ እንዳይሳተፍ ኢትዮጵያ መሰናክል ሆናብኛለች ያለችው ሶማሊያ የአፍሪካ ኅብረት በጉዳዩ ላይ ታማኝ እና ገለልተኛ ምርመራ እንዲያደርግ ጠይቃለች።

ኢትዮጵያ በበኩሏ ክሱን ውድቅ ያደረገች ሲሆን፣ የሶማሊያ ልዑካን በመንግሥት የተመደቡላቸውን የፀጥታ ሠራተኞችን አንቀበልም በማለት ጠባቂዎቻቸው የጦር መሳሪያ ታጥቀው ጉባኤው ወደሚካሄድበት ስፍራ ለመግባት ሲሞክሩ በኅብረቱ የፀጥታ አካላት ተከልክለዋል ብላለች።

የሶማሊያው ፕሬዝዳንት በጉባኤው ላይ ለመሳተፍ ችለው የነበረ ቢሆንም የአዲስ አበባ ቆይታቸውን አቋርጠው ወደ አገራቸው መመለሳቸው ተዘግቧል።

ኢትዮጵያ በበኩሏ የአገራቱን መሪዎች ለመቀበል ካደረገችው እንክብካቤ አንጻር ፍጹም የማይመጥን ምላሽ ነው ስትል ሶማሊያን ወቅሳለች።

“የዲፕሎማሲ ባህል ከሚፈቅደው ውጪ የመገናኛ ብዙኃንን ትኩረት ለመሳብ እና ያልተገባ ወቀሳን ለመሰንዘር” ያለመ ነው ሲሉም 37ኛው የአፍሪካ ኅብረት ጉባኤን አስመልክቶ መግለጫ የሰጡት የመንግሥት ኮሚዩኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዲኤታ ሰላማዊት ካሳ ተናግረዋል።

የተባበሩት መንግሥታት የፀጥታው ምክር ቤት ዛሬ አጠቃላይ የሶማሊያን ጉዳይ በዋና አጀንዳነት ይዞ የሚቀርብለትን ገለጻ ከሰማ በኋላ በዝግ ምክክር ያካሂዳል ተብሏል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ከሶማሊላንድ ፕሬዚዳንት ሙሴ ቢሂ ጋር ከሳምንታት በፊት የተፈራረሙትን የመግባቢያ ስምምነትም ሉዓላዊነቷ እና የግዛት አንድነትዋን የሚጻረር ነው በማለት ሶማሊያ ውድቅ ማድረጓ ይታወሳል።

ሶማሊያ ለፀጥታው ምክር ቤት ከዚህ ቀደም ኢትዮጵያ የሶማሊያ አካል የሆነችውን ሶማሊላንድን ለመጠቅለል እየጣረች ነው በሚል ምክር ቤቱ በአስቸኳይ እንዲመክርበትም ጥያቄ አቅርባ ነበር።

ኢትዮጵያ በበኩሏ ጉዳዩ በአፍሪካ ኅብረት ማዕቀፍ የታየ በመሆኑ ምክር ቤቱ ሊመክርበት አይገባም በሚል ተቃውማ ነበር።

ምክር ቤቱ ጥር 20/ 2016 ዓ.ም. “ሰላም እና ፀጥታ በአፍሪካ” በሚል አጀንዳ የሁለቱን አገራት ውዝግብ በዝግ ሰብሰባ መምከሩ ይታወሳል።

በዚህ ጉባኤ ላይ አልጄሪያ፣ ሞዛምቢክ እና ሴራሊዮንን ያቀፈው የኤ3 አገራት እንዲሁም ጋያና ጉዳዩ በቀጣናው፣ በአፍሪካ ኅብረት ጥላ ስር እየተመከረበት መሆኑን አጽንኦት ሰጥተው ይሄም ሊከበር ይገባል ብለው ነበር።

በዚህም ስብሰባ ላይ የምክር ቤቱ አባላት የሶማሊያን ሉዓላዊነት እና የግዛት አንድነት ማክበር እንደሚያስፈልግ ገልጸው የአፍሪካ ኅብረት የአፍሪካ ቀንድ ከፍተኛ ተወካይ የሆኑትን ኦሊሴጎን ኦቦሳንጆን ልዑክ በማድረግ ሁለቱን አገራት ለማሸማገል የጀመረውን ጥረት ይደግፋል ብለዋል።

ሁለቱ አገራት የገቡበትን ውጥረት በማርገብ ችግሩን በውይይት እንዲፈቱም ምክር ቤቱ አጽንኦት ሰጥቶ ነበር።

ኢትዮጵያ እራሷን ነጻ አገር አድርጋ ካወጀችው እና ሶማሊያ የግዛቴ አካል ናት ከምትላት ሶማሊላንድ ጋር ከአንድ ወር በፊት የመግባቢያ ስምምነት ከተፈራረመች ወዲህ በሁለቱ አገራት መካከል ውዝግብ መቀስቀሱ ይታወቃል።

በስምምነቱ ሶማሊላንድ ለኢትዮጵያ 20 ኪሎ ሜትር የሚረዝም የባሕር ጠረፍ ለመስጠት ስትስማማ፣ ኢትዮጵያ ደግሞ በምላሹ ለሶማሊላንድ የአገርነት እውቅና እንደምትሰጥ መጠቀሱ ተገልጿል።

ምክር ቤቱ ከሁለቱ አገራት ውጥረት በተጨማሪ የሶማሊያ የምሥራቅ አፍሪካ ማኅበረሰብ አባልነት፣ በአገሪቱ ላይ ተጥሎ የነበረው የመሳሪያ ማዕቀብ በምክር ቤቱ የመነሳት ውሳኔ እንዲሁም አልሻባብ በፀጥታው የደቀነው ስጋት የሚሉት መወያያ እንደሚሆኑም ተጠቁሟል።   ዘገባው የቢቢሲ ነው፡፡

selegna

By selegna

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *