የአጼ ኃይለ ሥላሴ ዘውዳዊ መንግሥትን በማስወገድ በኢትዮጵያ የፊውዳላዊ ሥርዓትን ከፍጻሜ ያደረሰው የኢትዮጵያ አብዮት በዚህ ዓመት የካቲት ወር 50 ዓመት ሆነው።

አብዮቱ መሠረታዊ ለውጦችን ያስገኘ ቢሆንም፣ አሁንም ድረስ አገሪቱ በግጭት እና በለውጥ ሂደት እየተናጠች ትገኛለች።

ለመሆኑ የየካቲት 1966ቱ የኢትዮጵያ አብዮት ምን ለውጥ አስገኘ? ምንስ የቀረው ነገር አለ? 50ኛ ዓመት የወርቅ ኢዮቤልዩ ዓመቱ ሲዘከርስ በምን መልኩ መሆን ሊሆን ይገባል? በሚል ቢቢሲ በዚህ በየካቲት ወር የአብዮቱን ታሪክ፣ ክስተቶችን ተሳታፊዎችን የሚዳስሱ ተከታታይ ዘገባዎችን ያቀርባል።

እነሆ ለመጀመርም የኢትዮጵያ አብዮት 50ኛ ዓመት በምን መልኩ መዘከር ይገባል። በአብዮተኞቹ እና በአዲሱ ትውልድ መካከል የሚኖረው ግንኙነት እና ከአምስት አስርት ዓመታት በኋላ አብዮቱን መለስ ብሎ በመቃኝት ለአገሪቱ የወደፊት ጉዞ ምን አስተዋጽኦ ማበርከት ይቻላል በሚል የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲው መምህር ዮናስ አሽኔ (ዶ/ር) ሃሳባቸውን ሰንዝረዋል።

እንደ መግቢያ

የየካቲት 1966 ዓ.ም. አብዮት በኢትዮጵያ ለዘመናት ሥር ሰዶ የቆየውን ሥርዓት በመለወጥ መሠረታዊ ለውጥ አምጥቷል ተብሎ ይታመናል።

አብዮቱ የነባሩን ሥርዓት የመደብ ልዩነት አፍርሶ አዲስ ሥርዓት የፈነጠቀ ለሚሊዮኖች የሕይወት ሽግግር ምክንያት የሆነ የለውጥ ማዕበል ነበር።

አብዮቱ መሬት አልባዎችን ባለ መሬት፣ ቤት የሌላቸውን ባለቤት፣ የበላይ እና የበታች የነበሩትን አቻ ለማድረግ የነፈሰ ፈጣን አውሎ ነፋስ ነበር። ይህ አብዮት የሃምሳ ዓመት የወርቅ እዮቤልዪ በዓል የሚከበርለት ዓመት ይኸው 2016 ዓ.ም. ነው።

ነገር ግን ብዙም አብዮቱን የማስታወስ እና የመዘከር ፍላጎት አይታይም። ለምን? ይህ ጽሑፍ ስለአብዮት ምንነት እና ፋይዳው መሠረታዊ መረጃ በማቀረብ የ50 ዓመት ልደቱን የማክበር ፋይዳን በወፍ በረር ይዳስሳል።

ፅንሰ ሃሳብ እና ንድፈ ሃሳባዊ ዳሰሳ

ብዙ ሰዎች በተለይም የአዲሱ ትውልድ አባላት የአብዮቱን ተረክና ታሪክ ከደም አፋሳሽነቱ ጋር ብቻ የሚረዱት ይመስላል።

በመጀመሪያ በአብዮታዊ ድርጅቶች፤ በመቀጠል በወታደራዊ መንግሥት እና በነፃ አውጪ ግንባሮች ሲካሄድ የቆየው የእርስ በእርስ ጦርነት የአብዮቱ ትርጉም ገላጭ የሆነ ይመስላል።

ስለዚህም የአብዮት ትርጉም ከዚሁ ደም አፋሳሽ ፋይዳው ጋር ብቻ የሚታሰብ ሆኗል።

በብዙ ምክንያቶች ብዙ የድኅረ አብዮት ትውልድ አባላት ከአብዮቱ መነጠል ወይም ፍፁም አለመገናኘት እና የእነሱ ትውልድ ጉዳይ አድርጎ አለማየት ይታያል።

እንድያውም ወደፊት ብቻ የሚመለከት ትውልድ የመጣ ይመስላል። በአብዮት ላይ አብዮት ያስነሳ ትውልድ አስመስሎታል።

ነገር ግን የአብዮትን ፅንሰ ሀሳብ ብንመረምር ምናልባት ወደፊት መመልከት ራሱ አብዮት ሊሆን እንደሚችል መረዳት ይቻል ይሆናል።

አብዮት ራሱ ወደፊት የሚያሰፈነጥር የለውጥ ዓይነት ነው። ለውጡ ነባራዊውን የማኅበረሰብ መዋቅር እና አደረጃጀት፣ ከፖለቲካ እንዲሁም ከኢኮኖሚ ባለቤቶቹ ተምኔታዊ ከሆነው ትልም እና ተረክ ጋር አብሮ ሁሉንም በአዲስ ማኅበረሰባዊ መዋቀር እና አደረጃጀት ብሎም በአዲሰ ፖለቲካ እና ኢኮኖሚያዊ ልሂቃን መተካት ነው። ለዚህም አዲሱን አንባሪ ተረክ እና ህልም መድረስ ያካትታል።

ብዙ ጊዜ ይህ ለውጥ ድንገቴ፣ ፈጣን እና ደም አፍሣሽ ይመስላል፤ ነገሩ ግን ታሪካዊ እና መዋቅራዊ ጉዞን ተከትሎ የሚከሰት ኅበረተሳባዊ ለውጥ ነው።

ይህ ክላሲካል አብዮት የሚባለው በሄይቲ፣ በፈንሳይ፣ በሩሲያ፣ በቻይና ብሎም በኩባ እና በቪየትናም የተካሄዱ አብዮቶች የሚገለጹበት ፅንሰ ሃሳባዊ ትንተና ነው። ለነገሩ የኢትዮጵያ አብዮት ራሱ ከእነዚህ አብዮቶች ጋር ንግግር ነበረው።

የኢትዮጵያም አብዮት ከእነዚሁ ክላሲካል አብዮቶች ተርታ ይመደባል። ሂደቱ አፍርሶ የመሥራት ሁኔታ ነው። ነባሩ ሥርዓት መዋቅራዊ ቅራኔ ውስጥ በመግባቱ ራሱን ማደስ እና ማሻሻል የማይችል፣ ባለበት የሚረግጥ፣ በፍጹም ዝግመታዊ ለውጥ እንኳ በማካሄድ አዲስ ትውልድ ማሳተፍ የማይችልበት ደረጃ ሲደርስ አብዮታዊ ሁኔታ ይፈጠራል።

ይህ ነባራዊ እውነት ብሶትን ቁጭትን የለውጥ መሻት ብሎም በሂደት ንቃተ ህሊናው የዳበረ ማኅበረሰብ ሲፈጥር ማኅበራዊ፣ ስሜታዊ፣ ግላዊ የአብዮት ተዋንያንን ይፈጥራል። የነባራዊው እና የስሜታዊ ንቃተ ህሊና መስተጋብር እንዲሁም የሁለቱ ባንድ ዘመን መገናኘት አይቀሬውን ፈጣኑን የለውጥ እንቅስቃሴ እንዲከሰት ይፈቅዳል።

በዚህም አፍርሶ የመሥራቱ ጉዞ ይጀምራል። ይህ ጉዞ አብዮት ይባላል። ይህም ብዙ ጊዜ በመደባዊ ቅራኔ ውስጥ ይፈጥራል።

የነባሩ ሥርዓት ተጠቃሚ በአንድ ጎራ፣ የተገፋው ማኅበረሰብ በሌላ ጎራ በሂደት ይሰለፋሉ።

ይህም ሂደት የመደብ ሽግግር በማምጣት የተገፋውን ተጠቃሚ የማድረግ ትግልን ይወልዳል። ትግሉ በአብዛኛው ከታችኛው ግርጌ ካለው ማኅበረሰብ የሚቀጣጠል ተራማጅ የነባሩ ሥርዓት ተጠቃሚዎችን ከላይ ሊያሳትፍ የሚችል የለውጥ ማዕበል ነው።

የኢትዮጵያ አብዮትም በዚህ ፅንሰ ሃሳባዊ ትንተና ሊገለጽ ይችላል። በሥነ አብዮት ድርሳናት ግን የኢትዮጵያ አብዮትን በተመለከት ከሚነሱ ብዙ ክርክሮች መካከል የሚከተሉት ዋነኞቹ ናቸው።

መዋቅር ወለድ ወይስ የንቁ ኅበረተሰብ ፈጠራ

ስለ አብዮት ሲታሰብ፣ ስለ ነገረ ፈጠራ እና ስለለውጥ ማሰብ ነው።

አብዮት አንድም መዋቅራዊ ቅራኔ የወለደው አይቀሬ የለውጥ ዓይነት ነው።

ሌላም ብሶት የወለደው ማኅበር በግብታዊነትም ይሁን በሂደት በሚዳብር ንቃተ ህሊና ተመርቶ በትግል የሚፈጠር ክስተት ነው።

በተመሳሳይ አብዮትን ዲበአካላዊ የታሪክ መንፈስ የራሱን ፍፁማዊነት የሚገልጥበት ነው በማለት ክስተቱን ከሰው ልጅ እጅ በማውጣት ሜታፊዚካል ያደርጉታል።

ሌሎች ደግሞ የማኅበረሰቡ ብሶት እና መገፋት የወለደው ለውጥ ነው በማለት ታሪኩን ለሰው በመስጠት ይከራከራሉ።

አብዮት ማኅበራዊ እና ሰዋዊ ክሰተት ነው። እንደ ጦርነት ወይም መፈንቅለ መንግሥት ወይም እንደ ቴክኖሎጂ ፈጠራ አብዮት የሰው ልጆች የሚፈጥሩት ክስተት ነው ብለውም ያሰረዳሉ።

የቀድሞዎቹ አብዮት፣ አብዮተኞችን ፈጠረ ሲሉ ሌሎቹ አብዮተኞች አብዮትን ፈጠሩ ይላሉ።

የኢትዮጵያን አብዮት አንዳንዶች መዋቀራዊ ወለድ የሆነ ባልተዘጋጀ በተለይም ባልተደራጀ ማኅበረሰብ ውስጥ የተከሰተ የለውጥ ማዕበል ነው ይላሉ።

አብዮቱ አብዮተኞችን ፈጠረም ይላሉ። ሌሎች በተቃራኒው አብዮቱ የተማሪዎች፣ የታክሲ አሽከርካሪዎች፣ የሠራተኞች እና ብሶት የተሰማቸው ኢትዮጵያውያን የትግል ውጤት ነው ይላሉ።

እውነታው ብዙ ጊዜ አማካዩ ላይ ነው። ያለመዋቅራዊ መደባዊ ቅራኔ ነባራዊ የአብዮት ሁኔታም ስሜታዊ ንቃተ ህሊናም አይፈጠርም። ያለ አብዮተኞች አብዮትም ሊካሄድ አይችልም።

ዝመና ወይስ ጉስቁልና

ሌላው ክርክር አብዮት የድህነት፣ የመገፋት እና የጉስቁልና ውጤት ነው።

ያልተቸገረ ሰው አብዮት አያስነሳም፤ እንዲያውም ከሌሎች ማኅረሰቦች አንፃር አንሶ መገኘት የአብዮት መነሻ ነው የሚሉ በአንድ ወገን ሲገኙ፣ የኢትዮጵያን አብዮት የጎሰቋሎች አብዮት እና በውጤቱም ለጎስቋሎች የደረሰ ነው ይላሉ።

በሌላ ወገን ደግሞ አይ አብዮት የዘመናዊ ፖለቲካ ኢኮኖሚ ውጤት ነው።

ክስተቱ ዘመናዊነት በተለይም የትምህርት እና የመገናኛ ብዙኃን መስፋፋት የሚወልደው ነው ይላሉ። የኢትዮጵያንም አብዮት ከዘመናዊ ተቋማት መዋቅር መስፋፋት ጋር ያያይዙታል።

በተለይም የአብዮቱ ዋነኛ ተዋናይ ከሆኑት ተማሪዎች እና የትምህርት መስፋፋት ጋር ያቆራኙታል። አሁንም ሁለቱም ነባራዊ ሁኔታ በኢትዮጵያ የተከሰተ በመሆኑ ታሪኩን በሁለቱ ንድፈ ሃሳቦች መረዳት ይቻላል።

ልሂቃዊ ወይስ ኅብረተሳባዊ

ሌላው ክርክር የኢትዮጵያ አብዮት ልሂቃዊ ወይም ከላዕላይ መንበር በተነሱ ወታደሮች ወይም ለቤተመንግሥት ቅርብ በሆኑ ልሂቃን የተካሄደ ፖለቲካዊ ለውጥ ነው ሲሉ፤ ሌሎች ደግሞ ክሰተቱ ሕዝባዊ እና ከታህታይ የማህበረሰብ ክፍል የተነሳ ማዕበል እንደሆነ በመግለጽ አብዮቱን ኅበረተሰባዊ ያደርጉታል።

ለዚህም ማሰታረቅያው በኢትየጵያ አብዮት ውስጥ የሕዝብ ተሳትፎ የሚካድ ባለመሆኑ ማኅበራዊ ወይም ኅበረተሰባዊ አብዮት ሲያደርገው፤ የላዕላይ ልሂቃን በተለይም በመደብ ከፍተኛ ደረጃ ካላቸው የበላይ ከሆኑ ቤተሰቦች የተወለዱ ወጣቶች የመሩት እና የተሳተፉበት በመሆኑ ፖለቲካዊም ማኅበራዊም ለውጥን ያጣመረ ኅበረተሳበዊ አብዮት መሆኑን መገንዘብ ያሻል።

መምህራን፣ ተማሪዎች፣ የሠራተኛ ማኅበራት ብሎም ወታደሮች ዋነኞቹ አብዮተኞች ነበሩ። የካቲት 1966 የመምህራን፣ የተማሪዎች እና የታክሲ አሽከርካሪዎች ሰላማዊ ሰልፍ የአደባባይ ተቃውሞ የአብዮቱ ጅማሮ ማሳያ ነበር።

ከአዲሰ አባባ እና አካባቢዋ በሂደት ብዙ ከተሞች በኅብረተሰቡ አመፆች እና ተቃውሞዎች መጥለቅለቅ የጀመሩት ከየካቲት ወር አንስቶ ነበር። ያለእነዚህ ሕዝባዊ አመፆች አብዮቱ የሚታሰብ አልነበረም።

ምንም አንኳ ከየካቲት ጀምሮ የተቀጣጠሉት አመፆች ከተሞች እና ከተማ ቀመስ አካባቢዎች ላይ የተካሄዱ ቢሆኑም የአብዮተኞቹ የሥርዓቱ ነባራዊ ሁኔታና ቅራኔው ገጠር ከተማ በሚል የተለየ አልነበረም።

የከተሜዎቹ አብዮታዊ ንቃት ያለገጠሬው ብሶት እና ምሬት የሚገነባ አልነበረም። አብዛኞቹ ከተሜዎች ከገጠር የተነጠለ ማንነት አልነበራቸውም። ከእነዚህ ክርክሮች ባሻገር የአብዮቱ የአዲስ ሥርዓት ግንባታ ፍላጎትን መመልከት ያሻል።

አብዮታዊ ህልም እና አዲስ ሥርዓት

ከየካቲት 1966 ዓ.ም. ጀምሮ በከተሞች የተቀጣጠለው አመፅ ከአንዱ ከተማ ወደሌላው የሚሻገር ለስድሰት ወራት የቆየ ሕዝባዊ ማዕበል ነበር።

የየካቲቱ አብዮት የሚባለውም ለዚሁ ነው። ይህን ተከትሎ ከሰኔ እስከ መስከረም ወታደራዊው ደርግ በሂደት ሥልጣኑን ሙሉ በሙሉ ከንጉሣዊው አስተዳደር ተረከበ።

አዲሱን ሥርዓት የመገንባት ሂደት “ኢትዮጵያ ትቅድም” በሚል መፈክራዊ መመርያ ማወጅ ጀመረ። በሂደትም በተለይ ከ1967 ዓ.ም. ኅዳር ወር ጀምሮ ኅብረተሰባዊት ኢትዮጵያ ወይም ኢትዮጵያዊ ሶሻሊዝም የአዲሱ ሥርዓት የፖለቲካ ኢኮኖሚ መመሪያ መሆኑን አወጀ። ሲቪል አደረጃጀቶች በተለይም የኢህአፓ እና የመኢሶን ክርክር እና ሂስ በተለይም የሕዝባዊ መንግሥት ይቋቋም ጥያቄ የደርግን ውሳኔዎች እና ሥልጣን የመቆናጠጥ ጉዞን አልተለዩትም ነበር።

የሶሻሊስት ኢትዮጵያን ወደ ተግባር ለመለወጥ በ1967 ዓ.ም. የግል ሀብት እና ንብረት ማለትም ባንኮች እና ፋብሪካዎችን በመውረስ ተጀመረ።

በመቀጠል የኢትዮጵያ ተማሪዎች “መሬት ላራሹ” በሚል መፈክር ሲጠይቁ የነበረውን የመሬት ስሪት የሚለውጥ አዋጅ በዚያው ዓመት በየካቲት ወር ታወጀ።

በአዋጁም ሁሉም የገጠር መሬት የኢትዮጵያ ሕዝብ የጋራ ሀብት እንደሆነ ተደነገገ። በዚህ አዋጅ መሠረትም በባላባቶች ተይዞ የነበረው መሬት ምንም እንኳ ለአራሹ ቢከፋፈልም ገበሬው የተሰጠው መብት በመሬቱ የመጠቀም እንጂ የመሸጥ እና የመለወጥ ሙሉ መብትን አልተጎናጸፈም።

መሬት ላራሹ እንዲከፋፈል ለዚሁም ገበሬው ተደራጅቶ ይህን አዋጅ አንዲያሰፈጽም ቁልፍ መሳሪያ የነበሩት የገበሬ ማኅበራት እንዲመሠረቱ አዋጁ ደንግጎ ነበር።

በዕድገት በሕብረት ዘመቻም መምህራን እና ተማሪዎችን ከከተማ ወደ ገጠሪቱ ኢትዮጵያ ማሰማራት የመሬት ክፍፍሉን ለማሳለጥ እና አብዮታዊ ሽግግሩን ለማፈጠን የታሰበ ነበር።

ይህም አዋጅ ሰፊ ሕዝባዊ ድጋፍ የነበረው ተገዳዳሪ ቡድኖች ሳይቀሩ የደገፉት እርምጃ ነበር። በእርግጥ ይህ ሁኔታ ለብዙዎች የሚሰጠው ትርጉም የተለያየ ነበር።

በሐምሌ ወር 1967 ዓ.ም. የከተማ ቦታ እና ትርፍ ቤቶች በመንግሥት እንዲወረሱ የተደረገበት ውሳኔ ደግሞ በአዋጅ ተደነገገ።

ይህም እንደ ገጠሩ መሬት ሁሉ የከተማ ቦታ ብሎም ቤቶችን ከግለሰቦች ወደ መንግሥት ባለቤትነት በማሸጋገር ለብዙዎች በኪራይ የተከፋፈለበት አብዮታዊ እርምጃ ነበር። በተመሳሳይ የከተማ ነዋሪዎች ማኅበራትን በማደራጀት እንደ ገጠሩ ሁሉ አዲሱን ሥርዓት እንዲያቀለጥፉ ተልዕኮ በመያዝ በየከተማው ተመሠረቱ።

አነዚህ ተስፋ ሰጪ የለውጥ እርምጃዎች በሂደት ትውልድ ወደሚያሳጣ ደም አፋሳሽ ግጭት እና ሽብር ብሎም የእርስ በርስ ጦርነት መግባት፣ ሥልጣንም ወደ አንድ ሰው እጅ በመግባት፣ ወደ አምባገነናዊ ሥርዓት መሸጋገር እጣው ሆነ።

ይህም እስከ 1983 ዓ.ም. የሽግግር ፖለቲካ ድረስ ሲቀጥል፣ ሌሎች ያልተመለሱ ጥያቄዎች በተለይም የብሔረ ጥያቄ፣ የሴቶች ጥያቄ፣ የዲሞክራሲ ጥያቄ ብሎም በኢኮኖሚ የማሸጋገር ጉዳይ በተለያዩ መንገዶች ሲሰተናገዱ እነሆ 50 ዓመታት ተቆጠሩ።

በዚህ በየካቲት ወር የኢትዮጵያ አብዮት ከፈነዳ እነሆ ሃምሳ ዓመት ሆነው። ይህም ዛሬ ላይ በመሆን አገሪቱ እና ሕዝቧ የተጓዙበትን መንገድ ወደ ኋላ ለመመልከት ጥሩ አጋጣሚ የሚፈጥር ነው። መለስ ብሎ ከመቃኘት ባሻገርም ይህንን አጋጣሚ እንዴት መጠቀም አለብን?

የኢትዮጵያ አብዮት፡ እርግማን ወይሰ በረከት

ዶ/ር እሌኒ ሳንቲም ‘ኢትዮጵያ ኢን ቲዎሪ’ የሚለውን ታሪክን እና ንድፈ ሃብን ባጣመረው መፅሐፏን በትዝታ እና በንድፈ ሃሳብ በተገነባ ሥነ ዘዴ ትጀምራለች።

ትዝታ መጀመሪያ ትናትን ከዛሬ የሚያስብ ነው። ዛሬ በሌሎች ሰዎች ተስፋ የተደረሰ ዘመንም ነው። የኢትዮጵያን ዛሬ ከአብዮተኞቹ ተስፋ ውስጥ መፈለግ ማለት ነው።

ተስፋቸውን ለማረም ሳይሆን፣ የዛሬ ጥያቄ ከዚያ ዘመን ሙዳይ ውስጥ ለመጠየቅ ነው ትላለች።

እሌኒ እንደምትለው በአብዮት ዘመን ውስጥ በተፈጠሩ ያልታረቁ ታሪካዊ ቅራኔዎች የተፈጠረ ዛሬን መመርመር በተለይም አብዮቱን በሚወክሉ ታሪኮች እና ተረኮች፣ ትዕምርቶች እና ዲሰኩሮች መካከል የምናገኘውን ትርጉም ከዛሬ ፈተናዎች እና ችግሮች ጋር በማዛመድ ጥያቄዎችን መጠየቅ ነው።

ይህን በማድረግ የአብዮቱን ሃምሳ ዓመት መዘከር ይቻላል።

ይህንን ስናደርግ አንድም አብዮቱን በኑፋቄ ብዕራቸው ከሚኮንኑት፣ በተለይም በሥር ነቀልነቱ እና በአፍራሽነቱ ከሚከሱት፤ በሌላ በኩል ድግሞ በናፍቆት ድሉን ከሚዘክሩት፣ ድርሳን ከሚደርሱለት እና ሌላ ትርጉም ከሚሰጡት በሻገር በአብዮቱን መመልከት ማለት ነው።

በተለይም በአብዮተኞች ተስፋ ከተደረሰበት ዛሬ ውስጥ መኖር ምን ማለት ነው ብሎ መጠየቅ የአብዮት ትዝታ እና ዝክር ጥያቄን ይመለከታል።

የአብዮትን ዝክር እንዲያው ዝም ብሎ ትናትን ዛሬ ላይ ማስታወስ ሳይሆን፤ ስለዛሬ ክርክር ማድረግ፣ ስለዛሬ መጠየቅ ነው።

በተለይም የአብዮቱ የ50 ዓመት የተስፋ ጉዞ የት አደረሰን? ብሎ መመርመር እና መከራከር ማለት ነው። ይህም ማለት አብዮተኞቹን ከመርገም እና ከማሞገስ ተሻግሮ ተስፋቸው ምን ዓይነት እኛን እና የእኛን ዘመን ፈጠረ ብሎ መነጋገር ማለት ነው።

ለምሳሌ የሶሻሊስት ማኅበረስብ ህልም ለሃምሳ ዓመት ከተገነባው ብሔራዊ ፖለቲካ ኢኮኖሚ አንፃር በተለይም ከዛሬው ነባራዊ ሁኔታ አኳያ በመመልከት፣ የመጪውን የ50 ዓመት ጉዞ ለመተልም መከራከር እና መወያየት አስፈላጊ ሊሆን ይችላል።

በሶሻሊስታዊ መርሃ ግብር ሥር የታወጁ መሬትን፣ ቤትን፣ ኢንዱስትሪን እና የባንክን ወደ መንግሥት ይዞታነት መዞራቸው ከ50 ዓመት ጉዞ በኋላ የት እንዳደረሰን መጠየቅ ተገቢ ሊሆን ይችላል።

የብሔር እና ሌሎች ማንነትን መሠረት ያደረጉ የዲሞክራሲ ጥያቄዎች እና መልሶቻችን ወዴት ወሰዱን? የዛሬዎቹ ጥያቄዎች አንዴት በተሻለ መንገድ እናንሳቸው እንዴትስ ይመለሱ? ብሎ ለመጠየቅ የአብዮቱን ዝክር ጠረጴዛ ማሰናዳት ያሻል።

ከሁሉ በላይ ያለንበት አገራዊ፣ ቀጠናዊ እና ዓለም አቀፋዊ ነባራዊ ሁኔታዎችን ለመመርመር የአብዮቱን እዮቤልዩ አንደ አጋጣሚ መጠቀም ያሻል።

ለአብዮተኞቹም ከዚሁ ትውልድ ጋር ለመነጋገር የሕይወት ታሪክ መጽሐፍ በመፃፍ በትውልዶች መካከል የደራሲ እና የተደራሲ ግንኙነት ላይ ብቻ ከመመሥረት፣ የትውልዶች ውይይት ለመክፈት ጥሩ አጋጣሚ ነው።

ለድኅረ አብዮት ትውልድ የአብዮት ትውልድ የወረሰውን ቅራኔ ለመከለስ እና በራሱ ዘመን ለማሸጋገር እንዲሁም የራሱን አዲስ ተስፋ ለመተለም ሊጠቀምበት ይገባል።

የዛሬ ዘመን ትውልድ የፍትሕ ተስፋን፣ ፍትሃዊ ነገን ለመተለም እና ለመገንባት በትናንቱ አብዮት በኩል ሊመለከትውም ይችላል።

ከአምስት አስርት ዓመታት በፊት ፈንጥቆ የነበረውን የአብዮቱን ተስፋ ዲሞክራሲያዊ ለማድረግም ያስችላል።

(ይህ ጽሑፍ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ከሚገኙ ወዳጆቼ ጋር በምናደርገው ውይይት የዳበረ ነው። በተጨማሪም በተለያዩ ምሁራን የተጻፉ መጽሐፍትን እንደ ማጣቀሻነት ተጠቅሜያለሁ።)

_____

*ዮናስ አሽኔ (ዶ/ር) በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የፖለቲካል ሳይንስ እና ዓለም አቀፍ ግንኙነት የትምህርት ክፍል ተባባሪ ፕሮፌሰር ናቸው)    ዘገባው የቢቢሲ ነው፡፡

selegna

By selegna

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *