ለደኅንነቱ ሲባል ስሙን የማንጠቅሰው ግለሰብ በአዋሽ አርባ ወታደራዊ ካምፕ ውስጥ በሚገኝ ጊዜያዊ ማቆያ ከአርባ ቀናት በላይ አሳልፏል።

ግለሰቡ በአማራ ክልል በፋኖ ታጣቂዎች እና በመከላከያ ሠራዊት መካከል የተከሰተውን ግጭት ተከትሎ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ከታወጀ ከአስር ቀናት ገደማ በኋላ ነበር በአዲስ አበባ ከተማው ውስጥ በመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች በቁጥጥር ሥር የዋለው።

እርሱ እንደሚለው “ከፋኖ ታጣቂዎች ጋር ግንኙነት አለህ” በሚል ነበር የተያዘው።

የተያዘበትን አጋጣሚና በአዋሽ አርባ ቆይታው የገጠመውን በራሱ አንደበት እንዲህ ሲል ይተርካል። ግለሰቡ አሁንም የደኅንነት ስጋት አለኝ ስላለ ከስሙ በተጨማሪ ማንነት ሊጠቁሙ የሚችሉ መረጃዎች እንዲቀሩ ተደርገዋል።

* * *

ከሌሊቱ 6፡00 ሰዓት አካባቢ ነበር። የተወሰኑት የፀጥታ ኃይሎች በአጥር ዘለው ወደምኖርበት ግቢ ገቡ።

ቤተሰቦቼ የመጡት ሰዎች የፀጥታ ኃይሎች መሆናቸውን ሲረዱ የፍርድ ቤት ትዕዛዝ ጠየቁ፤ የመለሰላቸው ግን አልነበረም።

ቤተሰቦቼ ባለኝ የፖለቲካ ተሳትፎ ምክንያት እኔን ፈልገው እንደመጡ አላጡትም። ሆኖም እናቴ ያለ ፍርድ ቤት ትዕዛዝ ግቢያችን መደፈሩ አንገበገባት። ድጋሚ የፍርድ ቤት ወረቀት ጠየቀች። በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ይህ እንደማይጠየቅ ልብ አላለችም ነበር።

በዚህ የተበሳጩት የፀጥታ ኃይሎች እናቴ ላይ እጃቸውን ሲሰነዝሩ ግብ ግብ ተፈጠረ። ከዚያም የነበርኩበትን ክፍል ከፍቼ ወጣሁ።

በመኪና ይዘውኝ ሜክሲኮ ወደሚገኘው የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ከነፉ። እኖርበት የነበረው አካባቢ ራቅ ያለ ስለነበር መሃል መንገድ ላይ ሲደርሱ አውርደው ይደበድቡኝ ጀመር።

“ፋኖ ያስጥልህ እንደሆነ እናያለን!” ይሉኝ ነበር ደጋግመው። አብረው የነበሩ የፀጥታ ኃይሎች ቆመው እያዩ “ፊቱን እንዳትመቱት! ፊቱን እንዳትመቱት!” እያሉ ሲናገሩ ብቻ ነበር የሚሰማኝ። ፊቴ ላይ አንዳች የድብደባ ምልክት እንዳይታይ ነበር ፊቱን አትምቱት የሚባባሉት። ደረቴን እና ኩላሊቴ አካባቢ መቱኝ።

ከሌሊቱ 8፡00 ሰዓት አካባቢ ፖሊስ ኮሚሽን ደረስን። ሌሊቱ እዚያው ነጋ። በነጋታው ለፍተሻ ብለው ወደ ቤት ወሰዱኝ። ቤቴ ተበረበረ። የተገኘ ነገር አልነበረም። ወደ ነበርኩበት መለሱኝ።

ከዚያም ከሌሊቱ 10፡00 እስከ 11፡00 ሰዓት ባለው ጊዜ በካቴና ታስሬ ከሌሎች ተጠርጣሪዎች ጋር ወደ አዋሽ አርባ ጉዞ ጀመርን።

“ወዴት ነው የምትወስዱን ለቤተሰብ እናሳውቅ” ብለን ብንጠይቃቸውም “እኛም አናውቀውም፤ ዝም ብላችሁ ሂዱ” የሚል መልስ ነበር ያገኘነው።

ከረፋዱ 5፡00 ሰዓት አካባቢ እዚያ ደረስን።

እንደደረስን ሌላ መርማሪ ቃላችንን ተቀበለን። የጤና ሁኔታዬን ሲጠይቁኝ በደረሰብኝ ድብደባ ለመተንፈስ እንደምቸገር ነገርኳቸው። እዚሁ ሕክምና ታገኛለህ ብለው አስገቡኝ።

“የምክር ቤት አባላቱን ተቀላቀልኩ”

በመከላከያ ሚኒስቴር የምዕራብ ዕዝ ማሠልጠኛ ማዕከል የሚል ታፔላ በሩ ላይ የተሰቀለበትን ግቢ ያገኘነው ከአዋሽ አርባ ከተማ መጨረሻ ወደ ግራ ታጥፈን 12 ኪሎ ሜትር ገደማ ከተጓዝን በኋላ ነበር። የተንጣለለ ግቢ ነው።

አጥር የለውም። መግቢያው ግን የብረት በር አለው። ከግቢው ጀርባ የአዋሽ ወንዝ አለ።

ግቢው ውስጥ ትልቅ አደባባይ አለ። እዚያ አካባቢ የሠልጣኞች መመገቢያ አለ። እሱን አለፍ ስንል አምስት በቆርቆሮ የተሠሩ መጋዘኖች አሉ። በኋላ ላይ አንደኛው ስቶር ሌሎቹ ደግሞ የከዱ ወታደሮች ማሰሪያ እንደሆኑ ሰማሁ።

እነዚህን መጋዘኖች እንዳለፍን በግንብ የተሰራ ሰፊ አዳራሽ አለ። እኛን እዚያ ነው ያስገቡን። ይህ አዳራሽ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል የሆኑት ክርስቲያን ታደለ፣ የአማራ ክልል ምክር ቤት አባል አቶ ዮሐንስ ቧያለው፣ የአዲስ አበባ ምክር ቤት አባል ካሳ ተሻገር (ዶ/ር) እንዲሁም ሌሎች የተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮች የታሰሩበት ነው።

በአዳራሹ ውስጥ የነበርነው እስረኞች በአጠቃላይ 66 ነበርን።

በአካባቢው ከፍተኛ ሙቀት ነው ያለው። ልብስ ለብሶ መዋል፣ ማደር ከባድ ነው። አንዳንዶቻችን ሐፍረተ ሥጋችንን ብቻ ሸፍነን ነበር የምንቀመጠው።

ጠዋት ላይ ዳቦ እና ሻይ፣ ምሳ እና እራት ምስር ወጥ በዳቦ ይቀርብልናል። አርባ አምስቱንም ቀን ስቆይ በአብዛኛው ምግባችን አልተለወጠም ነበር።

በርግጥ የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን መጥቶ ከጎበኘን በኋላ በሳምንት አንድ ፍየል ያርዱ እንደነበር አልክድም። ግን በቂ አልነበረም።

ለመፀዳዳት ካልሆነ በስተቀር ከመጋዘኑ መውጣት አይቻልም። ለመፀዳዳትም ቢሆን የሚፈቀደው በቀን ሁለት ጊዜ ብቻ ነው።

ማለዳ ከጠዋቱ ከ1፡00 እስከ 1፡30 ባለው እና አመሻሽ ላይ ደግሞ ከ11፡00 እስከ 12፡00 ሰዓት ጊዜ በቡድን ከፋፈለው ለሽንት ይዘውን ይወጣሉ- ወደ ጫካ።

ጫካው አቅራቢያ ለመቃብር የተዘጋጁ የሚመስሉ በግምት 50 የሚሆኑ ጉድጓዶች አሉ። እዚያ አካባቢ ነበር የምንፀዳዳው።

ከእነዚህ ሰዓት ውጪ ሽንቱ የመጣበት ካለ በሃይላንድ [በፕላስቲክ ኮዳ] ከማጠራቀም ውጭ ምርጫ የለውም።

በሙቀቱ ላይ ውሃ አለመጠጣት ከባድ ነው። ውሃ ከጠጣን ሽንት አለ። የምንሸናው ደግሞ ውስን በሆነ ወቅት። አንዳንዶች ሽንታቸውን ለመቋጠር አሊያም የሚጠጡትን ውሃ ለመቀነስ ይሞክራሉ። ይህ ግን የሚቻል አይደለም።

“ሬሳ ያወጣል ከሚባል ‘አውጭኝ’ ከተባለ እንስሳ ጋር ግብግብ”

የታሰርንበት መጋዘን ከብሎኬት የተሠራ ነው። ከመጋዘኑ ጀርባ በተቆለለ አፈር ላይ የድንጋይ ምልክት የተደረገባቸው በግምት 100 የሚሆኑ መቃብሮች ያሉበት ቦታ አለ። የመጋዘኑ በር ከብረት የተሠራ ነው።

በሩ ከተዘጋ አየር ስለማይገባ ገርበብ ተደርጎ ነው የሚተወው።

መብራት የምናገኘው ከጄኔሬተር ስለሆነ ምሽት 4፡00 ሰዓት ላይ ይጠፋል። ኃይል ለመቆጠብ ይመስለኛል የሚያጠፉት።

ታዲያ ጨለማውን ተገን አድርጎ ይሄው ከውሻ አነስ የሚል ጥቁር፣ ጅራተ ረጅም እንስሳ ገርበብ ተደርጎ በተተወው በር ሰተት ብሎ ይገባል።

እሱን ለማስወጣት ግብ ግብ ነው።

ቀደም ብለው የገቡት ታሳሪዎች በብረት ከተሠሩት ተደራራቢ አልጋዎች የተነቃቀሉ የብረት ዘንጎችን አዘጋጅተው ኖሮ በእርሱ ለማባረር ይሞክራሉ።

በሙቀቱ ሳቢያም እንዲሁም አይጡም፣ እባቡም፣ አውጭኙም እየገባ ስለሚያስበረግገን እንቅልፍ ባይናችን አይዞርም። በዚህ ላይ ደግሞ የተኩስ ልምምድ ነው እየተባለ ሌሊት ላይ የሚተኮሰው ተኩስ እንዲሁ ሲያባትተን ያድራል።

በቂ ምግብ፣ ውሃ፣ እና በቂ እንቅልፍ በስለትም ቢሆን የማይገኝበት ቦታ ነው። በላብ የቆሸሸ ገላችንን ስንፎክት ማደሩም ፋታ የሚሰጥ አይደለም።

“ገላ የመታጠብ ወረፋው የሚደርሰን በየአስር ቀኑ ነው”

የመከላከያ ቦቴ መኪኖች ውሃ ይዘው በየሦስት ቀኑ ሮቶ ውስጥ ይገለብጣሉ። በወረፋ ስለምንታጠብ አንድ ሰው ገላውን ለመታጠብ ቢያንስ አስር ቀን መጠበቅ ይኖርበታል። ይህ ካለው ሙቀት ጋር ተደማምሮ ፈታኝ ነበር።

ስንታጠብም ግላዊነትን በጠበቀ መልኩ አይደለም የምንታጠበው። ምግብ ከምንመገብበት በሸራ የተወጠረ ቤት ጀርባ ሜዳ ላይ ነው የምንታጠበው። ይህንን ዕድልም ለማግኘት በትዕግስት መጠባበቅ የግድ ነው። ለብዙዎቻችን ክብርን ዝቅ የሚያደረግ ነበር።

ሥነ ልቦናዊ ጫናው ከባድ ነው።

በየትኛውም አጋጣሚ ስንወጣ እንደምርኮኛ ቁጭ በሉ እየተባልን እንቆጠራለን።

ከዚህ በላይ ከፍተኛ የጤና ችግር ነበር። ከቤተሰብ ጋር አንገናኝም። ስልክ አይፈቀድም። ፌደራል ፖሊስ በወር አንድ ቀን ጠባቂ ሊቀይር ሲመጣ ነው ቤተሰቦቻችን ያስቀመጡልንን ይዘውልን የሚመጡት። ብቻዬን ምደረ በዳ ላይ የቀረሁ ያህል ይሰማኝ ነበር።

በዚህ ላይ የሚደርስብን ዛቻ ቀላል አልነበረም። “መከላከያን ነክታችሁ በሰላም ልትኖሩ ነው?!” እያሉ ይዝቱብን ነበር።

“ጭንቅላትህን አፍርሼ ነው የምሰራልህ” ከሚሉ ማስፈራሪያዎች ጀምሮ መሳሪያ ላያችን ላይ መተኮስ ፣ ብሔር ነክ ስድቦችን መሳደብ የተለመደ ነበር።

“በባዶ አዳራሽ ውስጥ መደገፊያ የሌለው ወንበር ላይ አስቀምጠውኝ ተኙ”

በአዋሽ አርባ ወታደራዊ ካምፕ የእስረኛ ማቆያ ሌላው ፈታኝ ነገር የሌሊት ምርመራ ነው።

ሌሊት ላይ የሚፈልጉትን ሰው ወስደው በተናጠል ይመረምራሉ። ይህ እኔም ላይ ደርሶብኛል። አንድ ቀን በባዶ አዳራሽ ውስጥ መደገፊያ የሌለው ወንበር ላይ አስቀመጡኝ።

ከፋኖ ጋር ያለኝን ግንኙነት ደጋግመው ጠየቁኝ ። “ምንም ግንኙነት የለኝም። ስለምትሉት ነገር የማውቀው ነገር የለም” የሚል ምላሽ ሰጠኋቸው። በመልሴ የተሰላቸው መርማሪው ሌላ ጠባቂ ጠራና ‘እያየኸው!’ ብሎት ተኛ። እዚያ መደገፊያ የሌለው ወንበር ላይ ወገቤ እየተንቀጠቀጠ ሌሊቱ ተገባደደ።

ይህን ምርመራ ለሳምንት ያህል በየቀኑ ሊያደርጉት ይችላሉ። ከዚያ በኋላ ወገብ እንዴት ሊሰራ ይችላል?

ቀን በሙቀት መተኛት አንችልንም። ሌሊት ደግሞ እዚያ ወንበር ላይ አስቀምጠውን ያድራሉ። ይህ በርካታ እስረኞች ያለፉበት እና እያለፉበት ያለ መከራ ነው።

በግቢው ውስጥ ከመጀመሪያ ሕክምና እርዳታ ውጭ የሕክምና አገልግሎት የለም። በጠና ስንታመም ነው ወደ አዲስ አበባ የሚወስዱን።

እኔም በደረሰብኝ ድብደባ ሳብያ ክፉኛ ታምሜ በመሃል አዲስ አበባ መጥቼ ታክሜያለሁ።

የምክር ቤት አባል የሆኑት ታሳሪዎችም በተደጋጋሚ ለህመም ተዳርገው ተመልክቻለሁ።

አቶ ዮሐንስ ቧያለው በሙቀቱ ምክንያት እግራቸው ቆስሎ መራመድ ተስኗቸው ነበር። በሌሎች የጤና እክሎች በተደጋጋሚ ሲታመሙ ብታዘብም፣ በቂ ህክምና ሲደረግላቸው ግን አላየሁም።

“ህመሜ ሲጠና ወደ ፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን መለሱኝ”

በአዋሽ አርባ ወታደራዊ ካምፕ ማቆያ ጣቢያ ከአንድ ወር በላይ ከቆየሁ በኋላ በጤና ምክንያት ወደ አዲስ አበባ ይዘውኝ መጥተው ፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን አሰሩኝ። ከአዋሽ አርባ ሻል ይል ነበር።

ቢያንስ ያስመዘገብነው ጠያቂ በቀን አንዴ እንዲጠይቀን ይፈቀዳል። በዚህ ሁኔታ ለወራት ቆየሁ። ከዚያ በኋላ ከሌሎች እስረኞች ጋር የተሃድሶ ሥልጠና እንድንወስድ ተነገረን።

የተሃድሶ ሥልጠና መውሰድ እንደማንፈልግ ተናገርን። ከብዙ ጭቅጭቅ በኋላ የተሃድሶ ሥልጠናው ‘ውይይት’ የሚል ስም ተሰጠው።

ኮልፌ በሚገኘው ወታደራዊ ካምፕ ለአንድ ሳምንት ያህል ሥልጠና ሰጡን። ሥልጠናው ስለሰላም፣ መንግሥት ለሰላም ስላለው ቁርጠኝነት የሚያነሳ ነበር።

ለመናገር ነጻነት ነበረን። በማሠልጠኛ ማንዋሉ የተጠቀሱ ሃሳቦችን በማንሳት በነጻነት እንከራከር ነበር።

አሠልጣኞቹ ሃሳባችንን ይቀበሉ ነበር። እንዲህ እያልን ሥልጠናው አርብ ዕለት ተጠናቀቀ። ቅዳሜ እና እሑድ እዚያው ቆየን። ሰኞ ከሰዓት በኋላ “ተፈታችኋል፣ ዕቃችሁን ይዛችሁ ወደ ቤታችሁ ሂዱ!” ተባልን።

ያለምንም ክስ፣ ያለምንም ፍርድ ከአራት ወራት በላይ በእስር ከቆየሁ በኋላ ተለቀቅኩ።

አሁን በሕክምና ላይ እገኛለሁ።

‘በሥራ’ ላይ ያለው አዋሽ አርባ

በአማራ ክልል በፋኖ ታጣቂዎች እና በመከላከያ ሠራዊት መካከል የተከሰተውን ግጭት ተከትሎ እንደ አስፈላጊነቱ በመላ አገሪቷ ተግባራዊ የሚሆን ለስድስት ወራት የሚዘልቅ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የታወጀው ሐምሌ 28/2015 ዓ.ም. ነበር።

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ተከትሎ የምክር ቤት አባላትን፣ የተቃዋሚ ፓርቲ አባላትንና አመራሮችን ጨምሮ በርካታ ሰዎችን ለእስር ተዳርገዋል።

ብሔርን መሠረት ያደረጉ የጅምላ እስሮች መዲናዋን ጨምሮ በተለያዩ አካባቢዎች ሲፈፀሙ እንደነበርም የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች በሪፖርቶቻቸው ሲገልጹ ቆይተዋል።

በርካቶች ታስረውባቸው ከሚገኙ ማቆያዎች መካከል ከእስረኞች ጋር በተያያዘ ስሙ ጎልቶ የሚነሳው የአዋሽ አርባ ወታደራዊ ካምፕ አንዱ ነው።

በዚህ ወታደራዊ ካምፕ ውስጥ የሚገኝ ጊዜያዊ ማቆያ ከቀደሙት የአገሪቱ አስተዳደሮች ጀምሮ አሁን ድረስ ተጠርጣሪ ናቸው የተባሉ ሰዎችን ለማሰር ጥቅም ላይ ውሏል።

ባለፉት ጥቂት ዓመታት ውስጥ በተለያዩ ጊዜያት በአገሪቷ ያጋጠሙ ግጭቶች እና ጦርነቶችን ተከትሎ ጋዜጠኞችን ጨምሮ ተጠርጥረው የተያዙ ግለሰቦች ያለምንም ክስ እና ፍርድ በዚሁ ካምፕ ታስረዋል።

በአማራ ክልል ለታወጀው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የተቋቋመው መርማሪ ቦርድ የእስረኞች የሰብዓዊ አያያዝ ጥሩ እንደሆነ በተለያዩ ጊዜያት ቢገልጽም፣ ታስረው የወጡ ግለሰቦች ግን በማቆያዎቹ ከፍተኛ ሰብዓዊ መብት ጥሰት እንደሚፈፀም ይናገራሉ።

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን የምክር ቤት አባላት እና ሌሎች እስረኞችን አዋሽ አርባ በመገኘት መጎብኘቱን በገለጸበት የነሐሴ 27/2015 ዓ.ም. መግለጫው፣ ብዙዎቹ ታሳሪዎች በቁጥጥር ሥር በሚውሉበት ወቅት ብሔር ተኮር ስድብ፣ ማጉላላት፣ ዛቻ እንደደረሰባቸው ገልጸውልኛል ብሏል።    ዘገባው የቢቢሲ ነው፡፡

 

selegna

By selegna

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *