በደቡባዊ ሶማሊያ በምትገኘው ጌዶ ክልል ውስጥ ታጣቂዎች በፈጸሙት ጥቃት ቢያንስ ሰባት ኢትዮጵያውያን ሲገደሉ በርካቶች ስጋት ውስጥ መሆናቸው ተገለጸ።

በሶማሊያ የኢትዮጵያውያን ማኅበረሰብ ተወካይ ለቢቢሲ እንደተናገሩት ሶማሊያ ከኬንያ ጋር በምትዋሰንበት ድንበር አቅራቢያ በምትገኘው በለደሀዎ ከተማ በተፈጸመው ኢትዮጵያውያን ስጋት ላይ እንደሆኑና በርካቶች ወደ አገር ቤት መመለስ ይፈልጋሉ ብለዋል።

ታጣቂዎቹ ሌሊት በጌዶ ክልል በለደሀዎ በተባለ ወረዳ ውስጥ ኢትዮጵያውያኑ ወደ ሚኖሩበት ቤት በመግባት በፈጸሙት ጥቃት ሦስት ሴቶች እና ሦስት ወንዶችን ሲገድሉ አንድ ሶማሊያዊም መገደላቸውን ቢበሲ ሶማሊኛ ዘግቧል።

ለደኅንነቱ በመስጋት ስሙ እንዳይጠቀስ የጠየቀው የማኅብረሰብ መሪ ደግሞ ቅዳሜ ሌሊት ስድስት እንዲሁም እሁድ ሌሊት አንድ በተለያዩ ሥራዎች ላይ የተሰማሩ ኢትዮጵያውያን መገደላቸውን ተናግረዋል።

የበለደሀዎ አስተዳዳሪ አብዲራሺድ አብዲ ግድያው ሌሊት ዘጠኝ ሰዓት መፈጸሙ የታወቀው፣ የአካባቢው የፀጥታ ባልደረቦች የተኩስ ድምጽ ከሰሙ በኋላ ሰባት ሰዎች ተገድለው በማግኘታቸው መሆኑን ጠቅሰው፣ ማቾቹ በአጠቃላይ ለሥራ የመጡ ስደተኞች ናቸው ብለዋል።

“ከተገደሉት መካከል ሁለቱ ሕጻናት ሲሆኑ፣ እናት እና አባቷ ተገድለውባት ብቻዋን የቀረች ሕጻንም አለች” ያሉት የማኅበረሰብ መሪው፣ የተገደሉት ኢትዮጵያውያን ቤተሰቦች መርዶውን እንዳልሰሙ እና እስከ ሰኞ ከሰዓት በኋላ ቀብራቸው አልተፈጸመም ብለዋል።

“የተገደሉት ሰዎች ወደ አገራቸው ተመልሰው በሥነ ሥርዓት ቀብራቸው እንዲፈጸም እንፈልጋለን። መንግሥት ይህን ማድረግ ይችላል። ለተገደሉትም ፍትሕ እንዲሰፍንም እንፈልጋለን።”

በአካባቢው ሆስፒታል ውስጥ የሚሠራ እና ስሙ እንዲገለጽ ያለፈለገ ዶክተር ለቢቢሲ ሶማልኛ እንደተናገረው በጥቃቱ የተገደሉ የስድስት ኢትዮጵያውያን አስከሬን ወደ ሆስፒታሉ መምጣቱን አረጋግጧል። በተጨማሪም ጉዳት የደረሰባቸው ሌሎች ስድስት ሰዎች ሆስፒታል መግባታቸውንም ገልጿል።

ታጣቂዎቹ ወደ ኢትዮጵያውያኑ ቤት ተዘጋጅተው በመሄድ ግድያውን የተፈጸመው ሌሊት ዘጠኝ ሰዓት አካበባቢ መሆኑን ያመለከቱት የማኅበረሰብ መሪው፣ ጥቃቱ በማን እንደተፈጸመ አለመታወቁን አመልክተዋል።

ኢትዮጵያውያኑ በተደጋጋሚ ተፈጽሞብናል በሚሉት ጥቃት እና ባለው ሁኔታ ምክንያት ከፍተኛ ስጋት እንዳለባቸው የሚናገሩት የማኅበረሰብ መሪው “የምንሸሽበት ቦታ የለንም፤ ከተማ ውስጥ አንዳንድ ሶማሊያውያን ስለ እኛ ምን እንደሚሉን እንሰማለን። ስለዚህ ፍርሃት ውስጥ ነን” ብለዋል።

ጥቃቱ በተፈጸመበት አካባቢ ያሉ ሰዎች ለቢቢሲ እንደተናገሩት ታጣቂዎቹ ኢትዮጵያውያኑ ወደ ሚኖሩበት ቤት በሌሊት በመግባት ነው ስድስቱን ኢትዮጵያውያንን እና አንዲት ሶማሊያዊ ሴት የገደሉት።

ኢትዮጵያውያኑ በተደጋጋሚ ተፈጽሞብናል በሚሉት ጥቃት እና ባለው ሁኔታ ምክንያት ከፍተኛ ስጋት እንዳለባቸው

ከዚህ ግድያ ቀደም ብሎ በከተማዋ ውስጥ ኢትዮጵያውያን ላይ አሰቃቂ ግድያ መፈጸሙን የሚናገሩት የማኅበረሰብ መሪው በዚህ ሳቢያ በርካታ ኢትዮጵያውያን ወደ አገራቸው መመለስ እንደሚፈልጉ እና መንግሥትም ሆነ የእርዳታ ድርጅቶች ድጋፍ እንዲያደርጉላቸው ጠይቀዋል።

እስካሁን በኢትዮጵያውያኑ ላይ ከተፈጸመው ጥቃት ጀርባ ማን እንዳለ የታወቀ ነገርም ሆነ ለጥቃቱ ኃላፊነቱን የወሰደ ወገን የለም።

የአካባቢው አስተዳዳሪ እንደሚሉት ግን “ማስረጃዎች እንደሚጠቁሙት ገዳዮቹ የአልሸባብ አሸባሪዎች ናቸው። እስካሁን አልተያዙም። ለምን ስደተኞን ዒላማ አደረጉ ለሚለው ጥያቄ፣ ይህ ግድያ በመላው አገሪቱ ከሚፈጸመው ግድያ የሚለይ አይደለም” በማለት እስላማዊውን ቡድን ተጠያቂ አድርገዋል።

በዜጎቹ ላይ በሶማሊያ ውስጥ የተፈጸመውን ግድያ በተመለከተ የኢትዮጵያ መንግሥት እስካሁን ያለው ነገር የለም።

ከአንድ ወር በፊት በኢትዮጵያ መንግሥት እና ነጻ አገርነቷን ባወጀችው በሶማሊላንድ መካከል የመግባቢያ ሰነድ መፈረሙን ተከትሎ፣ በሶማሊያ እና በኢትዮጵያ መካከል ውዝግብ ከተነሳ በኋላ በሶማሊያ ያሉ ኢትዮጵያውያን ደኅንነታቸው አደጋ ላይ መውደቁን ሲናገሩ ነበር።

ሶማሊላንድ የሉዓላዊ ግዛቴ ናት የምትለው ሶማሊያ፣ ኢትዮጵያ የተፈራረመችው ስምምነትን በማውገዝ ውድቅ እንዲሆን ከመጠየቋ ባሻገር ጉዳዩን ወደ ኢጋድ፣ የአፍሪካ ኅብረት እና የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት መውሰዷ ይታወቃል።

ይህ ሁኔታ በአፍሪካ ቀንድ ላይ ውጥረትን ከመፍጠሩ ባሻገር ወታደራዊ ግጭት እንዳይፈጠር ስጋት አስከትሏል። የሶማሊያ ፖለቲከኞች እና ታዋቂ ሰዎች ተቃውሞ ከማሰማት ባሻገር ወደ ግጭት የሚያመሩ ቁጣ የተሞላባቸው ንግግሮች ሲያደርጉ ነበር።

በዚህም ሳቢያ በሶማሊያ ውስጥ በተለያዩ ምክንያቶች የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ጥቃት እንደደረሰባቸው ባለፉት ሳምንታት መዘገባችን ይታወሳል።     ዘገባው የቢቢሲ ነው፡፡

selegna

By selegna

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *