የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄን (አብን) ወክለው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል የሆኑት ዶ/ር ደሳለኝ ጫኔ በመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች ተይዘው መታሰራቸውን ቤተሰቦቻቸው ተናገሩ።

የምክር ቤት አባሉን ረቡዕ ጥር 22/2016 ዓ.ም. በቁጥጥር ስር ያዋሏቸው አራት የታጠቁ የፀጥታ አካላት መሆናቸውን ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁት የቤተሰብ አባል ለቢቢሲ ተናግረዋል። ከአራቱ መካከልም ሁለቱ የፌደራል ፖሊስን የደንብ ልብስ መልበሳቸውንም አክለዋል።

የዶክተር ደሳለኝ ጫኔ ቤተሰብ አባል የሆኑት ግለሰብ ረቡዕ አመሻሽ የነበረውን ክስተት ለቢቢሲ እንደተናገሩት፣ የፀጥታ ኃይል አባላቱ የምክር ቤት አባሉን የያዟቸው ቴዎድሮስ አደባባይ ከሚገኘው መኖሪያ ቤታቸው ነው።

“በር በተደጋጋሚ ተንኳኳ፤ ማንነታቸውን እንዲገልጹ ስንጠይቅ ፈቃደኛ አልነበሩም፤ በሩ ሲከፈት ደሳለኝን ወደ ሕግ ትፈለጋለህ ብለው ወሰዱት” ሲሉ አስረድተዋል።

ዶ/ር ደሳለኝ ጫኔ ረቡዕ ማታ በቁጥጥር ስር ከዋሉ በኋላ ዛሬ አርብ ረፋድ ላይ በቤታቸው ውስጥ ለሁለት ሰዓታት ገደማ የቆየ ፍትሻ መካሄዱን እኒሁ የቤተሰብ አባል ገልጸዋል። ፍተሻውን ያካሄዱት ስድስት የፌደራል ፖሊስ አባላት ወረቀት፣ ፍላሽ፣ ስልክ እና ታብሌት መውሰዳቸውንም አክለዋል።

የምክር ቤት አባሉ ሜክሲኮ በሚገኘው የፌደራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ክፍል የሚገኙ መሆናቸውን የገለጹት የቤተሰብ አባሉ፣ ለምን በቁጥጥር ስር እንደዋሉ ግን እስካሁን የሚያውቀው ነገር እንደሌለ ገልጸዋል።

ዶ/ር ደሳለኝ ጫኔ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ስብሰባዎች ላይ የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ መንግስት ላይ ጠንካራ ትችት እና አስተያየቶችን በመስጠት ይታወቃሉ። ባለፉት ጥቂት ወራት ውስጥ በተካሄዱ የፓርላማ ስብሰባዎች ላይ ዶ/ር ደሳለኝ አልተገኙም ነበር።

የምክር ቤት አባሉ ባለፈው ዓመት ሐምሌ ወር ላይ በነበረ የምክር ቤቱ ስብሰባ ላይ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ስልጣናቸውን ለጊዜያዊ ሲቪል አስተዳደር እንዲያስረክቡ መጠየቃቸው ይታወሳል። ዶ/ር ደሳለኝ በዚሁ ስብሰባ ላይ የተወካዮች ምክር ቤት አባላትም ፓርላማውን እንዲበትኑ እና “ለአዲስ ምርጫ መንገዱን እንዲጠርጉ” ጠይቀው ነበር።

የሕዝብ እንደራሴው በዚሁ ስብሰባ ላይ በኢትዮጵያ ተስተውሏል ላሉት “ሁለንተናዊ ምስቅልቅል፣ ቀውስ፣ ውድመት እና አገራዊ መክሸፍ” የመንግሥትን እና የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድን “የወደቀ” አመራር ተጠያቂ አድርገዋል።

እንደ ዶ/ር ደሳለኝ ሁሉ ሌላኛው የአብን ተመራጭ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባሉ አቶ ክርስቲያን ታደለም ከስድስት ወራት በፊት በተመሳሳይ በፀጥታ አካላት ተይዘው በእስር ላይ መሆናቸው ይታወቃል።

ዶ/ር ደሳለኝ ጫኔ የአመራር አባል የሆኑበት ፓርቲያቸው የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) ስለመታሰራቸው አስካሁን ያለው ነገር የለም።

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል እና በምክር ቤቱ የመንግሥት ወጪ፣ አስተዳደር እና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ የሆኑት አቶ ክርስቲያን በቁጥጥር ስር የዋሉት ባለፈው ዓመት በአማራ ክልል ከተጣለው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጀ ጋር በተያያዘ መሆኑ ተገልጿል።

አቶ ክርስቲያንም በተመሳሳይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ከሥልጣን እንዲለቁ በምክር ቤቱ በተካሄደ ስብሰባ ላይ ጠይቀዋል።

ሁለቱም የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት በሕገ መንግሥቱ ያለ መከሰስ መብት የተሰጣቸው ሲሆን፣ በቁጥጥር ስር መዋል ካለባቸውም ምክር ቤቱ ያለመከሰስ መብታቸውን ማንሳት ይኖርበታል።

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላትን የሚመለከተው የሕገ መንግሥቱ ድንጋጌ፤ “ማንኛውም የምክር ቤቱ አባል ከባድ ወንጀል ሲፈጽም እጅ ከፍንጅ ካልተያዘ በስተቀር ያለ ምክር ቤቱ ፈቃድ አይያዝም በወንጀልም አይከሰስም” ይላል።   ዘገባው የቢቢሲ ነው፡፡

selegna

By selegna

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *