በአማራ እና በትግራይ ክልሎች የተከሰተው ድርቅ የጉዳት መጠን ላይ ምልከታ ያደረገው የኢትዮጵያ ሕዝብ እንባ ጠባቂ መንግሥት ድርቅ አሊያም ረሃብ መከሰቱን በይፋ ብያኔ እንዲሰጥ ጠየቀ።

የባለሞያዎች ቡድን ወደ ሁለቱ ክልሎች በመላክ ናሙና ወስዶ የችግሩን ስፋት እንዳጣና የገለጸው ተቋሙ፤ በተከሰተው ድርቅ ምክንያት የደረሰ ጉዳት እና የሰብዓዊ እርዳታ አቅርቦት ሁኔታን በመዳሰስ የአሰራር ክፍተቶችን ማግኘቱን አመልክቷል።

የተረጂዎችን ቁጥር መለየትን ጨምሮ በተዋረድ ያሉ የመንግሥት ተቋማት የተለያዩ አሃዞችን ማውጣታቸውን የጠቀሰው እንባ ጠባቂ ተቋም፤ በራሱ ያሰባሰበውን ቁጥር ይፋ አድርጓል።

የትግራይ ክልል ጊዜያዊ መስተዳደር የድርቁን ተጎጂዎች ቁጥር 4.2 ሚሊዮን ቢያደርሰውም፣ የአደጋ ስጋት እና ሥራ አመራር ኮሚሽን ግን 2.2 ሚሊዮን ናቸው ብሏል።

በአማራ ክልልም የተጎጂዎች ልየታ ላይ በክልሉ አደጋ መከላከል እና የምግብ ዋስትና እንዲሁም በዞን እና በወረዳዎች መካከል አለመናበብ ከመኖሩ ባሻገር በድርቅ ምክንያት የሞተ እና የተፈናቀለ ሰው የለም እያሉ መሆናቸውን ጠቅሷል።

ይህ በመሆኑም በትክክል ድጋፍ ለሚያስፈልጋቸው ዜጎች ተገቢውን እርዳታ ማቅረብ እንደማይቻል ዋና እንባ ጠባቂው ዶ/ር እንዳለ ኃይሌ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

“[ተጎጂዎች] በአግባቡ ባልተለዩበት ሁኔታ በተገቢው መንገድ እርዳታ ማቅረብ አይቻልም። ለምሳሌ የፌደራል መንግሥቱ 2.2 ሚሊዮን እያለ፤ የክልሉ መስተዳደር ደግሞ 4.2 ሚሊዮን ናቸው ማለት የ2 ሚሊዮን ክፍተት አለ። ስለዚህ 2 ሚሊዮን በትክክልም እርዳታ ማግኘት እየተገባቸው ላያገኙ ይችላሉ ማለት ነው።

ሁለተኛ በትክክልም አሀዙ 2.2 ሚሊዮን ከሆነ ደግሞ 2 ሚሊዮን ሕዝብ በሌላ አካባቢ ለተቸገሩ መድረስ የሚገባው እርዳታ ለአንድ ክልል ሊሄድ ይችላል” በማለት የተጎጂዎች ቁጥር በትክክል መጣራት እንዳለበት አሳስበዋል።

በድርቅ ምክንያት የተፈናቀሉ ሰዎች በአንድ አካባቢ (መጠለያ ጣቢያ) እንዳይሰባሰቡ በመንግሥት በኩል ተጽዕኖ ይደረጋል የሚሉት ዶ/ር እንዳለ፤ በዚህም ምክንያት ወደ ሕብረተሰቡ እንዲቀላቀሉ እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል።

ትግራይ ክልል

የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ባለፈው ወር በክልሉ የተከሰተው ድርቅ ከ1977ቱ ድርቅ የከፋ ነው ቢልም፣ የፌደራል መንግሥቱ ግን ክልሉ ይህን የማወጅ ሥልጣን የለውም በሚል መግለጫውን “ፈጽሞ ስህተት ነው” ብሎታል።

በትግራይ ክልል ድርቅ ከተከሰተባቸው አራት ዞኖች ውስጥ ሁለት ወረዳዎችን ናሙና ወስዶ ምልከታ ያደረገው የሕዝብ እንባ ጠባቂ ተቋም፤ በድርቅ ሕይወታቸው ያለፈ ሰዎችን፣ የእንስሳት ሞት እና የተፈናቀሉ ሰዎችን በአሃዝ አስደግፎ ይፋ አድርጓል።

ተቋሙ በአበርገሌና ኢስራ ወአዲ ወጅራት ወረዳዎች በተከሰተው ድርቅ ምክንያት 351 ሰዎች መሞታቸውን አረጋግጫለሁ ያለ ሲሆን፣ 15,565 ሰዎች ደግሞ ከወረዳዎቹ ተፈናቅለዋል ያለው ተቋሙ፤ የእንስሳት ሞት እና መፈናቀል እንዲሁም የትምህርት መስተጓጎል ተከስቷል ብሏል።

አማራ ክልል

በአማራ ክልል ባለው ጦርነት ምክንያት የባለሙያዎቹ ቡድን በአካል መሄድ ባይችልም፣ በስልክ አሰባስቦታል በተባለው መረጃ በክልሉ በድርቅ ምክንያት ከ1.8 ሚሊዮን በላይ ሰዎች ለችግር ተጋልጠዋል ብሏል።

በክልሉ 9 ዞኖች በድርቅ ምክንያት 326 ሺህ ሄክታር የሚጠጋ የሰብል ማሳ ሙሉ በሙሉ ከምርት ውጪ ሆኗል ያለው ተቋሙ፤ ከ1.8 ሚሊዮን በላይ ሰዎች ኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበራዊ እና ሥነ-ልቦናዊ ችግሮች እንደተጋለጡ ገልጿል።

የክልሉ መንግሥት በድርቅ ምክንያት የሞተ ሰው የለም ቢልም ተቋሙ ናሙና በወሰደባቸው ሰሜን ጎንደር እና የዋግኽምራ ዞኖች 21 ሰዎች በረሃብ መሞታቸውን አረጋግጫለሁ ብሏል።

በሰሜን ጎንደር በበየዳ ወረዳ በአልሚ ምግብ እጥረት ምክንያት 23 ሕጻናት ሞተው መወለዳቸውንም አስታውቋል።

የክልሉ መንግሥት በድርቁ የተፈናቀሉ ሰዎች የሉም ቢልም የሕዝብ እንባ ጠባቂ ተቋም ግን በሁለት ወረዳዎች በድርቁ ምክንያት ከ31 ሺህ በላይ ሰዎች በላይ ተፈናቅለዋል ብሏል።

የመጠለያ ጣቢያ አያስፈልግም በሚል የክልሉ መንግሥት አቅጣጫ በመስጠቱ ተፈናቃዮችን በተደራጀ መልኩ አገልግሎት እንዳያገኙ አድርጓል ሲልም፤ የዓለም አቀፍ የድርቅ ችግር ተጋላጮችን መብት ተጥሷል ሲል ወቅሷል።

‘ድርቅ ወይስ ረሃብ’

ድርቅ በትግራይ እና በአማራ ክልሎች ብቻም ሳይሆን በሌሎች የአገሪቱ ክልሎችም እንደተከሰተ ተነግሯል።

ችግሩ ክፉኛ በርትቶባቸዋል የተባሉት እና ቀድሞውኑም በሰሜኑ ኢትዮጵያ ጦርነት ጠባሳ ያረፈባቸው ትግራይ እና አማራ ክልሎች፤ በተለይም “ኪስ አካባቢዎች” ያላቸው ስፍራዎች ሊፈተሹ እንደሚገባ ዶ/ር እንዳለ ኃይሌ ተናግረዋል።

ዋና እንባ ጠባቂው በክልሎቹ የተከሰተው ችግር ተቋማቸው ከቃኘው በላይ የከፋ ሊሆን እንደሚችል ስጋት አላቸው።

ለተለያዩ አካባቢዎች ላሉ ተጎጂዎች አስፈላጊውን ድጋፍ በተቀናጀ መልኩ ለማቅረብ በመንግሥት መዋቅር መካከል የተከሰተው “ድርቅ” ወይስ “ረሃብ” በሚለው ብያኔ ላይ ስምምነት እንደሌለ ያመለከተው ተቋሙ በአስቸኳይ ምላሽ እንዲሰጠው ጠይቋል።

ለዚህም የዓለም የምግብ ፕሮግራም ትርጓሜን የጠቀሰው ተቋሙ፤ “ረሃብ” ተብሎ የሚገለጸው ሰዎች በተመጣጠነ ምግብ እጥረት እና በምግብ አቅርቦት እጥረት ምክንያት ከሞቱ፣ የህጻናት የተመጣጠነ ምግብ እጥረት በሽታ በከፍተኛ ሁኔታ ከተስፋፋ ነው ብሏል።

ተቋሙ አክሎም የመንግሥታቱ ድርጅት የረሃብ ትርጓሜን በመጥቀስ እንዳለው፤ የህጻናት ምግብ እጥረት በሽታ ከ30 በመቶ በላይ መሆኑ ሲረጋገጥ ረሃብ እንደሆነ ጠቁሟል።

በመሆኑም ‘ድርቅ ወይስ ረሃብ’ ከሚለው የቃላት ምልልስ በመወጣት ችግሩ የከፋ ጉዳት እንዳያመጣ “ትኩረት ይሰጠው” ሲል ጥሪ አቅርቧል።

ዶ/ር እንዳለ “አንደኛው ረሃብ ነው፤ ሌላኛው ድርቅ ነው እያለ ከሚወዛገብ ግልጽ የሆነ ትርጓሜ በዓለም የምግብ ፕሮግራምም በሌሎች ዓለም አቀፍ ተቋማትም ይሰጣሉ።…ስለዚህ ከዚህ ትርጓሜ ተነስታችሁ ብያኔ ስጡ ብለን ነው ለመንግሥት ሀሳብ ያስቀመጥነው” ብለዋል።

መንግሥት እርዳታ ለማቅረብ እያደረገ ያለውን ጥረት በበጎ የተነሳ ቢሆንም፤ በአቅርቦት እና በፍላጎት መካከል ግን “ከፍተኛ ክፍተት” እንዳለ ዋና እንባ ጠባቂው ገልጸዋል።

በኢትዮጵያ ባለፉት ዓመታት በተካሄደው ጦርነት እና በተከታታይ በተከሰተ የዝናብ እጥረት ምክንያት በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ውስጥ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎች ለችግር መጋላጣቸውን የመንግሥታቱ ድርጅት መግለጹ ይታወቃል።  ዘገባው የቢቢሲ ነው፡፡

selegna

By selegna

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *