በአማራ እና ኦሮሚያ ክልሎች የሚፈጸሙ የድሮን ጥቃቶች “ንፁሃን በሚኖሩባቸው አካባቢዎች ላይ ጉዳት እያደረሱ” መሆኑን የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ ገለጸ።

ኢዜማ፤ የመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች እና ታጣቂዎች “ንጹሃንን የሚጎዳ ወታደራዊ ጥቃት” መፈጸማቸውን እንዲያቆሙም ጠይቋል።

ተቃዋሚው የፖለቲካ ፓርቲ ኢዜማ፤ ይህንን ያለው ወቅታዊ ጉዳዮችን አስመልክቶ ዛሬ ሐሙስ ጥር 16/2016 ዓ.ም. በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ነው።

ፓርቲው በዚህ መግለጫው፤ የዜጎች ደኅንነት፣ የሰብዓዊ እና ዴሞክራሲያዊ መብቶች ይዞታ፣ በትግራይ ክልል የተከሰተው ድርቅና ረሀብን እንዲሁም በአማራ እና በኦሮሚያ ክልሎች የቀጠለውን ጦርነት በተመለከቱ ጉዳዮች ላይ አቋሙን አስታውቋል።

ኢዜማ በትግራይ ክልል የተከሰተውን ድርቅ በተመለከተ የፌደራሉ መንግሥት ተገቢውን እርምጃ አለመውሰዱን በመጥቀስ ወቅሷል።

“የፌደራሉ መንግሥት ለችግሩ እውቅና ሰጥቶ መፍትሔ ከመፈለግ ይልቅ ጉዳዩን ቁጥሮች ላይ የተመሠረተ ፖለቲካ በማድረግ ከክልሉ አስተዳደር ጋር እሰጣ እገባ ጀምሯል” ሲል ይህ አይነቱ ድርጊት “በንጹሃን ሕይወት ላይ የበለጠ አደጋ ሊጋብዝ” እንደሚችል አሳስበቧል።

በአማራ እና በኦሮሚያ ክልሎች እየተደረገ ያለው ጦርነት “ከፍተኛ ዋጋ እያስከፈለ” መሆኑን በዛሬው መግለጫው የጠቀሰው ፓርቲው፤ “በጦርነቱ እየተሳተፉ የሚገኙ አካላት ሳይቀር” ይህንን ጉዳት ይገነዘቡታል ብሎ እንደሚያምን ገልጿል።

በክልሎቹ ባለው ጦርነት ምክንያት የግብርና፣ የትምህርት፣ የንግድ፣ የኢንቨስትመንት እና የቱሪዝም እንቅስቃሴዎች እንደተስገጓጎሉ ጠቅሷል። በክልሉ ውስጥ የሚገኙ ዜጎችም ለችግር መጋለጣቸውን አንስቷል።

ከዚህም ባሻገር በክልሎቹ ውስጥ ከሚካሄደው ጦርነት ጋር በተያያዘ የሚወሰዱ ወታደራዊ ኦፕሬሽኖች “ንጹሃን ዜጎች ሰለባ” እየሆኑ እንደሆነ ኢዜማ በመግለጫው ላይ አስፍሯል።

“ኢዜማ ከዐይን እማኞች በሰበሰበው መረጃ መሠረት በተለይም በድሮን የሚደረጉ የአየር ላይ ጥቃቶች ንፁሃን በሚኖሩባቸው አካባቢዎች ላይ ጉዳት እያደረሱ ናቸው” ሲልም በመንግሥት የሚፈጸሙ የአየር ጥቃቶች እያስከተሉ ናቸው ያለውን ጉዳት አንስቷል።

መንግሥት በአማራ ክልል የሚፈጽማቸው የድሮን ጥቃቶች ጉዳይ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብአዊ መብቶች ቢሮ ኅዳር ወር ላይ ባወጣው መግለጫ በሰላማዊ ሰዎች ላይ ጉዳት መድረሱን ገልጾ ነበር።

የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ ታኅሣሥ ወር ላይ ለመንግሥት ቅርብ ለሆነው ፋና ቴሌቪዥን በሰጡት ቃለ መጠይቅ ይህን ዓይነቱን ክስ፣ የድሮን ጥቃቶች በሕዝብ እና በመኖሪያ አካባቢ ላይ ሠራዊታቸው እንዳማይጠቀም በመግለጽ አስተባብለው ነበር።

ኢዜማ በዛሬው መግለጫው በአማራ እና በኦሮሚያ ክልሎች በንጹሃን ላይ ለሚደርሱ ጥቃቶች ታጣቂ ኃይሎችንም ተጠያቂ አድርጓል።

“ከመንግሥት ጋር የሚፋለሙ ታጣቂዎችም ‘ከተሞችን እንቆጣጠራለን’ በሚል በሚያደርጉት የከተማ ውስጥ ውጊያ በሰው ሕይወት እና ሀብት ላይ ከፍተኛ ጉዳት እየደረሰ ነው” ሲል ፓርቲው ታጣቂዎችን ከሷል።

ፓርቲው አሁን ያለው ሁኔታ “በዚሁ ከቀጠለ ከዚህም የባሱ ለአገር ህልውና አስጊ የሆኑ ቀውሶች መፈጠራቸው የሚቀር አይመስልም። በእነዚህ ጦርነቶች እንደአገር ሁላችንም ከስረናል። ያተረፈም ካለ ኢትዮጵያን በዐይነ ቁራኛ የሚከታተሉ ጠላቶቿ ብቻ ናቸው” ሲል ስጋቱን ገልጿል።

በተጨማሪም ኢዜማ ለዜጎች ሰላም እና ደኅንነት ማጣት መንግሥት እና ታጣቂ ኃይሎችን ተጠያቂ አድርጓል። ባለፉት ኅዳር እና ታኅሣሥ ወራት በኦሮሚያ እና ጋምቤላ ክልል በታጣቂዎች የተፈጸሙ ሰባት ጥቃቶችን በማሳያነት የጠቀሰው ፓርቲው፤ በእነዚህ ጥቃቶች መንግሥት የዜጎችን ደኅንነት ማስጠበቅ አለመቻሉን አመልክቷል።

“በምንም መመዘኛ ቢሆን ንጹሃን ዜጎችን ቤተ እምነት ድረስ ገብቶ መግደል ፖለቲካ ሊሆን አይችልም። እንዲህ አይነቱ ድርጊት ምንም ዓይነት ግብ የማያሳካ የተራ ሽፍታ የጭካኔ ተግባር ነው” በማለት ደግሞ ታጣቂ ኃይሎችን ወቅሷል።

ተቃዋሚው የፖለቲካ ፓርቲ በመግለጫው የመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች እና በትጥቅ ትግል ላይ ያሉ ታጣቂዎች “ንጹሃንን የሚጎዳ ወታደራዊ ጥቃት መፈጸም” እንዲያቆሙ ጠይቋል።

“መከላከያ ሠራዊትን እየወጋችሁ ያላችሁ ታጣቂዎችም የጠመንጃው መንገድ ደጋግሞ አክስሮናልና ጠመንጃችሁን አስቀምጣችሁ ቢያንስ “ቆመንለታል” የምትሉትን ሕዝብ ከገባበት አጠቃላይ ቀውስ ለማውጣት የየበኩላችሁን ድርሻ እንድትወጡ ጥሪ እናቀርባለን” ብሏል።

መንግሥትም “በፀጥታ መዋቅሩ ውስጥ ያለውን ዘርፈ ብዙ እንቅስቃሴ በሚገባ” እንዲመረምር ፓርቲው አሳስቧል። “ጦርነት እንዲቆም ትጥቅ ላነሱ አካላት ሀቀኛ የሆነ ይፋዊ የሰላም ጥሪ” እንዲያቀርብም በመግለጫው ጠይቋል።

በአማራ እና በኦሮሚያ ክልሎች ውስጥ በመንግሥት ኃይሎች እና በታጣቂዎች መካከል የሚካሄደው ግጭት እንደቀጠለ ሲሆን፣ በሰላማዊ ሰዎች ላይ የሚደርሰው ጉዳት እና መፈናቀል እየበረታ መሆኑን በየጊዜው የሚወጡ ሪፖርቶች ያመለክታሉ።

መንግሥት ከታታቂዎች ጋር በመነጋገር ለፀጥታ ችግሩ መፍትሄ ለማግኘት ፍላጎት እንዳለው በተለያዩ ጊዜያት የገለጸ ሲሆን፣ ከተደረጉ ሙከራዎች ባሻገር በሁለቱ ክልሎች ሰላም ለማስፈን ያስቻላ ውጤት አስካሁን አልተገኘም። ዘገባው የቢቢሲ ነው፡፡

selegna

By selegna

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *