ባለፉት ሳምንታት በኢትዮጵያ እና በሶማሊያ መካከል ያለው ውጥረት ተባብሶ፣ በተለይ ሉዓላዊነቴ ተደፍሯል ከምትለው ሶማሊያ መንግሥት በኩል ቀውሱን የሚያባብሱ እና ለጦርነት የመዘጋጀት ጥሪ እየተሰማ ነው።

ረጅም ድንበር በሚጋሩት በሁለቱ ጎረቤት አገራት መካከል ውጥረቱ የተቀሰቀሰው ኢትዮጵያ ሶማሊያ የግዛቴ አካል ናት ከምትላት እረሷ ግን ነጻ አገርነቷን ካወጀች ሦስት አስርት ዓመታትን ካስቆጠረችው ሶማሊላንድ ጋር የመግባቢያ ሠነድ ከፈረመች በኋላ ነው።

ይህ የመግባቢያ ሠነድ ተፈጻሚ ሲሆን፣ ኢትዮጵያ እስከ 20 ኪሎ ሜትር የሚረዝም የባሕር ጠረፍ ስታገኝ፣ በምላሹ ደግሞ ኢትዮጵያ ሶማሊላንድ የአገርነት ዕውቅናን ትሰጣለች ተብሏል።

ከሶማሊያ በተሻለ የተረጋጋች እና ከማዕከላዊው መንግሥት ጋር ግንኙነት የሌላት ሶማሊላንድ እና እንደ አገር ሊያስቆጥራት የሚያስችላት አቋም ቢኖራትም፣ አስካሁን ከየትኛውም አገር እውቅናን ሳታገኝ ቆይታለች።

ስምምነቱ ኢትዮጵያ ከ30 ዓመታት በላይ ከባሕር ርቃ የቆየችበትን ጊዜ በማስቀረት የባሕር በር እና የባሕር ኃይል እንዲኖራት የሚያስችል ሲሆን፣ ሶማሊላንድ ደግሞ ከኢትዮጵያ የአገርነት እውቅናን ካገኘች ሌሎቹም እንዲቀበሏት በር ይከፍትላታል።

ይህ ስምምነት እና የሚያስከትለው ውጤት በእጅጉ ያስቆጣቸው የሶማሊያ መንግሥት ባለሥልጣናት ስምምነቱ “በአገራችን ሉዓላዊነት ላይ የተፈጸመ ጥቃት ነው” ሲሉ ቆይተው ከቀናት በፊት ደግሞ በተለያዩ መድረኮች ላይ ከኢትዮጵያ ጋር ጦርነት ውስጥ ለመገባት ዝግጁ ነን ሲሉ ተደምጠዋል።

የአገሪቱ መገናኛ ብዙኃንም ከ50 ዓመት ገደማ በፊት የዚያድ ባሬ ሠራዊት በኢትዮጵያ ላይ ወረራ ፈጽሞ የተካሄደውን የኢትዮ-ሶማሊያ ጦርነትን የሚያስታውሱ ‘ስሜት ቀስቃሽ’ የሆኑት ሙዚቃዎችን ደግመው ደጋግመው እያጫወቱ ይገኛሉ።

በወቅቱ የሶማሊያ ሠራዊት ባካሄደው ዘመቻ በብዙ ኪሎ ሜትሮች ወደ ኢትዮጵያ ዘልቆ በመግባት ከባድ ጉዳት ያደረሰ ሲሆን፣ ከዚያ በኋላ ግን በወቅቱ የነበረው የኢትዮጵያ ወታደራዊ መንግሥት መላውን ሕዝብ ክተት ጠርቶ በአጭር ጊዜ መቶ ሺህ ወታደሮችን አሠልጥኖ ጥቃቱን መመከት ችሏል።

ወቅቱ ኃያላኑ አሜሪካ እና ሶቪየት ኅብረት በቀዝቃዛው ጦርነት ፍጥጫ ውስጥ ስለነበሩ፣ በጦርነቱ ውስጥ ከኢትዮጵያ እና ከሶማሊያ ጀርባ ሆነው ሲያስታጥቁ እና ሲደግፉ ነበር።

በመጨረሻም በምሥራቁ ዓለም የምትደገፈው ኢትዮጵያ የሶማሊያ ሠራዊትን ከግዛቷ በማስወጣት ጦርነቱ ተቋጭቷል።

አሁን በተፈጠረው ፍጥጫ የሶማሊያው ፕሬዝዳንት እና ጠቅላይ ሚኒስትሩን ጨምሮ ለጦርነት ዝግጁ እንዲሆኑ ወጣቶችን ከመጥራት ባሻገር፣ ከአስርታት በፊት የተካሄደውን ጦርነት በመጥቀስ ቅስቀሳ ሲያደርጉ ተሰምተዋል።

የኢትዮጵያ እና ሶማሊያ ወታደራዊ ደረጃ

በተለያዩ ጦርነቶች ውስጥ የቆዩት ሁለቱ አገራት ተመጣጣኝ ያለሆነ የሠራዊት እና የትጥቅ አቅም እንዳላቸው የአገራትን አቋም ይፋ የሚያደርገው የዓለም አቀፉ ተቋም መረጃ ያመለክታል።

የአገራትን አጠቃላይ ወታደራዊ አቅም በመመዘን ደረጃን የሚሰጠው ግሎባል ፋየር ፓዎር፤ በ2024 ዕትሙ የ145 አገራትን ከሠራዊት ብዛት እስከ ትጥቃቸው ድረስ ወታደራዊ አቅምን ፈትሿል።

በዚህ መሠረት ግሎባል ፋየር ፓወር ኢትዮጵያ ከ145 አገራት 49ኛ ደረጃ ላይ ያስቀመጠ ሲሆን፣ ሶማሊያን 142ኛ ደረጃን ሰጥቷል።

በዚህ ደረጃ መሠረት ኢትዮጵያ እና ሶማሊያ ከአፍሪካ አገራት አንጻር ሲታዩ እጅግ በተራራቀ ደረጃ ላይ ይገኛሉ።

ኢትዮጵያ በወታደራዊ አቅም በአህጉሪቱ ካሉ 54 አገራት መካከል የአምስተኛ ደረጃ ላይ የምትገኝ ሲሆን፣ ከፊቷ የሚገኙት ግብፅ፣ አልጄሪያ፣ ደቡብ አፍሪካ እና ናይጄሪያ ናቸው።

በግሎባል ፋየር ፓወር ደረጃ መሠረት ከሶማሊያ ኋላ የሚከተሉት ሱሪናም፣ ሞልዶቫ እና ቡታን በመሆናቸው በአፍሪካ የመጨረሻው ደረጃ ላይ ትቀመጣላች።

የ145 አገራትን ወታደራዊ አቋም በመመዘን በየዓመቱ ደረጃ የሚያወጣው ግሎባል ፋየር ፓወር፣ ለምዘናው 60 ያህል የመገምገሚያ ነጥቦችን ይጠቀማል።

እነዚህ መመዘኛዎችም አገራት ያሏቸው ወታደራዊ ክፍሎች ብዛት፣ ለሠራዊታቸው የሚመድቡት ዓመታዊ በጀት፣ ለሠራዊታቸው የሚያስፈልጉትን አቅርቦቶች በተገቢው እና በአስፈላጊው ጊዜ በማቅረብ እንዲሁም አገራቱ ካላቸው መልክዓ ምድራዊ አቀማመጥ አንጻር በዝርዝር ተገምግመዋል።

እስኪ የኢትዮጵያን እና የሶማሊያን ሠራዊት የወታደር፣ የመሳሪያ፣ የአቅርቦት እና የበጀት አጠቃላይ መጠንን ለንጽጽር እንመልከት።

የሰው ኃይል

ኢትዮጵያ 116 ሚሊዮን አጠቃላይ ሕዝብ ያላት ሲሆን፣ ከዚህ መካከል ለወታደራዊ ዘመቻ ብቁ የሆነ 34.7 ሚሊዮን ሕዝብ አላት።

በአንጻሩ ሶማሊያ አጠቃላይ የሕዝብ ቁጥሯ 12.6 ሚሊዮን ሲሆን፣ ለወታደራዊ ዘመቻ ብቁ የሆነው የሕዝብ ቁጥሯ 1.7 ሚሊዮን ነው።

እንደ ግሎባል ፋየር ፓወር አሃዝ ከሆነ በአሁኑ ጊዜ የኢትዮጵያ መከላከያ ኃይል 162 ሺህ የሚሆን አጠቃላይ የሠራዊት ብዛት ያለው ሲሆን፣ በአንጻሩ ሶማሊያ የፈጥኖ ደራሽ ኃይሏን ጨምሮ የሠራዊቷ ቁጥር ከ17 ሺህ የሚሻገር አይደለም።

የሠራተኛ ኃይል፣ ፋይንስ እና ሎጂስቲክ

ለረዥም ጊዜ ቀጥሎ በሚካሄድ ጦርነት ውጤት ላይ የአንድ አገር ንቁ ተሳታፊ የሆነ ሠራተኛ ብዛት ትልቅ ሚና ይጫወታል።

ግሎባል ፋየር ፓወር በአገር ውስጥ ሊመረቱ የሚችሉ እና በጦር ሜዳ ውሎ ግብዓት የሚሆኑ እንደ ተተኳሽ፣ የደንብ ልብስ፣ መለዋወጫዎች፣ መድኃኒት፣ ምግብ. . . እና የመሳሰሉትን የሚያመርተው ሠራተኛ ኃይል ወሳኝ ነው ይላል።

ኢትዮጵያን ይህን የመከወን አቅም ያለው 56 ሚሊዮን ሕዝብ እንዳላት የገለጸ ሲሆን፣ በአንጻሩ ሶማሊያ ያላት የሠራተኛ ኃይል ቁጥር 3 ሚሊዮን ገደማ ነው።

በአንድ ወታደራዊ ዘመቻ ውስጥ የፋይናንስ አቅም እና እንደ ነዳጅ ያሉ የሎጂስቲክ አቅርቦቶች ለሠራዊቱ እንቅስቃሴ እና ውጤታማነት መሠረታዊ ናቸው።

ግሎባል ፋየር ፓወር እንደሚያመለክተው ኢትዮጵያ ለጦር ሠራዊቷ ከ888 ሚሊዮን ዶላር በላይ ዓመታዊ በጀት የምትመድብ ሲሆን፣ ሶማሊያ በአንጻሩ ዓመታዊ በጀቷ 458 ሚሊዮን ዶላር አካባቢ ነው።

የኢትዮጵያ ሠራዊት ወታደራዊ ተሸከርካሪዎች፣ ጦር አውሮፕላኖች . . . አጠቃላይ ወታደራዊ ኢንዱስትሪዎች 110 ሺህ በርሜል ድፍድፍ ነዳጅ የሚጠቀሙ ሲሆን፣ የሶማሊያ ጦር ግን የሚፈልገው ዓመታዊ የነዳጅ መጠን ግን 6 ሺህ በርሜል ነው።

የአየር እና ባሕር ኃይል

ግሎባል ፋየር ፓወር እንደሚለው ከሆነ ኢትዮጵያ 91 ወታደራዊ አውሮፕላኖች አሏት። ከእነዚህ መካከል 23 ተዋጊ ጄቶች ናቸው።

በተጨማሪም የጠላትን ዒላማ የሚመቱ እንዲሁም በጦር ሜዳዎች የቅኝት ሥራ የሚያከናውኑ፣ የተጎዱ የሚያነሱ፣ ልዩ ወታደራዊ ግዳጆችን የሚደግፉ እና የመሳሰሉትን የሚሰሩ 37 ሄሊኮፕተሮች አሏት።

የትራንስፖርት አገልግሎት የሚሰጡ እንዲሁም ለሥልጠና የሚውሉ 37 የተለያዩ መጠን ያላቸው አውሮፕላኖችም አሏት።

በዚህ እአአ 2024 በተሻሻለው የግሎባል ፋየር ፓወር ሪፖርት ላይ ባይጠቀስም ኢትዮጵያ ትንሽ የማይባል ቱርክ፣ ቻይና እና ኢራን ሰራሽ ሰው አልባ አውሮፕላኖች (ድሮን) እንዳላት ይታመናል።

በአንጻሩ ሶማሊያ ተዋጊም ሆነ የትራንስፖርት እንዲሁም ለሥልጠና አገልግሎት የሚውሉ ምንም አይነት የጦር አውሮፕላኖች እንደሌላት የግሎባል ፋየር ፓወር ሪፖርት ያሳያል።

በዚህ ሪፖርት ላይ በወታደራዊ አቅም ሶማሊያ ከኢትዮጵያ ተሽላ የተገኘችው በባሕር ኃይል አቅም ነው።

ሶማሊያ እንደ አውሮፕላን ተሸካሚ የመሳሰሉ ገዙፍ መርከቦች ባይኖሯትም፣ በዚህ ሪፖርት ላይ አቅማቸው በግልጽ ያልተጠቀሰ 11 የባሕር ላይ ቅኝት የሚያደርጉ መርከቦች አሏት።

የባሕር በር አልባዋ ነገር ግን ባሕር ኃይሏን መልሳ እየገነባች የምትገኘው ኢትዮጵያ ደግሞ በአሁኑ ወቅት ወታደራዊ ዘመቻን የሚወጡ ምንም አይነት የባሕር ኃይል መርከቦች የሏትም።

ሲያድ ባሬ የገነቡት የሶማሊያ ጦር ከኢትዮ-ሶማሊያ ጦርነት በኋላ እንዲሁም የአገሪቱ ማዕከላዊ መንግሥት ከወደቀ በኋላ የመንግሥቱ ሠራዊት ፈርሶ መቆየቱ ይታወቃል።   ዘገባው የቢቢሲ ነው፡፡

selegna

By selegna

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *