የስፖርት እና የታሪክ አዋቂው ታዋቂው ጋዜጠኛ ገነነ መኩሪያ አሊያም በቅፅል ስሙ ሊብሮ ከዚህ ዓለም በሞት ተለየ።

ስመ ጥሩ ጋዜጠኛ ባደረበት ሕመም ምክንያት በሕክምና ሲረዳ ቆይቶ ማክሰኞ ጥር 14/2016 ከዚህ ዓለም በሞት መለየቱ ተሰምቷል።

ገነነ መኩሪያ ይሠራበት የነበረው ‘አሻም’ የተሰኘው የቴሌቪዥን ጣቢያ የጋዜጠኛውን ሕልፈተ-ሕይወት በፌስቡክ ገፁ አረጋግጧል።

አንጋፋው ጋዜጠኛ ገነነ መኩሪያ (ሊብሮ) በአሻም ቴሌቪዥን “የገነነ” እና “ጥቁር እንግዳ” የተሰኙ ፕሮግራሞችን አዘጋጅ እና አቅራቢ ሆኖ እንዳገለገለ ጣቢያው ገልጧል።

ጋዜጠኛ ገነነ መኩሪያ ለበርካታ ዓመታት ለተለያዩ የአገር ውስጥ መገናኛ ብዙኃን ተወዳጅ የሆኑ ዝግጅቶችን በማቅረብ ሠርቷል።

ገነነ መኩሪያ እግር ኳስ እና ፖለቲካን እንዲሁም ታሪክን የሚዳስሱ በርካታ መጽሐፎችን ያሳተመ ሲሆን፣ “ኢሕአፓ እና ስፖርት” እና ሌሎች መፃሕፍትን ለአንባቢ አቅርቧል።

ሊብሮ ከስፖርት ጋዜጠኝነት ሕይወት ባሻገር በወጣትነት ዘመኑ ለበርካታ የእግር ኳስ ክለቦች በመሠለፍ ተጫውቷል።

የመንግሥት ባለሥልጣናትን ጨምሮ የሙያ ባልደረቦቹ እና ታዋቂ ሰዎች በሊብሮ ሕልፈተ ሕይወት ሐዘናቸውን እየገለጡ ነው።

ገነነ ከ30 ዓመታት በላይ በስፖርት ጋዜጠኝነት ሙያው አስተዋጽኦ ያበረከተ ሲሆን በጋዜጣ፣ በሬዲዮ እና በቴሌቪዥን እንዲሁም በማኅበራዊ ሚዲያዎች ላይ ሥራውን በማቅረብ ተወዳጅነትን አትርፏል።

ገነነ መኩሪያ በዘመናት የዳበረ የስፖርት፣ የፖለቲካ፣ የሙዚቃ እና የማኅበራዊ ጉዳይ ታሪኮችን በጥልቀት እና በዝርዝር የሚያውቅ ሲሆን፣ በስፖርት እና በፖለቲካ ዙሪያ የሚያጠነጥኑ መጽሐፍትን አሳትሞ ለንባብ አብቅቷል።

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን እንዳለው ገነነ መኩሪያ ለእግር ኳስ ስፖርት ላበረከተው ታላቅ አስተዋፅኦም በአዲስ አበባ ተሰናድቶ በነበረው የካፍ ኮንግረስ ላይ የረጅም ዘመን አግልግሎት ሜዳይ ተበርክቶለታል።

ሊብሮ

ግብ ጠባቂ ሆኖ ተጫውቷል። ተከላካይም ነበር። አማካይ ሆኖ ተጫውቷል። አጥቂም እንዲሁ።

የሚወደው ቦታ ግን የተከላካይ አማካይ ነው።

የተወለደው ይርጋለም ነው። ያደገው ሻሸመኔ። እግር ኳስ የጀመረው እዚያ ነው። ለሻሸመኔ አውራ ጎዳና ከግብጥ ጠባቂ እስከ አጥቂ መስመር ተሰልፎ ተጫውቷል።

ከአውራ ጎዳና ወደ ሜታ ቢራ ክለብ ተዘዋውሮ ጓዙን ጠቅልሎ አዲስ አበባ ገባ።

ሊብሮ የሚለው ስም የወጣለት ይህን ጊዜ ነው። የቅዱስ ጊዮርጊሱ ኃይሌ ካሤ እና የሜታ ቢራው ገነነ ከነበራቸው ግጥሚያ በፊት ሲያወጉ ገነነ “ሊብሮ” ስሚባለው የእግር ኳስ ጥበብ ይተነትናል።

የጨዋታው ሰዓት ደርሶ ገነነ “ሊብሮ” የተሰኘውን ጥበብ ተጠቅሞ ከተከላካይ መስመር ተነስቶ ግብ ያስቆጥራል።

ከዚህ ቀን በኋላ የገነነ ቅፅል ስሙ “ሊብሮ” ሆኖ ቀሮ። የእሱ መጠሪያ ብቻ ሳይሆን የጋዜጣው መለያም ነበር።

ሊብሮ የስፖርት ጋዜጣ ገነነ መኩሪያ በብድር የጀመራት ለ13 ዓመታት ያክል የዘለቀች በጊዜው ተወዳጅ የስፖርት ወሬ ምንጭ ነበረች።

ገነነ፤ ሊብሮ ብቻ ሳትሆን እነ ሻምፒዮን፣ ማራካኛ፣ ፉትቦል እና ሌሎችም ጋዜጦችን በግል እና ከሙያ አጋሮቹ ጋር በትብብር ሠርቷል።

ሻሸመኔ ገና ታዳጊ ሳለ ጭምር ጋዜጣ ማንበብ ብቻ ሳይሆን፣ መሸጥም ይወድ የነበረው ገነነ ከእግር ኳስ ወደ ጋዜጠኝነት ያደረገው ሽግግር ከባድ አልነበረም።

ከሜታ ቢራ ወደ መብራት ኃይል ተሸጋግሮ ኳስ እየተጫወተ፣ በቀሪ ጊዜ መካኒክ ሆኖ ኑሮውን እየደጎመ ሳለ ነው ጽሑፎቹን ለጋዜጣ መላክ የጀመረው።

ገነነ መኩሪያ ለሥነ-ጽሑፍ ያለው ፍቅር በጋዜጣ ብቻ የተገታ አይደለም። በጣም በርካታ መጽሐፍትም ለሕትመት አብቅቷል።

ኢሕአፓ እና ስፖርት፣ ፍትሐዊ የጠጅ ክፍፍል፣ መኩሪያ. . . ጥቂቶቹ ናቸው።

ገነነ መኩሪያ የጋዜጣ ሥራውን ትቶ ወደ ኤሌክትሮኒክ ሚድያ ካመራ በኋላም ለበርካታ የአገራችን የሬድዮ እና የቴሌቪዥን ጣቢያዎችም አገልግሏል።

ዛሚ ኤፍኤም፣ ኤፍኤም አዲስ፣ እንዲሁም በብስራት ኤፍ ኤም ላይ ሥራውን እና ዕውቀቱን ለአድማጮች አቅርቧል። ከህልፈቱ በፊት አሻም በተሰኘው የቴሌቪዥን ጣቢያ የተለያዩ ታሪክ እና ስፖርትን ያቀናጁ ፕሮግራሞችን አዘጋጅቶ በማቅረብ ለታዳሚያን ሲያቀርብ ቆይቷል።

ሊብሮ በተለይ በ1960ዎቹ እና 70ዎቹ የተከወኑ ታሪኮችን ቀን እና ሰዓታቸውን፣ ወር እና ዓመተ ምህረታቸውን ሳያጓድል፣ የሰዎችን ስም ሳይዘነጋ ታዳሚ በሥፍራው ያለ አስኪሰማው አድርጎ በማቅረብ ብቃቱ በብዙዎች ዘንድ ይወሳል።

2009 የአፍሪካ እግር ኳስ አስተዳዳሪ ካፍ አዲስ አበባ ላይ በነበረው ስብሰባ ወርቃማውን ‘ካፍ ኦርደር ኦፍ ሜሪት’ የተሰኘ ሽልማት ካበረከታቸው ስድስት ጋዜጠኞች መካከል አንዱ ገነነ መኩሪያ ነበር።   ዘገባው የቢቢሲ ነው፡፡

selegna

By selegna

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *