ፕሬዝዳንት አብድል ፋታህ አል-ሲሲ አገራቸው ግብጽ በሶማሊያም ሆነ በጸጥታዋ ላይ ምንም አይነት የደኅንነት ስጋት እንዲፈጠር አትፈቅድም ሲሉ ተናገሩ።

ፕሬዝዳንቱ ትናንት ከሶማሊያው አቻቸው ጋር በሁለትዮሽ ጉዳዮች ከተነጋገሩ በኋላ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ግብፅ ጣልቃ እንድትገባ ከተጠየቀች ከሶማሊያ ጎን ትሰለፋለች ብልዋል።

ፕሬዝዳንቱ ይህን ያሉት ኢትዮጵያ የባሕር በር ያስገኝላታል የተባለው የመግባቢያ ሠነድ ከራስ ገዟ ሶማሊላንድ ጋር ከተፈራረመች በኋላ ነው።

አል-ሲሲ ኢትዮጵያ ላይ ያነጣጠረውን አስተያየት ከሰጡ በኋላ የጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አሕመድ የብሔራዊ ደኅንነት አማካሪ አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን ስምምነቱ በሶማሊያ ላይ የደኅንነት ስጋት የሚፈጥር አለመሆኑን ገልጸው፤ በቀጠናው ያሉ አንዳንድ ኃይሎች አጀንዳ በአፍሪካ ቀንድ ቀውስ መፍጠር ነው ብለዋል።

ከሦስት ሳምንታት በፊት ይፋ በተደረገው የኢትዮጵያ እና ሶማሊላንድ ስምምነት መሠረት ኢትዮጵያ ከሶማሊላንድ ለምታገኘው የባሕር ጠረፍ፤ በምላሹም ሶማሊያ እንደ አንድ ግዛቷ ለምትመለከታት ሶማሊላንድ የአገርነት ዕውቅናን ትሰጣለች ተብሏል።

ይህ ታዲያ ሶማሊያን በእጅጉ ያስቆጣ ሲሆን፣ በሉዓላዊነቷ ላይ የተፈጸመ ጥቃት መሆኑን በመግለጽ ስምምነቱን አጥብቃ ተቃውማለች።

ከስምምነቱ መፈረም በኋላ የሶማሊያው ፕሬዝዳንት በቀጣናው ከሚገኙ መሪዎች ጋር በስልክ ከመነጋገር ባለፈ ወደ ካይሮ እና አሥመራ ጉዞዎችን አድርገዋል።

“ግብጽን አትሞክሯት . . . “

ፕሬዝዳንት ሐሰን ሼክ ሞሐሙድ ከአል-ሲሲ በቀረበላቸው ግብዣ ወደ ካይሮ ካቀኑ በኋላ ከፕሬዝዳንት አል-ሲሲ ጋር በሁለትዮሽ ጉዳዮች እና በቀጠናዊ የጸጥታ ጉዳዮች ላይ ማውራታቸውን የግብጽ ፕሬዝዳንት ጽ/ቤት አስታውቋል።

መሪዎቹ በጋራ በሰጡት መግለጫ ላይ ፕሬዝዳንት አል-ሲሲ “ግብጽ የትኛውም አገር ሶማሊያንም ሆነ ደኅንነቷን ስጋት ውስጥ እንዲጥል አትፈቅድም” ካሉ በኋላ “ግብጽን አትሞክሯት፤ በተለይ ደግሞ ወንድም አገር ጣልቃ እንድንገባ ሲጠይቀን” ሲሉም ተደምጠዋል።

ግብጽ ከኢትዮጵያ ጋር ውዝግብ ውስጥ ከገባችው ሶማሊያ ጎን እንደምትቆም ስትገልጽ ይህ ለመጀመሪያ ጊዜ ባይሆንም በካይሮ በኩል ኢትዮጵያ ላይ ያነጣጠረ ዛቻ አዘል ጠንካራ አስተያየት ሲሰማ ይህ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው።

በአባይ ወንዝ ላይ እየተገነባ ባለው የሕዳሴ ግድብ ከአዲስ አበባ ጋር የሻከረ ግንኙነት ያላት ካይሮ፤ ከጥቂት ሳምንታት በፊት የመግባቢያ ሠነዱ መፈረሙን ተከትሎ “ከሶማሊያ ጎን ለመቆም ያላትን ጠንካራ አቋም” ገልጻ ነበር።

ፕሬዝዳንት አል-ሲሲ ትናንት በሰጡት መግለጫ ኢትዮጵያ ከሶማሊላንድ ጋር የደረሰችውን ስምምነት “ግዛትን በኃይል የመቆጣጠር ሙከራ” ብለው ከገለጹ በኋላ፤ “ለኢትዮጵያ ያለኝ መልዕክት . . . መሬትን ለመቆጣጠር መሞከር ማንም የማይስማማ ነው” ብለዋል።

አል-ሲሲ ሶማሊያ የአረብ ሊግ አባል አገር መሆኗን አስታውሰው በሊጉ ቻርተር መሠረት ሶማሊያ ሊገጥማት ከሚችለው የደኅንነት ስጋት የመጠበቅ መብት አላት ሲሉም ተናግረዋል።

“የትኛውም አገር በሶማሊያን ደኅንነት ላይ ስጋት እንዲደቅን ወይም ግዛቷን እንዲጥስ አንፈቅድም። በግልጽ የምናገረው ነገር፣ የግብጽ ወንድም አገርን ማንም መዳፈር የለበትም፤ በተለይ ደግሞ ወንድሞቻችን ከጎናቻው እንድንሰለፍ ሲጠይቁን” ብለዋል ፕሬዝዳንት አል-ሲሲ።

የአል-ሲሲ አስተያየትን ተከትሎ የጠቅላይ ሚንስትሩ የብሔራዊ ደኅንንት አማካሪ አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን ኢትዮጵያ በሶማሊያ ላይ የደኅንነት ስጋት የምትደቅን አገር ሳትሆን ለሶማሊያ ጥበቃ ለማድረግ ወታደሮቿን ማሰማራቷን አስታውሰዋል።

ሁለቱ አገራት ከጉርብትናቸው በላይ አንድ ቋንቋ እና ባሕል የሚጋሩ ሕዝቦች እንዷላቸው አስታውሰው፤ “እውነቱ ይህ ሆኖ ሳለ በችግሯ ጊዜ ለሶማሊያ ድጋፍ ሳያደርጉ የቆዩ አንዳንድ ኃይሎች እራሳቸውን እውነተኛ ወዳጅ አድርገው ለማሳየት እየሞከሩ ነው” ብለዋል።

“የሚያነሳሳቸው ከሶማሊያ ጋር ያላቸው ወዳጅነት ሳይሆን ለኢትዮጵያ ያላቸው ጥላቻ እንደሆነ ግልጽ ነው” ብለዋል አምባሳደር ሬድዋን በኤክስ ገጻቸው።

አምባሳደር ሬደዋን በቀጠናው ያሉ አንዳንድ ኃይሎች አጀንዳ በአፍሪካ ቀንድ ቀውስ መፍጠር ነው ካሉ በኋላ ኢትዮጵያ ውጥረት ከሚያባብሱ መግለጫዎች እና ንግግሮች ይልቅ ቀጣይነት ያለው ንግግር ጠቃሚ ነው ብላ ታምናለች ብለዋል።  ዘገባው የቢቢሲ ነው፡፡

selegna

By selegna

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *