የቀድሞዎቹ የመገናኛና ኢንፎርሜሽን ሚኒስቴር እና የሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ተዋህደው፣ ‹‹የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር›› ሲፈጠር፣ በመገናኛና ኢንፎርሜሽን ሚኒስቴር አማካይነት መሰብሰብ የነበረበት 500 ሚሊዮን ብር ባለቤት የሌለው ዕዳ እንዲሰረዝለት፣ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ጥያቄ አቀረበ፡፡

የተጠቀሰውን መጠን ገንዘብ ለማወራረድ ምንም ዓይነት መረጃ የለኝም ያለው የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር፣ ዕዳው እንዲሰረዝለት የጠየቀው፣ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግሥት ወጪ አስተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ፣ የኢኖቬሽን ቴክኖሎጂ ሚኒስቴርን 2014 በጀት ዓመት የፋይናንስ ኦዲት ሪፖርት ላይ ሰኞ ጥር 6 ቀን 2016 ዓ.ም. ውይይት ባካሄደበት ወቅት ነው፡፡

ሁለቱ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶች በ2012 ዓ.ም. ሲዋሀዱ ዕዳው ተላላፊ እንጂ ምንም ዓይነት ማስረጃ አለመቀበላቸውን፣ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ደኤታ ይሽሩን ዓለማየሁ (ዶ/ር) አስረድተዋል፡፡

ከተለያዩ ድርጅቶች መሰብሰብ የሚገባውና በተለያዩ የሒሳብ መደቦች በተሰብሳቢ ሒሳብ ሪፖርት የተመላከተ፣ ነገር ግን ከማን እንደሚሰበሰብ የማይታወቅና ማስረጃ የሌለው በርካታ ገንዘብ መኖሩን ገልጸዋል፡፡ በተጨማሪም ገንዘቡ በቀጥታ የሚመለከታቸው ግለሰቦች በአገር ውስጥ ባለመኖር፣ በሞት መለየትና አሁን ያሉበት አለመታወቅ ምክንያት ሚኒስቴሩ ገንዘቡን መሰብሰብ እንደማይችል፣ ነገር ግን በአገር ውስጥ ያሉትን በሕግ ተጠያቂ ለማድረግ እየተሠራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ሁለቱ ሚኒስቴሮች ውህደት አካሂደው አዲሱ ሚኒስቴር ሲቋቋም ንብረቶቻቸውን ብቻ ሳይሆን ዕዳቸውንም እንዲወስድ ተወስኖበት እንደነበር፣ ከአጠቃላይ ተሰብሳቢ ከ700 ሚሊዮን ብር ወደ 500 ሚሊዮን ብር እንዲወርድ ማድረጉን ሚኒስቴር ደኤታው አስረድተዋል፡፡

ሚኒስቴሩ ይህንን የተከማቸ ተሰብሳቢ ገንዘብ በተመለከተ በተከታታይ ለዋና ኦዲተርና ለገንዘብ ሚኒስቴር ማቅረቡን የገለጹት ይሽሩን (ዶ/ር)፣ አሁን ጉዳዩ የመንግሥትን ውሳኔ የሚሻ በመሆኑ ለጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ማሳወቁን አስታውቀዋል፡፡ ችግሩ ከተቋሙ አቅም በላይ መሆኑንና አንዳንዱ የገንዘብ ዝርዝር ምንም ዓይነት ማስረጃ የሌለው በመሆኑ፣ ጉዳዩ ትኩረት ተሰጥቶበት ዕርምጃ እንዲወሰድበት የጠየቁት ሚኒስትር ደኤታው፣ ይህ ካልሆነ ግን በየዓመቱ ገንዘቡ በኦዲት ክፍተት እየተጠቀሰ ይቀጥላል ብለዋል፡፡

የገንዘብ ሚኒስቴር ኢንስፔክሽን ዳይሬክተር ወ/ሮ ዓባይነሽ ተሾመ ስለጉዳዩ በሰጡት አስተያየት፣ በታኅሳስ 2016 ዓ.ም. የሚኒስቴሩ አጠቃላይ ተሰብሳቢ ሒሳብ 501 ሚሊዮን ብር መድረሱን አስታውሰው ይህ የሚያመላክተው ተሰብሳቢ ሒሳቡ ‹‹በጣም እየጨመረ ነው፤›› ብለዋል፡፡

የተቋሙ የሥራ ኃላፊዎች የተሰብሳቢ ሒሳቡ ከቀድሞው መገናኛና ኢንፎርሜሽን ሚኒስቴር የመጣ ነው ቢሉም፣ የገንዘብ መጠኑ አሁንም እየጨመረ በመሆኑ ተቋማዊ ቁመናው እንዲፈተሽ አሳስበዋል፡፡

የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ፓርላማው ዕገዛ እንዲያደርግለት የጠየቀ ሲሆን፣ የገንዘብ ሚኒስቴር ዕዳውን እንዲሰርዝለትና የመጨረሻ መፍትሔ ለማግኘት እየተጠባበቀ መሆኑን ሚኒስትር ደኤታው ተናግረዋል፡፡ ይሁን እንጂ በዕዳው መጠየቅ ያለባቸው ሰዎችም ሆኑ ሰነዶች ካሉ ይፈለጉ ተብሎ መሞከሩን ጠቅሰው በሕይወት የሌሉ፣ ከአገር የወጡና በአገር ውስጥ የተለያዩ አካባቢዎች የሚገኙ ግለሰቦች በመኖራቸው ጉዳዩን የሕግ ክፍል ይከታተለዋል ብለዋል፡፡

የፌዴራል ዋና ኦዲተር ወ/ሮ መሠረት ዳምጤ በበኩላቸው፣ ተቋማት በሚዋሀዱበትና በሚለያዩበት ጊዜ ኦዲት ተደርጎና ንብረቱ በአግባቡ ተመዝግቦ ለሚተላለፍለት መሥሪያ ቤት በሕግና በሥርዓት መተላለፍ እንዳለበት ገልጸዋል፡፡

ለዚህም ይረዳ ዘንድ ከዚህ ቀደም ሁለቱ ተቋማት ተዋህደው አንድ ሚኒስቴር ከመፍጠራቸው በፊት፣ ከፕላንና ልማት ሚኒስትሯ ጋር ባደረጉት ውይይት እነዚህ ተቋማት ሲለያዩ ኦዲት ተደርገው፣ ተቋማዊ ቁመናቸው ታይቶና ተጠንቶ እንዲዋሀዱ የሚል ምክክር ማድረጋቸውን አስታውሰዋል፡፡

‹‹ይሁን እንጂ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ይህን ለምን እንዳላደረገ ግልጽ አይደለም፤›› ብለዋል፡፡ በቀጣይም ቢሆን መሰል ችግሮች ማጋጠማቸው የማይቀር በመሆኑ ሰዎች ሲለቁ ሥራዎች አብረው ከሰዎች ጋር መሄድ እንደሌለባቸው አሳስበው ሲስተምና ሥርዓት ሊዘረጋ እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡

‹‹ሥራችን ሰው ተኮር ባይሆንና ተቋማዊ ቢሆን ሰው በተቀያየረ ቁጥር ሥራ አዲስ እየሆነ እንደገና መጀመር የለበትም፤›› ብለዋል፡፡

የቋሚ ኮሚቴው ምክትል ሰብሳቢ ወ/ሮ አራሬ ሞሲሳ፣ ‹‹ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ምክር ቤት መጥቶ የሚናገረውና የምክር ቤት አባላት በመስክ ምልከታ ወርደው ሲመለከቱት የማይገናኝ ነገር እንደሚያቀርብ›› ገልጸው፣ ‹‹ሥራ መሥራት ቀርቶ አዳራሽ ውስጥ ያቀረቡትን ማስረጃ አምጡ ተብለው ሲጠየቁ እንኳ ማቅረብ አይችሉም፤›› ብለዋል፡፡ ‹‹እዚህ ላይ ባልናገር ይመረጣል፣ ጥሩ አይደለም፣ ለመናገር የሚከብዱ አሠራሮች አሉ፡፡ ያለፉት ትሩፋቶች፣ አደጋዎችም ይሁኑ ጉደለቶች የአሁኑ አመራር ሸክም ናቸው፡፡ አመራሮች እዚህ ቦታ የተቀመጣችሁት ያንን ሸክም ለማንሳት ነው፡፡ ለማንም አሳልፈን የምንሰጠው አይደለም፡፡ ያለፉት አመራሮች ያጠፉም ቢሆኑ የእኛው ናቸው፡፡ የኢትዮጵያ ዜጋ ናቸው፡፡ አሁንም እየመራን ያለነው እኛው ነን፡፡ በማንም ላይ ጣታችንን የምንቀስርበት አግባብ የለም፡፡ እንድታስተታክሉ ነው እዚያ የተቀመጣችሁት፡፡ ትናንት የሆነ ሰው አጥፍቷል፣ አዎ ሊያጠፋ ይችላል፡፡ ትናንት ለጠፋው ትናንት ያጠፉትን ሰዎች ብቻ የምንወቅስ ከሆነ፣ ዛሬ እኛ ምን ሠራን? ምን አስተካከልን? ወቃሾች ብቻ ሆነን እንዳንቀር እፈራለሁ፤›› ሲሉ ተናግረዋል፡፡

‹‹አመራር በመጣና በሄደ ቁጥር አመራር የምንወቅስ ሆነን እንዳንቀር እፈራለሁ፣ እኔ ምን አስተካከልኩ በአመራርነቴ ምን ሠራሁ ልንል ይገባል፤›› ብለዋል፡     ዘገባው የቢቢሲ ነው፡፡

selegna

By selegna

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *