ኢትዮጵያ ከሶማሊላንድ ጋር የተፈራረመችውን የመግባቢያ ስምምነት እስካላነሳች እና ለሶማሊያ የግዛት አንድነት ማረጋገጫ እስካልሰጠች ድረስ ከአዲስ አበባ ጋር ለሚደረግ ሽምግልና “ቦታ እንደሌላት” ሶማሊያ አስታወቀች።

ሶማሊያ ይህንን አቋሟን ያሳወቀችው የአፍሪካ ኅብረት የሰላም እና የፀጥታ ምክር ቤት ትላንት ረቡዕ ካደረገው ስብሰባ በኋላ ሁለቱ አገራት “ትርጉም ያለው ንግግር” በማድረግ ችግራቸውን እንዲፈቱ መጠየቁን ተከትሎ ዛሬ ሐሙስ ጥር 9/2016 ዓ.ም. ባወጣችው መግለጫ ነው።

ኢትዮጵያ እና ሶማሊላንድ ታኅሣሥ 22/2016 ዓ.ም. በመሪዎቻቸው መካከል በተፈራረሙት የመግባቢያ ሰነድ መሠረት ኢትዮጵያ ነጻ አገር መሆኗን ላወጀችው ሶማሊላንድ ዕውቅናን ለመስጠት፣ ሶማሊላንድ በበኩሏ ደግሞ ለኢትዮጵያ የባሕር በር ለመፍቀድ ስምምነት ደርሰዋል።

ይህም ሶማሊላንድን የግዛቱ አንድ አንድ አካል እንደሆነች የሚገልጸው የሶማሊያ መንግሥት ስምምነቱን አጥብቆ በመቃወም፣ የአገሪቱን ሉዓላዊነት የሚጥስ ድርጊት ነው በማለት በአካባቢው ውጥረት እንዲፈጠር አድርጓል።

የሰላም እና የፀጥታ ምክር ቤቱ በውይይቱ ኢትዮጵያ እና የሰሜን ሶማሊያ ግዛት (ሶማሊላንድ) የመግባቢያ ስምምነት ከተፈራረሙ በኋላ በአዲስ አበባ እና በሞቃዲሾ መካከል የተፈጠረው ውጥረት እንዳሳሰበው አስታውቋል።

ምክር ቤቱ ከውይይቱ በኋላ ባወጣው መግለጫ የሶማሊያ እና የኢትዮጵያን ጨምሮ የሁሉም የኅብረቱ አባል አገራት “ሉዓላዊነት፣ የግዛት አንድነት እና ነጻነት” እንዲጠበቅ “ጠንካራ ቁርጠኝነት እና ድጋፍ” እንዳለው አስታውቋል።

የኢትዮጵያ እና የሶማሊያ ተወካዮች በተገኙበት ውይይቱን ያካሄደው ምክር ቤቱ፤ ሁለቱ አገራት የተፈጠረው ውጥረት ግንኙነታቸውን ሊያበላሽ ከሚችሉ ተጨማሪ ድርጊቶችን ከመፈጸም እና እርምጃዎችን ይፋ ከማድረግ እንዲቆጠቡ ጠይቋል።

ምክር ቤቱ በመግለጫው፤ ኢትዮጵያ እና ሶማሊያ ለጉዳዩ ሰላማዊ መፍትሄ ለመስጠት ሲባል ትርጉም ያለው ንግግር እንዲያደርጉም ጠይቋል።

የቀድሞው የናይጄሪያ ፕሬዝዳንት ኦሉሴጉን ኦባሳንጆ በሁለቱ አገራት መካከል ንግግር እንዲያመቻቹ በአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር መሾማቸውን ኮሚሽኑ እንደሚቀበለውም በመግለጫው ላይ ሰፍሯል።

የአፍሪካ ኅብረት የሰላም እና የፀጥታ ምክር ቤት ውይይትን አስመልክታ ዛሬ መግለጫ ያወጣችው የሶማሊያ ምክር ቤቱ ኅብረቱ ለሁሉም አባል አገራት “ሉዓላዊነት እና የግዛት አንድነት” ማረጋገጫ መስጠቱን እንደሚቀበለው ገልጿል።

“ይህንን መርኅ ከመደገፍ አኳያ፤ ኢትዮጵያ ከሰሜን ሶማሊያ ግዛት (ሶማሊላንድ) ጋር ሕገወጡን የመግባቢያ ስምምነት ስትፈራረም የሶማሊያ ሉዓላዊነት እና የግዛት አንድነት ተጥሷል” ስትል ኅብረቱ የሚደግፈው መርኅ መጣሱን ገልጻለች። “በተቃራኒው ሶማሊያ እነዚህን የተከበሩ መርሆዎች አልጣሰችም” ስትል ጥፋት የተፈጸመው በኢትዮጵያ ነው የሚል አቋሟን አንጸባርቃለች።

ሶማሊያ በመግለጫዋ፤ “በዚህም ምክንያት ኢትዮጵያ የፈረመችውን የመግባቢያ ስምምነት እስካላነሳች እና የሶማሊያን የግዛት አንድነት እስካላረጋገጠች ድረስ ለሽምግልና የሚሆን ቦታ የለም” ስትል የኅብረቱ የፀጥታ ምክር ቤት ሁለቱ አገራት እንዲያደርጉ ለጠየቀው ንግግር ቅድመ ሁኔታን አስቀምጣለች።

ስምምነቱን ተከትሎ የኢትዮጵያ የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ባወጣው መግለጫ ላይ የተፈረመው የመግባቢያ ሰነድ በየትኛውም ወገን ላይ ጉዳት የማያደርስ መሆኑን መግለጹ ይታወሳል።

ሶማሊያ የዓለም አቀፍ ሕግን መሠረት በማድረግ ሁሉንም ወገን በሚጠቅም መልኩ “የኢኮኖሚ እድገት እና የጋራ ብልጽግና” የሚያመጣ ግንኙነት ከሁሉም የተባበሩት መንግሥታት፣ የአፍሪካ ኅብረት እና የኢጋድ አባል አገራት ጋር ለማድረግ ዝግጁ መሆኗን በመግለጫው አስታውቃለች።

የአፍሪካ ኅብረት የሰላም እና የፀጥታ ምክር ቤት ያደረገው ውይይት አስመልክቶ ከኢትዮጵያ መንግሥት በኩል እስካሁን የተሰጠ መግለጫም ሆነ አስተያየት የለም።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ እና የሶማሊላንዱ ፕሬዝዳንት ሙሴ ቢሂ በአዲስ አበባ የተፈራረሙት የመግባቢያ ስምምነት በቀጣናው ላይ ውጥረት ከፈጠረ ከሁለት ሳምንት በላይ ሆኗታል። በአንድ ወር ውስጥ ይፈጸማል በተባለው በዚህ ስምምነት መሠረት ኢትዮጵያ ለወታደራዊ እና ንግድ አገልግሎት የሚውል የባሕር በር ታገኛለች።

ኢትዮጵያ በምላሹ ሶማሊላንድን እንደ አገር የሚያስቆጥራትን እውቅና ለመስጠት መስማማቷን የሃርጌሳ ባለሥልጠናት ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ መንግሥት ግን ስምምነት የፈጸመው ጉዳዩን በጥልቀት አጢኖ አቋም ለመያዝ መሆኑን አስታውቋል። ከዚህ ባሻገር ግን ሶማሊላንድ ከኢትዮጵያ አየር መንገድ ድርሻ እንደሚኖራት የኢትዮጵያ መንግሥት መግለጹ ይታወሳል።  ዘገባው የቢቢሲ ነው፡፡

selegna

By selegna

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *