ጥናቶች ኤች-ፒ-ቪ (HPV) በሚል ምሕጻር የሚጠራው ቫይረስ መከላከያ ክትባት 90 ከመቶ የማኅጸን በር ጫፍ ካንሰርን እንደሚከላከል ያሳያሉ።

የማኅጸን በር ጫፍ ካንሰር በዓለም ላይ አራተኛው ገዳይ የካንሰር ዓይነት ነው። በየዓመቱ 300 ሺህ ሰዎችን ይገድላል።

ኤች-ፒ-ቪ (HPV) ክትባት ዘጠኝ ዓይነት ኤች-ፒ-ቪ ቫይረስን ይከላከላል።

ከእነዚህ መካከል ሁለቱ የማኅጸን በር ጫፍ ካንሰርን የሚያመጡ ናቸው። የፊንጢጣ ካንሰር እና የመራቢያ አካላት ካንሰር እንዲሁም የጭንቅላት እና የአንገት ካንሰር ሌሎቹ ናቸው።

ጥናቶች ይህ ክትባት ቢያንስ ለ10 ዓመት ይከላከላል።

ክትባቱ ለነማን ይሰጣል?

ይህ ክትባት ወጣት ወንድ እና ሴቶች ከግንኙነት በፊት ቢወስዱት፣ ለቫይረሱ ከመጋለጣቸው ቀደም ብለው ቢወስዱት ይመከራል።

ይህ የሆነበት ዋናው ምክንያት ክትባቱ ኢንፌክሽንን ስለሚከላከል ነው። ሰውነት አንዴ በዚህ ኢንፌክሽን ከተጠቃ ግን ክትባቱ ቫይረሱን ከሰውነት የማስወገድ አቅም የለውም።

ቫይረሱ በጣም ተዛማጅ ስለሆነ ክትባቱ ወጣቶች ለወሲብ ግንኙነት ዝግጁ ከመሆናቸው በፊት ቢሰጣቸው መልካም ነው።

የዓለም የጤና ድርጅት ክትባቱ በባለ አንድ ወይም በባለ ሁለት ጠብታ (doses) ሊሰጥ እንደሚችል ይገልጻል። ነገር ግን የበሽታ መከላከል አቅማቸው ዝቅተኛ የሆኑ ሰዎች በባለሁለት እና ባለ ሦስት ጠብታ እንዲወስዱት ይመከራል።

ኤች- ፒ- ቪ ምንድነው?

ኤች-ፒ-ቪ (HPV) በሚል ምሕጻር የሚጠራው ይህ ቫይረስ በሙሉ ስሙ ሂውማን ፓፒሎማቫይረስ (human papillomavirus) ይሰኛል።

ከመቶ በላይ የቫይረሱ ዓይነቶች አሉ። ኢንፌክሽኖች ታዲያ ምንም ምልክት ላያሳዩ ይችላሉ። ቆዳ ላይ ትንንሽዬ እብጠቶች የሚታዩበት አጋጣሚ አለ። እነዚህ ቆዳ ላይ ኩፍ የሚሉ ምልክቶች ታዲያ በእጅ፣ በእግር፣ በመራቢያ አካል እና በአፍ ውስጥ ሊከሰቱ ይችላሉ።

ደም የተቀላቀለበት ሽንት፣ ከማረጥ በኋላ የሚከሰት የደም ፍሰት፣ ያለ ጊዜው በወር አበባ መሀል የሚመጣ የደም መፍሰስ፣ ብሽሽት አካባቢ የህመም ስሜት ከታየ ሐኪም መጎብኘት ይመከራል።

ብዙ ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸውን ሳያውቁ ሰውነታቸው በራሱ ጊዜ ቫይረሱን ሊያስወግደው ይችላል።

ይሁንና ከፍተኛ የሚባለው የኤችፒቪ ዓይነት ወደ ካንሰር ሊያድግ የሚችል ነው።

ቫይረሱ በግብረ ሥጋ ግንኙነት ይተላለፋል?

አዎ ይተላለፋል። በቀላሉ ከሰው ወደ ሰው የሚተላለፍ ቫይረስ ነው። በቀላሉ የቆዳ ለቆዳ ንክኪም ይተላለፋል።

ከ80 በመቶ በላይ ሰዎች ገና 25 ዓመት ሳይሞላቸው ለኤችፒቪ ቫይረስ ሊጋለጡ ይችላሉ።

ብዙ ሰዎች ከ18 ወራት እስከ ሁለት ዓመት ድረስ በቫይረሱ ይጠቃሉ።

ነገር ግን ቫይረሱ የተራክቦ በሽታ ነው ለማለት ይቸግራል። ምክንያቱም በግብረ ሥጋ ግንኙነት ጊዜ በሚፈጠር ፈሳሽ ልውውጥ የሚተላለፍ ስላልሆነ።

ቢሆንም ግን ቫይረሱ በወሲብ ጊዜ በሚደረግ የቆዳ ለቆዳ ንክኪ ሊተላለፍ መቻሉ አደገኛ ያደርገዋል።

ክትባቱ ምን ያህል በቀላሉ ይገኛል?

ኢትዮጵያ ይህን ክትባት ከሚሰጡ የአፍሪካ አገሮች አንዷ ናት።

ከ90 በመቶ በላይ የማኅጸን በር ጫፍ ካንሰር ሞት የሚከሰተው በዝቅተኛ እና መካከለኛ ገቢ ባላቸው አገሮች ዘንድ እንደሆነ የዓለም ጤና ድርጅት ያወጣው ዘገባ ያሳያል።

በእነዚህ አገሮቸ ብዙውን ጊዜ የማኅጸን በር ካንሰር ምልክት እስኪያሳይ ድረስ ሳይታወቅ ይቆያል። የዓለም ጤና ድርጅት በሚቀጥለው ምዕተ ዓመት ከዓለም ለማጥፋት ያስባል። ይህን ለማሳካት ከ90 በመቶ በላይ ክትባት በ2020 ለማድረስ እየሠራ ነው።

የትኞቹ አካባቢዎች ይበረታል?

ከሰሐራ በታች ባሉ የአፍሪካ አገሮች የማኅጸን በር ካንሰር ምጣኔው ከፍተኛ ነው። ከዚያ ቀጥሎ ደግሞ በላቲን አሜሪካ እና በካሪቢያን ከፍተኛ ሥርጭት አለ።

ከሰሐራ በታች ባሉ አገራት መበርከቱ አንዱ ምክንያት በጊዜ ምርመራ ስለማይደረግ እና ሕክምናውም ስለማይዳረስ ነው።

ብዙ ዜጎችም ክትባቱን ለመውሰድ ዳተኛ መሆናቸው ሥርጭቱን አባብሶታል።

ሩዋንዳ በአፍሪካ ክትባቱን በዘመቻ በማስተዋወቅ ስሟ ቀዳሚ ነው።

በአውሮፓውያን 2011 ልጃገረዶች በጊዜ ክትባቱን እንዲወስዱ ዘመቻ ጀምራለች። የማኅጸን በር ጫፍ ቅድመ ምርመራ መርሐ ግብርም ጀምራለች።

በመጀመሪያው ዓመት ከ10 ለክትባት ከደረሱ ልጃገረዶች 9 የሚሆኑትን በመከተብ ይበል የሚያሰኝ ተግባር አሳክታለች።

ምንም እንኳ ክትባቱ በቫይረሱ የመያዝን ዕድል በከፍተኛ ሁኔታ የሚቀንስ ቢሆንም ሁሉንም ዓይነት ኤችፒቪ ቫይረስ ያጠፋል ማለት አይደለም።

ለዚህም ነው ዕድሜያቸው 25 ዓመት የደረሱ ሴቶች በየጊዜው ምርመራ ያድርጉ ተብሎ የሚመከረው።  ዘገባው የቢቢሲ ነው፡፡

selegna

By selegna

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *