በቅርቡ በርካታ ፖለቲካዊ የአሰላለፍ ለውጦች እና ውጥረቶችን እያስተናገደ በሚገኘው የአፍሪካ ቀንድ ጉዳዮች ዙሪያ በቀጣይ ቀናት ከሚጠበቁ ሁነቶች መካከል የኢጋድ እና የአረብ ሊግ ስብሰባዎች እንዲሁም የካይሮ ጉብኝት ከፍተኛ ትኩረትን የሚስቡ ናቸው።

ለእነዚህ ሁነቶች ዋነኛ ማጠንጠኛ ይሆናል ተብሎ የሚጠበቀው ከሁለት ሳምንት በፊት ኢትዮጵያ ከሶማሊያ ተነጥላ ከሦስት አስርት ዓመታት በላይ ነጻ አገር መሆኗን ካወጀችው ሶማሊላንድ ጋር የባሕር በር ማግኘት ያስችላታል የተባለውን የመግባቢያ ሠነድ መፈረሟን ተከትሎ የተፈጠረው ውዝግብ ነው።

በስምምነቱ ኢትዮጵያ በኤደን ባሕረ ሰላጤ ላይ የባሕር በር እና የባሕር ኃይል ሰፈር እንድታገኝ በምላሹም ሶማሊላንድ የአገርነት ዕውቅናን ከኢትዮጵያ ለማግኘት መስማማታቸው መዘገቡን ተከትሎ ጉዳዩ ከአፍሪካ ቀንድ አልፎ በምሥራቅ አፍሪካ ፖለቲካዊ ውጥረትን ፈጥሯል።

ስምምነቱ በእጅጉ ያስቆጣው እና ሶማሊላንድን እንደ አንድ የራሱ ግዛት አድርጎ የሚመለከተው የሶማሊያ መንግሥት ስምምነቱ ሕጋዊ መሠረተ የሌለው እና ተፈጻሚ ሊሆን የማይችል ነው ብሏል።

የዚህ ስምምነት መፈረምን ተከትሎ ባለፈው ሳምንት በቀጠናው መሪዎች እና በልዑካኖቻቸው አማካይነት የሚደረጉ ጉብኝቶች እና ውይይቶች የጨመሩ ሲሆን፣ የተፈጠረው ውጥረት እንዲረግብ የተለያዩ አገራት ጥሪ ሲያቀርቡ ሰንብተዋል።

በዚህም ሳቢያ በአገራት መካከል ከሚደረጉት ንግግሮች ባሻገር የአካባቢያዊ እና በርካታ አገራትን ያቀፉ ተቋማት አስቸኳይ ስብሰባ ጠርተዋል። በዚህም ከኢትዮጵያ እና የሶማሊላንድ ጉዳይ በተጨማሪ የሱዳን ጦርነትም መነጋገሪያ እንደሚሆን እየተነገረ ነው።

የኢጋድ ስብሰባ

የምሥራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግሥታት ድርጅት (ኢጋድ) በኢትዮጵያ እና በሶማሊያ ውዝግብ ዙሪያ ለመነጋገር የጠራው አስቸኳይ ስብሰባ የፊታችን ሐሙስ ጥር 9/2016 ዓ.ም. በኡጋንዳ ካምፓላ ይደረጋል።

የጂቡቲ የውጭ ጉዳይ ሚንስቴር ለኢጋድ አባል አገራት እና በጂቡቲ ለሚገኘው የድርጅቱ ዋና ጽ/ቤት በላከው ደብዳቤ ስብሰባውን ለማዘጋጀት የኡጋንዳው ፕሬዝዳንት ዩዌሪ ሙሴቪኒ መስማማታቸውን ይፋ ያደርግ እንጂ፤ እስካሁን ከትኛውም የኢጋድ አባል አገር በስብሰባው ሰለመገኘታቸው የተሰጠ ማረጋገጫ የለም።

ይህ በኢትዮጵያ እና በሶማሊያ መካከል የተፈጠረውን ውጥረት ለማርገብ የተጠራው ስብሰባ የሚደረገው ከሶማሊያ መንግሥት ከፍተኛ አመራሮች ግጭት ቀስቃሽ የሆኑ ጠንካራ አስተያየቶችን እየተሰጡ ባለበት ወቅት ነው።

የሶማሊያ ጠቅላይ ሚንስትር ሐምዛ አብዲ ባሬ ከትናንት በስቲያ ቅዳሜ ከኢትዮጵያ ጋር ጦርነት ውስጥ ለመግባት ዝግጁ ነን ሲሉ ተደምጠዋል።

“ካልተዋችሁን፤ እንድትተዉን የሚያደርግ ነገር እናሳያችኋለን። . . .ወደ ሶማሊያ ግዛት አንድ ኢንች ለመግባት ቢሞከሩ፤ አስክሬኖችን ይዘው ወደ አገራቸው ይመለሳሉ” ብለዋል ጠቅላይ ሚንስትር ሐምዛ አብዲ ባሬ።

ከዚህ ከጠቅላይ ሚንስትሩ ንግግር ሁለት ቀናት በፊት ደግሞ ፕሬዝዳንት ሐሰን ሼክ ሞሐሙድ ኢትዮጵያን የሶማሊያ “ጠላት” ሲሉ ገልጸዋታል።

“ከዚህ ቀደም የወረራ ሙከራቸውን ተከላክለናል። ከዚህ ቀደም አሸንፈናቸዋል፤ አሁንም እናሸንፋቸዋለን” ሲሉ ፕሬዝዳንቱ አርብ ጥር 3/2016 ዓ.ም. በአንድ መስጂድ ውስጥ ከተካሄደ የፀሎት ሥነ-ሥርዓት በኋላ ተናግረዋል።

የወቅቱ የኢጋድ ሊቀ መንበር የሆኑት የጂቡቲው ፕሬዝዳንት ኢስማኤል ኦማር ጊሌ የጠሩት አስቸኳይ ስብሰባ የሱዳን የእርስ በእርስር ጦርነት ሌላኛው አጀንዳው እንደሆነ ተጠቅሷል።

ኢጋድ በሱዳን የእርስ በእርስ ጦርነት እየተሳተፉ የሚገኙትን ሁለቱን የጦር መሪዎች በአካል በተገኙበት ልዩነቶቻቸውን በንግግር እንዲፈቱ ጥሪ ቢያቀርብም የሱዳኑ መሪ በስብሰባው ላይ እንደማይገኙ ይፋ ተደርገዋል።

የሱዳን ሠራዊት አዛዥ የሆኑት ሌተናል ጄኔራል አብዱል ፋታል አል-ቡርሃን በስብሰባው እንደማይገኙ የሱዳን ዜና ወኪል የሆነው ሱና ያስነበብ ሲሆን፤ በተቃራኒው ከሱዳን ጦር ጋር እየተዋጋ የሚገኘው የፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ መሪ ሌተናል ጄኔራል ሞሐመድ ሐምዳን ዳጋሎ (ሔምቲ) በኤክስ ገጻቸው በስብሰባው ላይ እንደሚገኙ ይፋ አድርገዋል።

በተጠራው የመሪዎች ስብሰባ ላይ የሔምቲ መገኘት ያላስደሰታቸው ጄኔራል አል-ቡርሃን፤ በሱዳን ያለው ግጭት የአገር ውስጥ ጉዳይ ስለሆነ ቀጠናዊው ድርጅቱ በአገራዊ ጉዳይ ውስጥ ጣልቃ በመግባት የሱዳንን ሉዓላዊነት መዳፈር የለበትም ብለዋል።

የአረብ ሊግ የጠራው ስብሰባ

ሌላኛው በዚህ ሳምንት ስብሰባ የጠራው የአረብ ሊግ በሶማሊያ ጥያቄ በኢትዮጵያ እና ሶማሊያ ውዝግ ዙሪያ ውይይት ለማድረግ ለረቡዕ ጥር 8/2106 ዓ.ም. አስቸኳይ ስብሰባ መጥራቱ ተሰምቷል።

ኢትዮጵያ ከሶማሊላንድ ጋር የተፈራረመች “ሕጋዊ” ያልሆነ የመግባቢያ ሠነድ በቀጠናው ሊያስከትለው ስለሚችለው ውጤት የአረብ ሊግ አጀንዳ አንደሚሆን አናዱሉ የግብፅ መንግሥት የዜና ወኪል የሆነውን ሜና ጠቅሶ ዘግቧል።

ከዚህ ቀደም የአረብ ሊግ ኢትዮጵያ እና ሶማሊላንድ የደረሱትን ስምምነት እንደሚቃወም እና ከሶማሊያ ጎን እንደሚቆም መግለጹ ይታወሳል።

የአረብ ሊግ ረቡዕ ታኅሣሥ 24/2016 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ የሶማሊያን ሉዓላዊነት የሚጋፋን ማንኛውንም ስምምነት “አንቀበልም” ብሎ ነበር።

የሊጉ ቃል አቀባይ ጋማል ሮሽዲ “ኢትዮጵያ እና ሶማሊላንድ በወደብ ጉዳይ አብረው ለመሥራት መወሰናቸውን የሶማሊያ ካቢኔ ‘ተቀባይነት የለውም’ ማለቱን የአረብ ሊግ ሙሉ በሙሉ ይደግፈዋል” ብለው ነበር ሊጉ ባወጣው መግለጫ።

የካይሮ ጉብኝት

በዚህ ሳምንት ከሚጠበቁ ሁነቶች መካከል ሌላኛው የሶማሊያ እና የኤርትራ መሪዎች ወደ ካይሮ የሚያደርጉት ጉብኝት ነው።

ምንም እንኳ መሪዎቹ በየትኛው ቀን ወደ ካይሮ እንደሚሄዱ በይፋ የተባለ ነገር ባይኖርም፣ አንዳንድ ሪፖርቶች ፕሬዝዳን ሐሰን ሼክ ሞሐመድ እና ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ የፕሬዝዳንት አብደል ፈታህ አል-ሲሲ ግብዣን ተከትሎ በቀጣይ ቀናት ወደ ካይሮ ሊጓዙ እንደሚችሉ ጠቁመዋል።

የግብፁ አል-ሲሲ ለሶማሊያ እና ለኤርትራ አቻዎቻቸው ለይፋዊ የሥራ ጉብኝት ወደ ካይሮ እንደሚመጡ ባለፈው ሳምንት ግብዣ ማቅረባቸው ይፋ መደረጉ ይታወሳል።

ከቀናት በፊት የግብፅ የውጭ ጉዳይ ሚንስትር ሳሚ ሽኩሪ ወደ አሥመራ ባቀኑ ወቅት ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ለይፋዊ የሥራ ጉብኝት ወደ ካይሮ እንዲመጡ ከፕሬዝዳንት አል-ሲሲ ጥሪ እንደቀረበላቸው ተገልጿል።

ከጥቂት ቀናት በፊት በተመሳሳይ ፕሬዝዳንት አል-ሲሲ ወደ ሶማሊያ የላኩት የልዑክ ቡድን የሶማሊያው ፕሬዝዳንት ለይፋዊ የሥራ ጉብኝነት ካይሮ መጋበዛቸው መገለጹ ይታወሳል።

የኤርትራ እና የሶማሊያ ፕሬዝዳንቶች የካይሮ ጉብኝነት የሚደረግበት ዕለት እንዲሁም ጉብኝቱ በተናጠል ወይም በጋራ የሚደረግ ስለመሆኑ እስካሁን በይፋ የተባለ ነገር የለም።

ኢትዮጵያ እና ሶማሊላንድ ብዙ ያነጋገረውን የጋራ የመግባቢያ ሠነድ ከፈረሙ በኋላ የሶማሊያው ፕሬዝዳንት ሐሰን ሼክ ሞሐሙድ ባደረጉት ብቸኛ የውጭ አገር ጉዞ ወደ ኤርትራ ማቅናታቸው ይታወቃል።     ዘገባው የቢቢሲ ነው፡፡

selegna

By selegna

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *