የምሥራቅ አፍሪካ በይነ መንግሥታት ድርጅት (ኢጋድ) በኢትዮጵያ እና ሶማሊያ ውዝግብ ዙሪያ ለመነጋገር አስቸኳይ ስብሰባ ጠራ።

የወቅቱ የኢጋድ ሊቀ መንበር የሆኑት የጂቡቲው ፕሬዝዳንት ኢስማኤል ኦማር ጊሌ የጠሩት አስቸኳይ ስብሰባ በኡጋንዳ እንደሚካሄድ ቢቢሲ ሶማልኛ ከጂቡቲ መንግሥት ምንጮች አረጋግጧል።

በኡጋንዳ በሚካሄደው አስቸኳይ ጉባኤ ላይ ከኢትዮጵያና ሶማሊያ ሰሞነኛ ውዝግብ በተጨማሪ ስለ ሱዳን የእርስ በእርስ ጦርነትም ውይይት እንደሚካሄድ ታውቋል።

የሶማሊያ ዜና ወኪል የሆነው ሶና ለኢጋድ አባል አገራት የተላከ ነው ባለው የስብሰባ ጥሪ ደብደቤ ላይ የፊታችን ሐሙስ፣ ጥር 9፣ 2016 ዓ. ም. በኡጋንዳ በሚካሄደው ልዩ ጉባኤ ላይ የኢጋድ አባል የሆኑ የምሥራቅ አፍሪካ መንግሥታት ተገኝተው በሱዳን እንዲሁም በኢትዮጵያና ሶማሊያ ጉዳይ እንዲወያዩ የኢጋድ ሊቀ መንበርና የጂቡቲ ፕሬዝዳንት ኢስማኤሊ ኦማር ጊሌ ጥሪ ማቅረባቸውን ዘግቧል።

ከኡጋንዳው ፕሬዝዳንት ዩዌሪ ሙሴቪኒ ጋር በመወያየት ጉባኤው በኡጋንዳ እንደሚካሄድም ተገልጿል።

የሶማሊያ ብሔራዊ ዜና አገልግሎት ሶና በኤክስ ገጹ ላይ ለኢጋድ አባል አገራት የቀረበውን የውይይት ጥሪ ደብዳቤ አያይዞ ያወጣው ጽሑፍ እንደሚያስረዳው፣ ከኢጋድ አባል አገራት በተጨማሪ የአፍሪካ ኅብረትና ዓለም አቀፍ የዲፕሎማቲክ ማኅበረሰብም እንዲሳተፉ ጥሪ ይደረጋል።

ኢትዮጵያ ከሶማሊያ ተገንጥላ ራስ ገዝ ከሆነችው ሶማሊላንድ ጋር የባሕር በር ማግኘት ያስችላታል የተባለውን የመግባቢያ ሠነድ መፈረሟን ተከትሎ፣ የሶማሊያ መንግሥት ስምምነቱ ሕጋዊ መሠረተ የሌለው እና ተፈጻሚ ሊሆን የማይችል ነው ካለ በኋላ በቀጠናው ውጥረት አይሏል።

ትናንት ጥር 3፣ 2016 ዓ. ም. በሺዎች የሚቆጠሩ ሰልፈኞች በዋና ከተማዋ ሞቃዲሾ ተገኝተው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ እና የሶማሊንዱ ፕሬዝደንት ሙሴ ቢሂ አብዲ የገቡትን ስምምነት ተቃውመዋል።

በስምምነቱ መሠረት ሶማሊላንድ የኤደን ባሕረ ሰላጤ ላይ ለኢትዮጵያ የባሕር በር የምትሰጣት ሲሆን ኢትዮጵያ ደግሞ ለሶማሊላንድ ዕውቅና እንደምትሰጥ በስፋት ተዘግቧል።

በኡጋንዳ በሚካሄደው የኢጋድ ውይይት አጀንዳ ሆነው ከሚቀርቡ አንደኛው በሱዳን እየተዋጉ ባሉት የጦር ጄነራሎች መካከል የተኩስ አቁም ስምምነት እንዲደረስ ማስቻል እና በውይይት ለግጭቱ ፖለቲካ መፍትሄ በመስጠት በአገሪቱ በሲቪሎች የሚመራ አስተዳደር እንዲዋቀር መንገድ ማመቻቸት ነው።

በተጨማሪም የኢትዮጵያ እና ሶማሊላንድን ስምምነት ተከትሎ በኢትዮጵያ እና ሶማሊያ መካከል የተፈጠረውን ውዝግብ ውይይቱ የሚዳስስ ይሆናል።

“ሰላማዊ መፍትሄ ላይ መድረስ” የዚህ ልዩ ጉባዔ ዓላማ እንደሆነ በስብሰባ ጥሪ ደብዳቤ ላይ ተገልጿል።

የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የብሔራዊ ደኅንነት አማካሪ አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን ጥር 3፣ 2016 ዓ. ም. በኤክስ ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት “የሕዳሴውን ግድብ ያሳካነው ተጨብጭቦልን ሳይሆን ከቅርብም ከሩቅም እየተላጋን፣ የስጋት ከበሮ እየተደለቀ፣ ዛቻና ማስፈራሪያ በምድርም በአየርም ልምምድ እያስገመገመብን፣ ሁሉንም ዓይነት ጫና ተቋቁመን ነበር። የባሕር በሩም እንዲሁ ይሆናል” ብለዋል።

የሶማሊያው ፕሬዝዳንት ሐሰን ሼክ ሞሐሙድ መንግሥት ስምምነቱን “በሶማሊያ ነጻነት፣ ሉዓላዊነት፣ የግዛት አንድነት እና የሶማሊያ ፌደራላዊ ሪፐብሊክ ላይ የተቃጣ ጥቃት ነው” ማለቱ አይዘነጋም።

ፕሬዝዳንቱ ኢትዮጵያ ከሶማሊላንድ ጋር የገባችውን ስምምነት “ውድቅ የሚያደርግ” ያሉትን ሕግ ፈርመው አፅድቀዋል።

ወደ ኤርትራ ተጉዘው ከፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ጋር ውይይት ያደረጉ ሲሆን አሁን ደግሞ ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ የግብፅ የውጭ ጉዳይ ሚንስትር ሳሚ ሹኩሪን ተቀብለው አነጋግረዋል።

የግብጽ ፕሬዝዳንት አብዱል ፋታህ አል-ሲሲ ከኢትዮጵያ ጋር ውዝግብ ውስጥ ለገባችው ሶማሊያ ድጋፍ እንደሚያደርጉ ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ የመንግሥት ኮሚዩኒኬሽን አገልግሎት በበኩሉ ባለፈው ሳምንት ባወጣው መግለጫ፣ ኢትዮጵያና ሶማሊላንድ የደረሱት ስምምነት “ማንንም የሚጎዳ አይደለም፤ ሕግም አልተጣሰም” ማለቱ ይታወሳል።

ከስምምነቱ በኋላ የአፍሪካ ኅብረት እና አሜሪካ፣ በኢትዮጵያና ሶማሊያ መካከል ያለው ውጥረት እንዲረግብ ጥሪ ሲያቀርቡ፣ የአውሮፓ ኅብረት የሶማሊያን የግዛት አንድነት ማክበር ያስፈልጋል ብሏል።

የኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ጥር 3፣ 2016 ዓ. ም. ባወጣው መግለጫ፣ በኢትዮጵያና በሶማሊላንድ መካከል የተፈረመውን የመግባቢያ ሠነድ በተመለከተ የስምምነቱን ማዕቀፍ፣ ዝርዝር ይዘቱን እና ከስምምነቱ ጋር ተያይዘው ባሉት ዕድሎችና ስጋቶች ላይ ከተወያየ በኋላ ስምምነቱን ያለልዩነት መደገፉን አሳውቋል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ ኢትዮጵያ እና ሶማሊላንድ ለኢትዮጵያ የባሕር ጠረፍ ያስገኛል የተባለውን የመግባቢያ ሰነድ መፈራረማቸውን ተከትሎ በሶማሊያ እና ሶማሊላንድ በሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ላይ አካላዊ ጥቃት እና የንብረት ዝርፊያዎች እየተፈጸሙ እንደሆነና ዛቻዎችና ማስፈራሪያዎችም እየደረሱ እንደሆነ ስደተኛ ኢትዮጵያውያን ገልጸዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ እና የሶማሊላንድ ፕሬዝደንት ሙሴ ቢሂ አብዲ በደረሱት የግዴታ ተፈጻማኒት የሌለው የመግባቢያ ሠነድ መሠረት ኢትዮጵያ ከሶማሊላንድ 20 ኪሎ ሜትር ገደማ ወደብ ታገኛለች።

ሶማሊላንድ ደግሞ ከአገርነት ዕውቅና በተጨማሪ ከኢትዮጵያ አየር መንገድ የተወሰነ ድርሻ እንደምታገኝ ተገልጿል። ዘገባው የቢቢሲ ነው፡፡

selegna

By selegna

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *