በአማራ ክልል ጎንደር ከተማ በቀናት ልዩነት ለሁለተኛ ጊዜ በፋኖ ታጣቂዎች እና በመከላከያ ሰራዊት መካከል በተደረገ የተኩስ ልውውጥ በሰው ሕይወት እና በንብረት ላይ ጉዳት መድረሱን ነዋሪዎች ገለጹ።

ሐሙስ ጥር 2፤ 2016 ዓ.ም ከ5፡00 ሰዓት ገደማ ጀምሮ እስከ ምሽት ድረስ በዘለቀው የተኩስ ልውውጥ፤ የግለሰብ መኖሪያ ቤቶች በመሣሪያ መመታታቸውን ሁለት ነዋሪዎች ለቢቢሲ ገልጸዋል።

ሶስት የከተማዋ ነዋሪዎች ለቢቢሲ እንደገለጹት የተኩስ ልውውጡ የተካሄደው “ልደታ” ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ነው።

ይህ አካባቢ የጎንደር ዩኒቨርስቲ ማራኪ ካምፓስን ጨምሮ የመምህራን ማሰልጠኛ ኮሌጅ እንዲሁም የቅድመ መደበኛ እና የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤቶች እንደሚገኙበት ነዋሪዎቹ አስረድተዋል።

ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁ አንድ የአካባቢው ነዋሪ፤ “4፡40 ሰዓት አካባቢ የፋኖ ኃይሎች እዚህ ገብተዋል በሚል የመንግስት ሚሊሻ እና መከላካያ፤ ከባባድ መሣሪያዎችን የታጠቁ የመንግስት ኃይሎች ወደ ከተማዋ በመግባት ተኩስ ከፈቱ” ሲሉ ገልጸዋል።

ተኩስ የተጀመረው ሰዎች እንዳይንቀሳቀሱ “በአካባቢው ላይ የእንቅስቃሴ ገደብ” ተደርጎ መሆኑን የሚናገሩት ነዋሪው፤ እስከ ምሽት ድረስ ከባድ መሣሪያ ተኩስ ይሰማ እንደነበር አስታውሰዋል።

ሌላ የከተማዋ ነዋሪ በበኩላቸው ግጭቱ ሲመጀር ከሁለት ወገኖች የተኩስ ልውውጥ ሲካሄድ የነበረ ቢሆንም በኋላ ላይ የመሣሪያ ድምጽ ይሰማ የነበረው ከአንድ አቅጣጫ ብቻ እንደነበር አስረድተዋል።

እንደ ነዋሪው ገለጻ የተኩስ ልውውጡ የተጀመረው የሰዎች እና የንግድ እንቅስቃሴ በነበረበት የሥራ ሰዓት በመሆኑ ነዋሪዎች ላይ ድንጋጤ ተፈጥሮ ነበር።

የልደታ አካባቢ ነዋሪ የሆኑት ግለሰብ በበኩላቸው፤ “አካባቢው ላይ“ ብዙ ትምህርት ቤቶች አሉ፣ መዋለ ሕጻናትም አሉ። ወላጆች ልጆቻቸውን [ከትምህርት ቤቶች] ለማምጣት [ሲያደርጉ] የነበረው እንቅስቃሴ ለመናገር ይከብዳል” ሲሉ ተመሳሳይ ሃሳብ አንስተዋል።

ነዋሪው እንደሚያስረዱት በተኩስ ልውውጡ በርካቶች ጉዳት የደረሰባቸው ሲሆን “እስካሁን ድረስ የሰባት ሰዎች የቀብር ሥነ-ሥርዓት ተፈጽሟል።”

አካባቢው የመኖሪያ መንደር እና የንግድ እንቅስቃሴ የሚከናወንበት መሆኑን የሚጠቅሱት እኚህ ነዋሪ፤ በተኩስ ልውውጡ ምክንያት የግለሰብ መኖሪያ ቤቶች “ከባድ” ጉዳት ደርሶባቸዋል።

“አብዛኛው መሣሪያ የወደቀው የግለሰቦች ቤት ውስጥ ነው። አካባቢው የሚገኙ ቤቶች ላይ የወደቁ መሣሪያዎች ከባድ ጥፋቶችን አስከትለዋል” ሲሉ በንብረት ላይ የደረሰውን ጉዳት ጠቅሰዋል።

ቢቢሲ ያነጋገራቸው ሌላ የከተማዋ ነዋሪም በመሣሪያ ተደብድቦ “ግማሽ ጎኑ” ከፍተኛ ጉዳት የደረሰበት የመኖሪያ ሕንጻ መመልከታቸውን ገልጸዋል።

ሐሙስ ዕለት የተኩስ ልውውጥ መጀመሩን ተከትሎ በከተማዋ የሚደረገው እንቅስቃሴ ቆሞ እንደነበር የገለጹት ነዋሪዎቹ አርብ ሙሉ በሙሉ ባይሆንም ሁኔታዎች ወደ ነበሩበት መመለሳቸውን ተናግረዋል።

ጎንደር ከተማ በቀናት ልዩነት ውስጥ የፋኖ ኃይሎች እና በመከላከያ ሰራዊት አባላት መካከል የሚደረግን የተኩስ ልውውጥ ስታስተናግድ የሐሙሱ ለሁለተኛ ጊዜ ነው።

ባለፈው ሳምንት ቅዳሜ እና እሁድ በተደረገ የተኩስ ልውውጥ ጉዳት የደረሰባቸው ከ20 በላይ ሰላማዊ ነዋሪዎች ወደ ጎንደር ሆስፒታል መግባታቸውን አንድ የሆስፒታሉ ሐኪም ለቢቢሲ ተናግረው ነበር።

የጎንደር ከተማ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ አቶ ባዩህ አቡሃይ በሳምንቱ መጀመሪያ ሰኞ ዕለት በሰጡት መግለጫ ማራኪ ክፍለ ከተማ አየር ጤና ቀበሌ የተከሰተው ግጨዕት በጸጥታ ኃይል ርብርብ በቁጥጥር ስር መዋሉን ተናግረው ነበር።

ቢቢሲ የሐሙሱን የተኩስ ልውውጥ በተመለከተ ከአካባቢው ባለሥልጣናት ተጨማሪ መረጃ ለማግኘ ያደረገው የሙከራ አልተሳካም። ዘገባው የቢቢሲ ነው፡፡

selegna

By selegna

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *