የኤርትራው ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ የግብጽ የውጭ ጉዳይ ሚንስትር ሳሚ ሹኩሪን ተቀብለው አነጋገሩ።

የኤርትራ የማስታወቂያ ሚንስትር የማነ ገ/መስቀል ሁለቱ ባለስልጣናት በሁለቱ አገራት ግንኙነት ዙሪያ እና በቀጠናዊ ጉዳዮች ላይ ውይይት አድርገዋል ብለዋል።

ከዚህ በተጨማሪም የውጭ ጉዳይ ሚንስትሩ ከፕሬዝዳንት አብደል ፋታህ አል-ሲሲ የተላከውን ደብዳቤ ለፕሬዝዳንት ኢሳያስ ማስረከባቸው ተገልጿል።

የውጭ ጉዳይ ሚንስትሩ ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ለይፋዊ የሥራ ጉብኝት ወደ ካይሮ እንዲመጡ ከፕሬዝዳንት አል-ሲሲ ግብዣ እንደቀረበላቸው ጨምረው ገልጸዋል።

ከጥቂት ቀናት በፊት በተመሳሳይ ፕሬዝዳንት አል-ሲሲ ወደ ሶማሊያ የላኩት የልዑክ ቡድን የሶማሊያው ፕሬዝዳንት ለይፋዊ የሥራ ጉብኝነት ካይሮ መጋበዛቸው መገለጹ ይታወሳል።

ኢትዮጵያ ከሶማሊያ ተገንጥላ ራስ ገዝ ከሆነችው ሶማሊላንድ ጋር የባሕር በር ማግኘት ያስችላታል የተባለውን የመግባቢያ ሠነድ መፈረሟን ተከትሎ በቀጠናው የሚደረጉ የመሪዎች የሥራ ጉብንቶች እና ውይይቶች ጨምረዋል።

ከቀናት በፊት የሶማሊያ ፕሬዝዳንት ሐሰን ሼይክ ሞሐሙድ ለይፋዊ የሥራ ጉብኝት ወደ ኤርትራ ማቅናታቸው ይታወሳል።

የፕሬዝዳንቱ ጽ/ቤት ቪላ ሱማሊያ ሐሰን ሼይክ ሞሐሙድ ሰኞ ታኅሣሥ 29/2016 ወደ ኤርትራ የተጓዙት “በሁለቱ ወንድማማች አገራት” የሁለትዮሽ ጉዳዮች ላይ ለመምክር ዛሬ መሆኑን መግለጹ ይታወሳል።

ኢትዮጵያ ከሶማሊላንድ ጋር የባሕር በር ማግኘት ያስችላታል የተባለውን የመግባቢያ ሠነድ መፈረሟን ተከትሎ ፕሬዝዳንት ሐሰን ሼይክ ሞሐሙድ ወደ ኤርትራ ካደረጉት ጉዞ በተጨማሪ ከተለያዩ መሪዎች ጋር የስልክ ውይይቶችን ሲያደርጉ ቆይተዋል።

ፕሬዝዳንት ሐሰን ሼይክ ባለፉት ጥቂት ቀናት ከግብጽ፣ ኡጋንዳ፣ ቱርክ እና ኳታር መሪዎች ጋር እንዲሁም ከተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ጸሐፊ እና ከአውሮፓ ኅብረት ኃላፊዎች ጋር በስልክ ተወያይተዋል።

ፕሬዝዳንቱ በሶማሊያ የቻይና አምባሳደርንም በጽ/ቤታቸው ተቀብለው አነጋግረዋል።

ኢትዮጵያ ከራስ ገዟ ሶማሊላንድ ጋር የደረሰችው ስምምነት በቀይ ባሕር ላይ ለወደብ እና ለጦር ሠፈር ልማት የሚውል 20 ኪሎ ሜትር የባሕር ጠረፍ እንድታገኝ የሚያስችላት ሲሆን በምላሹ ሶማሊላንድ ከኢትዮጵያ አየር መንገድ ድርሻ እንዲሁም እንደ አገር ከአዲስ አበባ እውቅና እንደምታገኝ ተዘግቧል።

ታኅሣሥ 22/2016 ዓ.ም. ኢትዮጵያ እና ራስ ገዟ ሶማሊላንድ የደረሱት ስምምነት የሶማሊያን መንግሥት አስቆጥቷል።

የፕሬዝዳንት ሐሰን ሼክ ሞሐሙድ መንግሥት ስምምነቱንም “በሶማሊያ ነጻነት፣ ሉዓላዊነት፣ የግዛት አንድነት እና የሶማሊያ ፌደራላዊ ሪፐብሊክ ላይ የተቃጣ ጥቃት ነው” ብሎታል።

በተጨማሪም ፕሬዝዳንቱ ኢትዮጵያ ከሶማሊላንድ ጋር የገባችውን ስምምነት “ውድቅ የሚያደርግ” ያሉትን ሕግ ፈርመው አፅድቀዋል።

ሶማሊላንድን እንደ አንድ ግዛቷ የምትቆጥረው ሶማሊያ ጠ/ሚ ዐቢይ እና ፕሬዝደንት ሙሴ ቢሂ የገቡትን ስምምነት በመቃወም አምባሳደሯን ከአዲስ አበባ መጥራቷ ይታወሳል።   ዘገባው የቢቢሲ ነው፡፡

selegna

By selegna

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *