የራስ ገዟ ሶማሊላንድ መከላከያ ሚኒስትር በአፍሪካ ቀንድ ዋና መነጋጋሪያ የሆነው የኢትዮጵያና የሶማሊላንድን ስምምነት ተከትሎ መንበራቸውን ለቀዋል።

አብዲቃኒ ሞሐሙድ አተየ ሥልጣናቸውን የለቀቁት ሶማሊላንድ ከኢትዮጵያ ጋር ስምምነት ከመድረሷ በፊት የካቢኔ ሚኒስትሮች መማከር ነበረባቸው በሚል ነው።

በስምምነቱ መሠረት ሶማሊላንድ ባሕር የሚታከከውን ወደቧን ለባሕር በር አልባዋ ኢትዮጵያ ታከራያለች።

ሶማሊላንድ የራሷ ግዛት አድርጋ የምታስበው ሶማሊያዋ ይህ ዜና ካስቆጣቸው ሀገራት የመጀመሪያዋ ናት። ስምምነቱን “ተቀባይነት የሌለው” ስትል ገልጣ ነበር።

ዩናይትድ ስቴትስን ጨምሮ የአፍሪካ ኅብረትና የአውሮፓ ኅብረት ደግሞ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

ስምምነቱ ምን ይላል?

ኢትዮጵያና ሶማሊላንድ በገቡት የመግባቢያ ሰነድ ቃል በቃል ምን እንደሚል ለሕዝብ ይፋ ስላለሆነ ግልፅ አይደለም።

ለዚህም ነው ከኢትዮጵያና ከሶማሊላንድ መንግሥታት የተለያዩ መግለጫዎች ሲወጡ የሚስተዋሉት።

የመግባቢያ ሰነድ የግዴታ ተፈፃሚነት ያለው ሰነድ አይደለም። ነገር ግን ሶማሊላንድ ለኢትዮጵያ የባሕር በሯን ለማከራየት ዝግጁ እንደሆነች አሳይታለች።

ስምምነቱ ወታደራዊ ትብብርንም ያቀፈ ነው። ሶማሊላንድ የባሕር በሯን ለኢትዮጵያ ባሕር ኃይል ልታከራይ እንደሆነ ተናግራለች። ይህን አዲስ አበባም አረጋግጣለች።

በምላሹ ሶማሊላንድ ከአትራፊው የኢትዮጵያ አየር መንገድ አክሲዮን ልታገኝ እንደምትችል ተሰምቷል።

ነገር ግን ነገሮች የተወሳሰቡት ኢትዮጵያ ለሶማሊላንድ ዕውቅና ትሰጣለች ወይ? የሚለው ጥያቄ ሲነሳ ነው። የቀድሞዋ የብሪታኒያ ግኝ ግዛት የነበረችው ሶማሊላንድ ራስ ገዝ ከሆነች 30 ዓመት ቢያልፋትም ዕውቅና ማንም ሰጥቷት አያውቅም።

ስምምነቱ በተፈረመ ወቅት የሶማሊላንድ ፕሬዝደንት ሙሴ ቢሂ አብዲ ኢትዮጵያ ለሀገራቸው ወደፊት ዕውቅና ልትሰጥ እንደምትችል ተናግረው ነበር።

ኢትዮጵያ ይህን ጉዳይ እስካሁን አላረጋገጠችም። ባይሆን የኢትዮጵያ መንግሥት ከስምምነቱ በኋላ ባወጣው መግለጫ “ለሶማሊላንድን ዕውቅና መስጠትን በተመለከተ አቋም ለመያዝ” መስማማቱን ገልጧል።

አከራካሪ የሆነው ለምንድን ነው?

ሶማሊላንድ ማለት ለሶማሊያ የግዛት አንድነቷ አንድ ትልቅ አካል ናት። ሶማሊላንድ ከየትኛው ሀገር ጋር የምትገባው ስምምነት ያለሞጋዲሹ ይሁንታ መሆኑ ለሶማሊያ አደጋ ነው።

የመግባቢያ ሰነዱ በተፈረመ ማግስት ሶማሊያ ስምምቱን “የወረራ ድርጊት” ነው በማለት “ሰላምና መረጋጋትን” ሊያናጋ እንደሚችል ጠቅሳ ነበር።

በስምምነቱ እጅግ የተቆጣችው ሶማሊያ አምባሳደሯን ከአዲስ አበባ እስከ መጥራት ደርሳለች።

ባለፈው ሰንበት የሶማሊያው ፕሬዘደንት ሐሰን ሼኽ ሞሐሙድ “ሀገራችንን በምንችለው መንገድ እንመክታለን። የትኛውም ሊረዳን የሚችል አካል ካለ ለመተባበር ዝግጁ ነን” ብለዋል።

ወጣቶች “ሀገራችንን ለመጠበቅ ዝግጁ ሁኑ” የሚል መልዕክትም አሰምተዋል።

ባለፈው ሳምንት በሞጋዲሹ ስምምነቱን የሚቃወም ሰልፍ የተካሄደ ሲሆን በሺዎች የሚቆጠሩ አደባባይ ወጥተዋል።

ሶማሊላንድ ከሶማሊያ ነፃ መውጣቷን ያወጀችው በአውሮፓውያኑ 1991 ነው። ሀገር መሆን የሚያስችላት ቁመና አላት። ማለትም የፖለቲካ ሥርዓት፣ መደበኛ ምርጫ፣ የፖሊስ ኃይል እና የራሷ መገበያያ ገንዘብ አላት።

ባለፉት አሥርት ዓመታት ሶማሊያ በግጭት ስትናወጥ ሶማሊላንድ በተነፃፃሪው ሰላማዊ ጊዜ አሳልፋለች።

ነገር ግን የሶማሊላንድ ሀገር መሆን በየትኛውም ውጫዊ ወገን ዕውቅና አግኝቶ አያውቅም።

ሶማሊላንድ እንዳለችው ኢትዮጵያ ዕውቅና ብትሰጣት ይህ ውሳኔ በአፍሪካ ቀንድ ትልቅ ፖለቲካዊ አንድምታ ይኖረዋል።

ኢትዮጵያ ምን አለች?

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የባሕር በር የማግኘትን ጉዳይ የኅልውና ጉዳይ ነው ሲሉ ይገልጡታል።

ኢትዮጵያ ባሕር በር አልባ የሆነችው በአውሮፓውያኑ 1990ዎቹ መጀመሪያ ኤርትራ ነፃነቷን ስታውጅ ነው።

ከ100 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ ያላት ኢትዮጵያ ከዓለማችን ሀገራት በጣም ብዙ ሕዝብ ነገር ግን የባሕር በር የሌላት ናት።

የጠቅላይ ሚኒስትሩን መግለጫ ተከትሎ የኢትዮጵያ መንግሥት ምናልባት ዕቅዱን በጉልበት ሊያሳካ ይችላል የሚል ፍራቻ ነበር።

የኢትዮጵያ መንግሥት ከሶማሊላንድ ጋር የተገባውን ስምምነት “ታሪካዊ” ብሎ ገልጦት ዓላማው ሁሉን ነገር በሰላማዊ መንገድ መፈፀም እንደሆነ አሳውቋል።

“የመንግሥት አቋም በግልጥ እንደሚያሳየው ከማንም ጋር ጦርነት ውስጥ መግባት እንደማንሻ ነው” ይላል የኢትዮጵያ ኮሚዩኒኬሽን አገልግሎት መግለጫ።

ነገር ግን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ባለፈው እሑድ በኤክስ ገፃቸው ባስተላለፉት መልዕክት “ነገሮችን ከዚህ በፊት በለመድነው መንገድ ብናካሂዳቸው [ዕድሎች] ያመልጡን ነበር” ብለዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ አክለው ዓለማን ለማሳካት “ከተለመደው ወጣ ያለ አስተሳሰብ” አስፈላጊ መሆኑን በመልዕክታቸው ገልጠዋል።

ሌሎች ምን አሉ?

የአፍሪካ ሕብረት ኮሚሽን ሊቀ-መንበር ሙሳ ፋኪ ማሀማት፤ በኢትዮጵያ እና ሶማሊያ ዘንድ ያለው ውጥረት “እንዲረግብ” ጥሪ አቅርበዋል።

በኅብረቱ መርህ መሠረት “አየከረረ ያለው ውጥረት እንዲረግብ” በኮሚሽኑ ስም መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል

የዩናይትድ ስቴትስ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ማቲው ሚለር፤ ኢትዮጵያ ለሶማሊላንድ ዕውቅና የመስጠቷ ነገር ሀገራቸው እንደሚያሳስባት ገልጠዋል።

“ይህ በአፍሪካ ቀንድ ምን ሊያስከትል እንደሚችል ስጋት እንዳለን ለመግለጥ እንወዳለን” ሲሉ በአንድ ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ተናግረዋል።

በሶማሊያ ትልቅ ሚና የምትጫወተው ቱርክ “ለሶማሊያ የግዛት አንድነት፣ ሉዓላዊነት እና አንድነት” ያላትን “ቁርጠኝነት” ገልጣለች።

ሌላኛዋ ለሶማሊያ ያላትን ድጋፍ የገለጠችው ግብፅ ናት።

ፕሬዝደንት አብዱል ፋታህ አል-ሲሲ ለሶማሊያው አቻቸው ያላቸውን ድጋፍ አሳውቀዋል።

በሌላ በኩል የሶማሊያው ፕሬዝደንት ወደ አስመራ አቅንተው የኢትዮጵያ የቅርብ ጎረቤት ከሆነችው ኤርትራ ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ጋር እየመከሩ ነው።

የኢትዮጵያ እና የሶማሊላንድ ጠቅላይ ኢታማዦር ሹሞች ደግሞ በወታደራዊ ጉዳይ አብረው ለመሥራት ንግግር ጀምረዋል።ዘገባው የቢቢሲ ነው፡፡

selegna

By selegna

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *