በኢትዮጵያ ድርቅ ባጋጠማቸው ስድስት ክልሎች ውስጥ የሚገኙ 4 ሚሊዮን ገደማ ዜጎች አስቸኳይ የምግብ እርዳታ እንደሚያስፈልጋቸው የተባበሩት መንግስታት የሰብዓዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ቢሮ (ኦቻ) አስታወቀ።

በሀገሪቱ ለሚደረግ ድጋፍ የገንዘብ እርዳታ በቶሎ እንዲደረግለት የጠየቀው ቢሮው፤ በመጋቢት እና ሚያዝያ ወራት የሚመጣ የገንዘብ ድጋፍ “እጅጉን የዘገየ” ይሆናል ሲል አስጠንቅቋል።

ኦቻ ይህንን የገለጸው የኢትዮጵያን የሰብአዊ እርዳታ አቅርቦት እና ፍላጎት አስመልክቶ ትላንት ጥር 1፤ 2016 ዓ.ም ባወጣው መግለጫ ነው።

የማስተባበሪያ ቢሮው፤ በኢትዮጵያ በተከሰተው ድርቅ ምክንያት በአማራ፣ ትግራይ፣ ኦሮሚያ፣ አፋር፣ ደቡብ ኢትዮጵያ እንዲሁም ደቡብ ምዕራብ ክልሎች ውስጥ ዜጎች ከፍተኛ ችግር ውስጥ መውደቃቸውን በመግለጫው ጠቅሷል።

ኦቻ፤ ከኢትዮጵያ አደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽንን አገኘሁት ባለው መረጃ መሰረት ከፍተኛ የድርቅ ተጎጂዎች ባሉበት አማራ ክልል 1.7 ሚሊዮን ነዋሪዎች እርዳታ ጠባቂ መሆናቸውን ገልጿል።

በአማራ ክልል ድርቅ የተከሰተባቸው አካባቢዎች ሰሜን ጎንደር፣ ደቡብ ወሎ፣ ሰሜን ሸዋ እና ሰሜን ወሎ እንዲሁም የዋግ ኽምራ እና የኦሮሞ ብሔሰረብ አስተዳደር ዞኖች እንደሆኑ በመግለጫው ላይ ሰፍሯል።

በትግራይ ክልል ደግሞ በአምስት ዞኖች ውስጥ ባሉ 36 ወረዳዎች ድርቅ እንደተከሰተ የሰብዓዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ቢሮው መረጃ ያመለክታል።

በእነዚህ አካባቢዎች ውስጥ የሚገኙ 1.4 ሚሊዮን ዜጎች ከተያዘው ጥር ወር ጀምሮ አስቸኳይ የድንገተኛ ምግብ እርዳታ እንደሚያስፈልጋቸው ቢሮው አስታውቋል።

እንደ ኦቻ ገለጻ በትግራይ ክልል ውስጥ መታረስ ካለበት መሬት ውስጥ የታረሰው 49 በመቶው ብቻ ሲሆን ባለፈው የመኸር እርሻ ጊዜም የተሰበሰበው ሰብል መገኘት ከነበረበት ውስጥ 37 በመቶው ብቻ ነው።

ቢሮው፤ “[በአማራ እና አፋር ክልሎች] በወቅቱ የሰብአዊ እርዳታ ካልቀረበ በድርቅ እና በምግብ እጥረት ምክንያት በፍጥነት እያሽቆለቆለ ባለው የሰብአዊ ሁኔታ ሳቢያ አስከፊ ሁኔታ ሊፈጥር እንደሚችል የአማራ እና ትግራይ ክልሎች ባለስልጣናት አሳስበዋል” ሲል በሁለቱ ክልሎች የተጋረጠውን ስጋት አንስቷል።

የኦቻ መግለጫ እንደሚያመለክተው ድርቅ ባጋጠማቸው ክልሎች ውስጥ ከምግብ ዋስትና አለመረጋገጥ እና ከፍተኛ የምግብ እጥረት ባሻገር የወባ፣ ኩፍኝ እና ኮሌራ ወረርሽኝ መከሰቱ ተደራራቢ ችግር በመሆኑን በአካባቢዎቹ ያላውን ችግር አባብሷል።

በእነዚህ ክልሎች ውስጥ በድርቅ ምክንያት ያገጠመውን ችግር ለመቀልበስ የተቀናጀ የባለ ብዙ ዘርፍ ምላሽ እንደሚያስፈልግ ቢሮው አስገንዝቧል።

ለዚህም ሲባል የገንዘብ እርዳታ የሚያቀርቡ አካላት በተያዘው ጥር ወር የሚያደርጉትን ድጋፍ እንዲያሳድጉም ጥሪ አቅርቧል።

“በመከራ እና እጦት ውስጥ ያሉ ብዙ [ሰዎች] ችግራቸው ከተባባሰ በኋላ ከመጋቢት እስከ ሚያዝያ ባሉት ጊዜያት የሚመጣ ገንዘብ እጅጉን የዘገየ ይሆናል” ሲልም ቢሮው በፍጥነት የገንዘብ እርዳታ እንደሚያስፈልግ አሳስቧል።

የኢትዮጵያ አደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን በበኩሉ በትላንትናው ዕለት በሰጠው መግለጫ ከተያዘው ጥር እስከ መጋቢት ወር ድረስ በሀገሪቱ ውስጥ ያለውን የእርድታ ፍላጎት ለመሸፈን በቂ ዝግጅት መደረጉን አስታውቋል።

መግለጫውን የሰጡት ኮሚሽነር አምባሳደር ሽፈራው ተክለማርያም በእነዚህ ወራት ውስጥ ድጋፍ ለሚደረግላቸው 6.6 ሚሊዮን ዜጎች 9.2 ቢሊዮን ብር የሚሚገመት 1,118,700 ኩንታል ምግብ በመንግስትና በአጋር አካላት እንደሚቀርብ አብራርተዋል::ዘገባው የቢቢሲ ነው፡፡

selegna

By selegna

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *