በትግራይ ክልል በተከሰተው ድርቅ ምክንያት 223 ሺህ ገደማ ተማሪዎች ትምህርታቸውን ለማቋረጥ “ጫፍ ላይ” መድረሳቸውን የክልሉ ትምህርት ቢሮ አስታወቀ።

ቢሮው ድርቅ ባጋጠመባቸው አካባቢዎች በሚገኙ 625 ትምህርት ቤቶች ውስጥ የምገባ ፕሮግራም ለማስጀመር 365.1 ሚሊዮን ብር እንደሚያስፈልገው ገልጿል።

የትግራይ ክልል ትምህርት ቢሮ በሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት ምክንያት ከሁለት ዓመት በላይ ለሚሆን ጊዜ ተዘግተው የቆዩት የክልሉ ትምህርት ቤቶች በድጋሚ የመዘጋት ስጋት እንደተጋረጠባቸው ያስታወቀው ትላንት ማክሰኞ ታህሳስ 30፤ 2016 ዓ.ም ባወጣው መግለጫ ነው።

በአሁኑ ጊዜ በክልሉ ከአንድ ሚሊዮን በላይ ተማሪዎች በትምህርት ላይ እንደሚገኙ ለቢቢሲ የተናገሩት የክልሉ ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ዶ/ር ኪሮስ ግዑሽ፤ ከእነዚህ ውስጥ ድርቅ ባለባቸው አካባቢዎች ውስጥ የሚገኙት ተለይተው ጥናት መካሄዱን ገልጸዋል።

በህዳር እና ታህሳስ ወራት የተካሄደው ይህ ጥናት በ36 ወረዳዎች ውስጥ የሚገኙ 213 ቀበሌዎች “በከፍተኛ መጠን” በድርቅ መጠቃታቸውን አሳይቷል።

በእነዚህ አካባቢዎች ውስጥ የሚገኙት 625 ትምህርት ቤቶች በአሁኑ ጊዜ 222,940 ተማሪዎችን በማስተማር ላይ እንደሚገኙ የትምህርት ቢሮ ኃላፊው ገልጸዋል።

ዶ/ር ኪሮስ እንደሚያስረዱት እነዚህ ተማሪዎች “የእለት ጉርስ በማጣታቸው በከፍተኛ መጠን ትምህርት ለማቋረጥ ጫፍ ላይ” ደርሰዋል።

“በእነዚህ 36 ወረዳዎች ብዙ ህጻናት ናቸው ያሉት። እኛ ግን ትኩረት ያደረግነው ትምህርት ጀምረው የነበሩ፤ [ነገር ግን] በዚህ ርሃብ ምክንያት ትምህርት ለማቋረጥ ጫፍ ላይ ያሉትን ነው” ብለዋል።

የክልሉ ትምህርት ቢሮ በድርቅ ምክንያት ተማሪዎች ትምህርት እንዳያቋርጡ ለማድረግ በመፍትሄነት ያቀረበው አማራጭ የትምህርት ቤት ምገባ ስርዓትን ማስጀመር መሆኑን ዶ/ር ኪሮስ ገልጸዋል።

“ተማሪዎቹ ቢያንስ በቀን አንድ ጊዜ ምግብ ቢያገኙ ትምህርት ቤት ቁጭ ብሎ ለመዋል የሚያስችል ትንሽ አቅም ያገኛሉ” ያሉት የትምህርት ቢሮ ኃላፊው፤ በመጪዎቹ ስድስት ወራት ይህንን ምገባ ለማከናወን 365,175,720 ብር እንደሚያስፈልግ አስታውቀዋል።

በትምህርት ቢሮው እቅድ መሰረት ለአንድ ተማሪ ምገባ በቀን ለመመደብ የታሰበው የገንዘብ መጠን 12 ብር እንደሆነ በመገለጫው ላይ ተጠቅሷል።

ቢሮው በዚህ መግለጫው የምገባ ፕሮግራሙን ለማስጀመር የሚያስፈልገውን ገንዘብ ለማግኘት የፌደራል መንግሥት፣ ዓለማቀፉ ማህበረሰብ እና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ድጋፍ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርቧል።

የክልሉ ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ዶ/ር ኪሮስ፤ “ለተማሪዎች ምገባ ተብሎ የሚመደብ 365 ሚሊዮን ብር ለፌደራል መንግስት ትንሽ ገንዘብ ነው። ሌሎች ባለ ድርሻ አካላት ሲጨመሩበት ደግሞ [ለማሰባሰብ] ከባድ ገንዘብ ነው የሚል እምነት የለንም” ሲሉ የተለያዩ አካላት ድጋፍ እንዲያደርጉ እንደሚጠበቅ አስረድተዋል።

የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር በክልሉ የተከሰተውን ድርቅ ለመቋቋም የፌደራል መንግስትን እርዳታ ሲጠይቅ ይህ የመጀመሪያ ጊዜው አይደለም።

ከሶስት ሳምንት ገደማ በፊት የጊዜያዊ አስተዳደሩ ፕሬዝዳንት አቶ ጌታቸው ረዳ የፌዴራል መንግሥቱና ዓለም አቀፉ ማሕበረሰብ በክልሉ የተከሰተውን ድርቅ ለመግታት እጃቸውን እንዲዘረጉ ጥሪ አቅርበው ነበር።

በክልሉ ያጋጠመው ሁኔታ ከ1977ቱ ድርቅ በኋላ ታይቶ የማይታወቅ እንደሆነ የገለጹት አቶ ጌታቸው፤ “በትግራይ ረሃብ እና ሞት እያንዣበበ ነው” ሲሉ ነዋሪዎች በከፍተኛ ቸግር ውስጥ መሆናቸውን አስታውቀዋል።

ድርቁ ከክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር አቅም ውጪ መሆኑን ጠቅሰውም የፌደራል መንግስት እና ሌሎቸ አካላት አፋጣኝ ምላሽ እንዲሰጡ መጠየቃቸው ይታወሳል።

ከዚህ ጥሪ መቅረብ በኋላ ለጋዜጠኞች መግለጫ የሰጡት የመንግሥት ኮሚዩኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዶ/ር ለገሰ ቱሉ ግን በክልሉ ያለው ድርቅ “ከ77ቱ ርሃብ እና ድርቅ ጋር ወደ የሚስተካከል ድርቅ እና ርሃብ እየተሸጋገረ ነው” መባሉ “ፈጽሞ ስህተት” እንደሆነ ተናግረው ነበር።

ዶ/ር ለገሰ፤ “አጋር አካላት የእርዳታ አቅርቦት ቢያቆሙም፤ መንግሥት ፕሮጀክቶቹን አጥፎ፣ አስፈላጊውን በጀት መድቦ የሰብአዊ እርዳታ ከሌሎች አካባቢዎች በተሻለ ብቻ ሳይሆን በበቂ መጠን ለትግራይ እያቀረበ ይገኛል” ሲሉም የፌደራል መንግስት እያደረገ ያለውን ድጋፍ ገልጸዋል። ዘገባው የቢቢሲ ነው፡፡

selegna

By selegna

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *