የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ ከሶማሊላንድ ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ሜጄር ጄኔራል ኑህ ኢስማኤል ታኒ ጋር በወታደራዊ ትብብር ዙሪያ መወያየታቸው ተገለጸ።

የመከላከያ ሠራዊት በፌስቡክ ገጹ እንዳለው፣ የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላና የሶማሊላንድ ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ሜጄር ጄኔራል ኑህ ኢስማኤል ታኒ በወታደራዊ ትብብር ዙሪያ አብረው ለመሥራት የሚያስችላቸውን ውይይት አድርገዋል።

“በሶማሊላንድ ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ሜጄር ጄኔራል ኑህ ኢስማኤል ታኒ የተመራ ልዑክ በመከላከያ ጠቅላይ መምሪያ ሲደርስ በጄኔራል መኮንኖች አቀባበል ተደርጎለታል” በማለትም ተገልጿል።

ስለ ውይይታቸው ይዘት በመከላከያ ሠራዊት የፌስቡክ ገጽ ላይ በዝርዝር የተባለ ነገር የለም።

ኢትዮጵያ ከሶማሊያ ተገንጥላ ራስ ገዝ ከሆነችው ሶማሊላንድ ጋር ባለፈው ሳምንት የደረሰችበት ስምምነት በቀይ ባሕር ላይ ለወደብ እና ለጦር ሠፈር ልማት የሚውል 20 ኪሎ ሜትር የባሕር ጠረፍ እንድታገኝ የሚያስችላት እንደሆነ ተገልጿል።

በስምምነቱ መሠረት፣ በምላሹ ሶማሊላንድ ከኢትዮጵያ አየር መንገድ ድርሻ እንዲሁም እንደ አገር ከኢትዮጵያ ዕውቅና እንደምታገኝ ተዘግቧል።

በዛሬው ዕለት የሶማሊያ ፕሬዝዳንት ሐሰን ሼይክ ሞሐሙድ ለይፋዊ የሥራ ጉብኝት ኤርትራ፣ አሥመራ ገብተዋል።

የኤርትራው የማስታወቂያ ሚኒስትር አቶ የማነ ገብረመስቀል በኤክስ ገጻቸው፣ የሶማሊላንድ ፕሬዝዳንት ሐሰን ሼይክ ሞሐሙድ እና የኤርትራው ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ “በሁለትዮሽ ጉዳዮች እንዲሁም በቀጠናዊና ዓለም አቀፍ ጉዳዮች ዙርያ” እንደሚወያዩ ገልጸዋል።

ሶማሊላንድ እአአ 1991 ላይ ራሷን ከሶማሊያ በመገንጠል ነጻነቷን ብታውጅም እስካሁን ከኢትዮጵያ በስተቀር የትኛውም አገር እስካሁን ዕውቅና ሳይሰጣት ቆይቷል።

ኢትዮጵያ ከሶማሊያ ተገንጥላ ራስ ገዝ ከሆነችው ሶማሊላንድ ጋር የባሕር በር ማግኘት ያስችላታል የተባለውን የመግባቢያ ሠነድ መፈረሟን ተከትሎ ፕሬዝዳንት ሐሰን ሼይክ ሞሐሙድ ከተለያዩ መሪዎች ጋር የስልክ ውይይቶችን ሲያደርጉ ቆይተዋል።

ከዚሁ ጋር በተያያዘ ኢትዮጵያ እና ሶማሊላንድ የተፈራረሙትን የመግባቢያ ሰነድ በመቃወም የሶማሊላንድ መከላከያ ሚንስትር አብዲጋኒ መሐሙድ አቴዬ በገዛ ፍቃዳቸው ሥልጣን መልቀቃቸውን ይፋ ማድረጋቸው ይታወሳል።

የሶማሊያው ፕሬዝደንት ሐሰን ሼክ ሞሐሙድ በበኩላቸው ኢትዮጵያ ከሶማሊላንድ ጋር የገባችውን ስምምነት “ውድቅ የሚያደርግ” ያሉትን ሕግ ፈርመው አጽድቀዋል።

ፕሬዝደንቱ በኤክስ ገጻቸውን በለጠፉት መልዕክት “የኢትዮጵያ መንግሥት እና ሶማሊላንድ የገቡትን የመግባቢያ ሰነድ ውድቅ የሚያደርግ ሕግ ፈርሜያለሁ” ብለዋል።

ከአንድ ሳምንት በፊት ሰኞ ታኅሣሥ 22/2016 ዓ.ም. ኢትዮጵያ ከራስ ገዟ ሶማሊላንድ ጋር የተፈራረመችው የመግባቢያ ሰነድ የሶማሊያን መንግሥት አስቆጥቷል።

የፕሬዝዳንት ሐሰን ሼክ ሞሐሙድ መንግሥት ስምምነቱንም “በሶማሊያ ነጻነት፣ ሉዓላዊነት፣ የግዛት አንድነት እና የሶማሊያ ፌደራላዊ ሪፐብሊክ ላይ የተቃጣ ጥቃት ” ብሎታል።

የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ጽሕፈት ቤት ከስምምነቱ መፈረም ጋር ተያይዞ ባወጣው መግለጫ፤ “የመግባቢያ ሰነዱ ኢትዮጵያ የባሕር በርን በአስተማማኝ ሁኔታ ለመጠቀም ያላትን ፍላጎት ዕውን ለማድረግ መንገዱን ይጠርጋል” ማለቱ ይታወሳል።  ዘገባው የቢቢሲ ነው፡፡

selegna

By selegna

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *