የኤርትራ ፕሬዝደንት ኢሳያስ አፈወርቂና የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ግንኙነት ከፕሪቶርያ ስምምነት በኋላ እንደ ቀድሞው አለመሆኑን ብዙዎች ይናገራሉ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በሐምሌ ወር 2018 ዓ.ም ወደ አሥመራ በተጓዙበት ወቅት “ፕሬዝደንት ኢሳያስ. . . ለኢትዮጵያ ሕዝብ ትልቅ ክብርና ፍቅር አለው” ካሉ በኋላ፣ “ለኢትዮጵያ ልማትና ሰላም የሚጨነቅ፣ በሁለቱም አገራት ግንኙነት ብቻ ሳይሆን ለቀጠናው ሃገራት የሚያስብ መሪ” መሆናቸውን መስክረው ነበር።

በዚህ ወቅትም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ፕሬዝደንት ኢሳያስ መኖርያ ቤት አጃቢዎቻቸውን ጨምሮ ቡና ሲጋበዙ በመገናኛ ብዙኅን ላይ ታይቷል።

ፕሬዝዳንት ኢሳያስ በበኩላቸው ከ20 ዓመታት በኋላ በሐምሌ 15 ቀን 2018 ዓ.ም አዲስ አበባ ሲደርሱ፣ የጠበቃቸው ትልቅ የሕዝብ አድናቆት፣ ያልተለመደ የደስታ ስሜት እንዲያሳዩ ከማድረጉም በላይ የብዙዎች መነጋገርያ ሆኖ ነበር።

“ልቤ ውስጥ ያለውን ስሜት መግለጽ ከበደኝ. . . ታሪክ እየተሰራ ነው። [በመካከላችን] ጥላቻንና ቂም፣ ውድመትን ለማስፋፋት የሚደረገውን ሴራ በማክሸፍ በሁሉም ዘርፍ ለልማት፣ ለብልጽግና እና መረጋጋት በጋራ ወደ ፊት ለመራመድ ቆርጠናል” በማለት ነበር በወቅቱ መልዕክት ያስተላለፉት።

በጠቅላይ ሚኒስትር የመጀመሪያዎቹ ሁለት የስልጣን ዓመታት ውስጥ ብቻ ሁለቱ መሪዎች ቢያንስ 14 ጊዜ ከአዲስ አበባ ወደ አሥመራ፥ ከአሥመራ ወደ አዲስ አበባ ተመላልሰዋል።

ይህ ግን የመቶ ሺህዎችን ሕይወት ከቀጠፈው የትግራይ ጦርነት በስምምነት መጠናቀቅ በኋላ ፈጽሞ ሊታይ አልቻለም።

ከሰላም ጓዶች እስከ የትግል አጋሮች

እ.ኤ.አ. ታህሳስ 10፣ 2019 ዓ.ም ዶ/ር ዐቢይ የኖቤል የሰላም ሽልማትን በተቀበሉበት ወቅት፣ በሁለቱ ሀገራት መካከል ለተደረገው የሰላም ስምምነት የፕሬዝዳንት ኢሳያስ ሚና ወሳኝ መሆኑን ተናግረዋል።

“ይህን ሽልማት የተቀበልኩት በባልደረባዬና የሰላም አጋሬ በፕሬዚደንት ኢሳያስ ስም ጭምር ነው። ጦርነት የሁሉም ተሳታፊዎች የውድቀት ምልክት ነው . . . ጦርነት ሰዎችን ምህረት የለሽ፣ ጨካኝ፣ ቁጡና ጨካኝ ያደርጋቸዋል” በማለት፣ ከመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ በመጥቀስ ሰይፋቸውን ወደ ማረሻ፣ ጦራቸውንም ወደ ማጭድ እንደሚቀይሩ ተናግረው ነበር።

ብዙም ሳይቆይ ግን ሁለቱ መሪዎች የጦር ሠራዊታቸውን በጋራ በማቀናጀት ህወሓት ወደ ሚያስተዳድራት ትግራይ ዘመቱ።

ከፕሪቶሪያ ስምምነት በኋላም ቢሆን አንዳንድ የሁለቱም ሀገራት ከፍተኛ የጦር አዛዦች “እንደ አንድ አካል” በመሆን ህወሓትን መዋጋታቸውና ወታደሮቻቸውም “በአንድ ጉድጓድ ውስጥ እንደተቀበሩ” ሲናገሩ ተደምጠዋል።

በሁለት ዓመታት ውስጥ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን በቀጠፈው የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት በፕሪቶሪያ በተደረሰው ስምምነት ምክንያት መቋጨቱ ለፕሬዝዳንት ኢሳያስ እንዳልተዋጠላቸው ጉዳዩን በቅርበት የሚከታተሉ ይናገራሉ።

በቻይና ተመድበው ሲሰሩ የነበሩና የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድን መንግሥት አካሄድ በመቃወም ስደት የመረጡት አምባሳደር እውነቱ ብላታ፣ “የሁለቱ መሪዎች ግንኙነት በመርህ እና በህጋዊ ተቋማት ላይ የተመሰረተ ሳይሆን ህወሓትንና የፌዴራል ስርዓቱን ለማጥፋት ያለመ ነው” ሲሉ ይተቻሉ።

“ህወሓት በፖለቲካዊ አግባብ ከመግደል ይልቅ ጦርነትን መምረጣቸው ትልቅ ስህተት ነው” በማለት ውሎ አድሮ ሁለቱንም ማቃቃሩ አክለዋል።

የፕሪቶሪያ ስምምነት፡ ሰላምና መሰናክሎቹ

የኤርትራ ሕዝባዊ ግንባር ከፍተኛ አመራርና የቀድሞ ዲፕሎማት የነበሩት አምባሳደር አብደላ አደም በበኩላቸው በዐቢይ እና በኢሳያስ መካከል ያለው ግንኙነት “የግል” እንደሆነ ከዚህ በፊት በኢሳያስ እና የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ መካከል የነበረውን በመጥቀስ “ታሪክ ራሱን እንደደገመ” ይናገራሉ።

የሁለቱ አገራት መሪዎች ግንኙነት ተመስርቶ የነበረው የጋራ ጠላት ባሉት ህወሓት ላይ ነው የሚሉት አምባሳደር አብደላ፣ በሁለቱ ሀገራት መካከል መደበኛ የሁለትዮሽ ዲፕሎማሲያዊ እና ኢኮኖሚያዊ ግንኙነት ለመፍጠር ያለመ አልነበረም ይላሉ።

“በኤርትራና በኢትዮጵያ መካከል እንደ የድንበር ማካለል፣ የኢኮኖሚ ስምምነት እና ግንኙነት የመሳሰሉ ዋና ዋና ጉዳዮች አሉ። ግን ይህ ሁሉ ወደ ጎን ተትቶ ቆይቷል። ህወሓት ለማጥፋት ያለሙት ውጥን ‘እንቅፋት’ ስለገጠመው ሳይሳካ ቀርቷል” የሚሉት ዲፕሎማቱ፣ ለዚህም ቀጥተኛ የአሜሪካ ጣልቃ ገብነት እና ጫና ዋና ምክንያት እንደሆነ ይገልጻሉ።

ከዚህ ባሻገር፤ ኤርትራ ከፕሪቶሪያ የተኩስ አቁም ስምምነት በመገለሏ ፕሬዝደንት ኢሳያስ ክህደት እንደተሰማቸው ያስረዳሉ።

ይህንንም ሲያብራሩ ፕሬዝደንት ኢሳያስ በአፍሪካ ሕብረት፣ በአሜሪካ እና በኢጋድ አደራዳሪነት የተደረገውን ስምምነት “የማስተጓጎል ዘዴ” ሲል መውቀሳቸውን ይጠቅሳሉ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በመካከላቸው ያለውን አለመግባባት ለመፍታት ሙከራ ማድረጋቸውን የሚናገሩት አምባሳደር አብደላ፣ ከኤርትራ መሪ በኩል አዎንታዊ ምላሽ አለማግኘታቸውን ይገልጻሉ።

የአማራ ክልል ግጭትና የኤርትራ አቋም

ከትግራይ ጦርነት በኋላ ወደ ተመሳሳይ ደም አፋሳሽ ግጭት የገባው የአማራ ክልል ሁኔታ ቢያንስ በሁለቱ መሪዎች መካከል አለመተማመን ሊፈጥር የሚችል አደገኛ ሁኔታ ነው ይላሉ አምባሳደር አብደላ።

ኤርትራ ህወሓት መራሹን የኢህአዴግን አገዛዝ ለማስወገድ እንደ ግንቦት 7 ያሉ ታጣቂ ቡድኖችን እና ተቃዋሚዎችን ስታሰለጥንና ስታስታጥቅ ነበረ።

ምንም እንኳ የፋኖ አመራሮች ትጥቅና ቁሳቁሶች ከሕዝባቸው እንደሚያገኙ እና ከኤርትራ ምንም አይነት እርዳታ እንደማያገኙ ቢናገሩም ይህ ለቀድሞው የኤርትራ አምባሳደር የሚዋጥ አልሆነም።

የፋኖ የፖለቲካ ክንፍ ኃላፊ መሆኑን የሚናገረው አቶ አስረሰ ማሬ ዳምጤ ለቢቢሲ በሰጠው ቃል ግን፤ ዋነኛ የመሳሪያና ስንቅ ምንጫቸው በክልሉና ከሀገር ውጭ በሚገኘው ህዝባቸው መሆኑን ተናግሯል።

በጎጃም አካባቢዎች የሚንቀሳቀሰው የፋኖ ክፍል ምክትል አዛዥ የሆነው ማንችሎት እሱባለው በበኩሉ፤ “የማጠልሸት ክስ” በማለት ከኤርትራ የሚያገኙት ድጋፍ እንደሌለ ገልጿል።

“በክልሉ ሰፊ የህዝብ ድጋፍ አለን፤ በህዝብ ነው የምንመራው። ሕዝባዊ ትግል ነው የምናካሂደው። የሚቀልበንና የሚደግፈን ደግሞ ሕዝብ ነው . . . [ከኤርትራ ድጋፍ ታገኛላችሁ] ብለው የሚከሱን ምንም ማስረጃ ሊያቀርቡ አይችሉም”።

አምባሳደር እውነቱም እስከ አሁን ኤርትራ በአማራ ክልል እየተካሄደው ባለው ግጭት ውስጥ ስላላት አስተዋጽኦ የሚያረጋግጥ ተጨባጭ ማስረጃ እንደሌለ ይናገራሉ።

አምባሳደር አብደላ ግን፤ ኤርትራ ለአማራ ኃይሎች በግልጽ ድጋፍ ባትሰጥም፤ በሁለቱም ኃይሎች መካከል የነበረው ግኑኝነት ግምት ውስጥ በማስገባት ግን እጇን አጣጥፋ አትቀመጥም በማለት ይከራከራሉ።

ለዚህም እንደምክንያት የሚጠቅሱት የሰሜኑ ጦርነትን ተከትሎ በአማራ ኃይሎች ስር በሚገኘው ምዕራብ ትግራይ በኩል ኤርትራ ከአማራ ክልል ጋር የሚያገናኛት መስመር መኖሩን ነው።

ሆኖም፤ የኤርትራ መንግሥት ለአማራ ተቃዋሚ ኃይሎች ቀጥታዊ ድጋፍ መስጠት ከጀመረ፤ በሁለቱም አገራት መሪዎች መካከል ግጭት ሊነሳ እንደሚችል አስተያየት ሰጪዎቹ ይናገራሉ።

የባሕር በር፤ የዐቢይ መግለጫዎችና የኢሳያስ ዝምታ

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ በቅርቡ በቀይ ባሕር ወደብ ላይ የሰጡት መግለጫ ብዙ ኤርትራውያንን ያስቆጣ እና ያነጋገረ ነበር።

“120 ሚሊዮን ሕዝብ የጂኦግራፊያዊ እስረኛ ሆኖ ሊቀጥል አይችልም” በማለት ነበር በጥቅምት ወር ለሕዝብ ተወሰካዮች ምክር ቤት በሰጡት ማብራሪያ ላይ ኢትዮጵያ የባሕር በር የማግኘት ጉዳይ የሕይወትና የሞት ጉዳይ ነው ያሉት።

በወቅቱ የኤርትራ መንግሥት በማስታወቅያ ሚኒስቴሩ በኩል ባወጣው አጭር መግለጫ ፣ የባሕር በር እና ተያየዥ ጉዳዮች ውይይት ወደ ሚደረግባቸው መድረኮች የመግባት ፍላጎት እንደሌለው ገልጿል።

በቀጠናው ተጽእኖ ፈጣሪ የመሆን ምኞት እንዳላቸው የሚነገርላቸው ፕሬዝዳንት ኢሳያስ፣ ዶ/ር ዐቢይ ለሰጡት ንግግር እስካሁን ይፋዊ ምላሽ አልሰጡም።

አምባሳደር እውነቱ የዐቢይ አካሄድ ያልተለመደ መሆኑ በመግለጽ፤ ጉዳዩ በመሪዎች ደረጃ የሁለቱንም ሀገራት ጥቅም ባስከበረ መልኩ ውይይት ሊካሄድበት ይገባል ይላሉ።

“እንደ አለመታደል ሆኖ ግን ሁለቱም መሪዎች ከግል ስልጣንና ስግብግብነት የዘለለ ራዕይ ስለሌላቸው ወደ አላስፈላጊ ውጥረት ሊያመራ ይችላል” በማለት ጉዳዩ አላስፈላጊ አለመረጋጋት እንዳያስከትል በዓለም አቀፍ ሕግ፣ አሰራር እና መርሆች ማዕቀፍ መፈታት እንዳለበት ይመክራሉ።

አምባሳደር አብደላ በበኩላቸው ሁለቱ መሪዎች በቀጠናው የበላይ ለመሆን ያላቸው ፍላጎት እርስ በርስ እንዲፎካከሩ ስለሚያደርግ ሊጋጩ ይችላሉ ባይ ናቸው።

አምባሳደር እውነቱ ግን “የዐቢይ ህልሞች መሰረት የሌላቸውና የማይደግማቸው” ስለሆኑ በቁም ነገር መታየት የለባቸውም ይላሉ።

የሁለቱ አገራት ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት በምን ደረጃ ላይ ነው?

በታህሳስ 2018 በኢትዮጵያ የኤርትራ አምባሳደር ሆኖ የተሾመው ሰመረ ርዕሶም በ2022 መጋቢት ወር ላይ “የስራው ጊዜ ስላበቃ” ከአገሪቷ መሰናበቱ ይታወሳል።

የትምህርት ሚኒስትር በነበረበት ወቅት የዲፕሎማት ስልጣን ጨምሮ ይሰራ የነበረው አምባሳደር ሰመረ ወደ ኤርትራ ከተመለሰ በኋላ ከሕዝብ ዕይታ ርቋል።

በተመሳሳይ ሁኔታ ኢትዮጵያ በታህሳስ ወር 2019 ላይ የኢትዮጵያ አምባሳደር ሆነው ወደ አሥመራ ያቀኑት ሬድዋን ሁሴን፣ ወደ አገራቸው ከተመለሱ በኋላ ኢትዮጵያ በምትኩ ሌላ አምባሳደር አልላከችም።

የሁለቱንም አገራት ይፋዊ ግንኙነቱ ያለበትን ደረጃ በግልጽ የሚታወቅ ባይሆንም፤ በ2018 ዓ.ም የጀመረው የኢትዮጵያ አየር መንገድ በረራዎች ግን ቀጥለዋል።

ለአጭር የተከፈቱት ድንበሮች ግን በስምንት ወራት ውስጥ ተዘግተዋል።

ለረጅም ጊዜ የቆየው የቡሬ – ደባይሲማ ድንበር በሚያዝያ 22 2019 ሙሉ በሙሉ ተዘግቷል።

በፕሪቶሪያ ስምምነት ያልተደሰቱት ፕሬዚዳንት ኢሳያስ በኢትዮጵያ ያካሄዱት የመጨረሻ ይፋዊ ጉብኝት የትግራይ ጦርነት ከመጀመሩ ከሁለት ሳምንታት በፊት፣ ጥቅምት 13 2020 ነበር።

ለሶስት ቀናት ባደረጉት በዚህ ጉብኝት የህዳሴ ግድብና ሌሎች የልማት ስራዎችን በመጎብኘት ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ጋር መወያየታቸው ተዘግቧል።

የፕሪቶሪያን የሰላም ስምምነት በኋላ ደግሞ በብሄራዊ ደህንነት ኃላፊ በብርጋዴር ጄኔራል አብርሃ ካሳ የተመራ የልዑካን ቡድን በሚያዝያ 2023 መጀመሪያ ላይ ኢትዮጵያን ጎብኝቷል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ እና ፕሬዝደንት ኢሳያስ ለመጨረሻ ጊዜ በአካል የተገናኙት እ.ኤ.አ ሐምሌ 12 2023 የሱዳን መሪዎች ግብጽ ላይ ተሰብስበው በካርቱም እየተካሄደ ስላለው ጦርነት ለመወያየት ተገኙ በተባሉበት ወቅት ነው።

የጠቅላይ ሚኒስትሩ የብሔራዊ ደኅንነት አማካሪ አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን በወቅቱ እንደተናገሩት “ሁለቱ መሪዎች በመጪው የፕሬዚደንት ኢሳያስ ጉብኝት ተጨማሪ የሁለትዮሽ ውይይት ለማድረግ ቃል ገብተዋል” ብለው ነበር።

ይሁን እንጂ ይህ ሳይተገበር አምስት ወራት አልፈዋል።

አንዳንድ ተንታኞች የአምባሳደር ሬድዋን መግለጫ የሻከረውን ግንኙነት ለማሻሻል የተሰጠ ነው ቢሉም፣ ፕሬዚደንት ኢሳያስ ያካሄዱታል የተባለው ጉብኝት እስካሁን ያልተካሄደበት ምክንያት ግልጽ አይደለም። ዘገባው የቢቢሲ ነው፡፡

selegna

By selegna

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *