ከትናንት በስትያ ታኅሣሥ 24/ 2016 ዓ. ም. በአማራ ክልል፣ ደብረ ብርሃን ከተማ በተደረገው የተኩስ ልውውጥ ቢያንስ አምስት ሰዎች ሕይወታቸው እንዳለፈ እና የሆስፒታል ባልደረባን ጨምሮ አራት ሰዎች እንደቆሰሉ የደብረ ብርሃን ኮምፕርሄንሲቭ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ምንጭ ለቢቢሲ ተናገሩ።

ቢቢሲ ያነጋገራቸው ሁለት የከተማዋ ነዋሪዎች በበኩላቸው ከትናንት በስትያ ከሰዓት እና ትናንት ቢያንስ የሰባት ሰዎች የቀብር ሥነ ሥርዓት መከናወኑን ገልጸዋል።

በደብረ ብርሃን ከተማ ባሳለፍነው ረቡዕ እስከ ቀኑ አጋማሽ የቆየ የተኩስ ልውውጥ መካሄዱን የከተማዋ ተቀዳሚ ከንቲባ አቶ በድሉ ውብሸት እና ነዋሪዎች ለቢቢሲ ገልጸው ነበር።

እንደ ነዋሪዎች ገለጻ፣ የፋኖ ታጣቂዎች እና የፀጥታ ኃይሎች ከትናንት በስትያ ጠዋት አንስቶ የተኩስ ልውውጥ ያካሄዱት “በተለያዩ የከተማዋ አቅጣጫዎች” ነው።

የረቡዕ ዕለቱን ሁነት አስመልክቶ ትናንት ታኅሣሥ 23/ 2016 ዓ. ም. መግለጫ ያወጣው የደብረ ብርሃን ከተማ እና አካባቢው ኮማንድ ፖስት “ጽንፈኛ” ሲል የጠራው ኃይል “ጉዳት ለማድረስ በማሰብ” ወደ ከተማዋ “በአቋራጭ” ገብቶ እንደነበር አስታውቋል።

ይህንን ተከትሎም የመከላከያ ሠራዊት እንዲሁም የአማራ ክልል አድማ ብተና እና የከተማዋ የሰላም አስከባሪ ኃይሎች በወሰዱት “የተቀናጀ ኦፕሬሽን በአጭር ጊዜ ከተማው ወደ መደበኛ እንቅስቃሴው” መመለሱንም ኮማንድ ፖስቱ ገልጿል።

ኮማንድ ፖስቱ “የፀጥታ ችግር” ሲል በጠራው የትናንት በስትያው ክስተት “በሰው ሕይወት ላይ ጉዳት” መድረሱን በመግለጫው አስታውቋል።

ይሁንና መግለጫው በምን ያህል ሰዎች ላይ ጉዳት እንደደረሰ በቁጥር አልጠቀሰም።

ቢቢሲ ያነጋገራቸው የደብረ ብርሃን ኮምፕርሄንሲቭ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ምንጭ አራት ሰዎች ሕይወታቸው ካለፈ በኋላ ወደ ሆስፒታሉ እንደተወሰዱና አንድ ግለሰብ ደግሞ ተጎድቶ ሄዶ ሕይወቱ ማለፉን ተናግረዋል።

ሕይወታቸው ካለፈ በኋላ የተወሰዱት አራት ግለሰቦች “በአጀብ” ወደ ሆስፒታሉ መግባታቸውን የሚገልጹት የቢቢሲ ምንጭ፤ በዚህም ምክንያት የፀጥታ ኃይል አባላት ናቸው የሚል ግምት እንዳላቸው ተናግረዋል።

ወደ ሆስፒታሉ ከገባ በኋላ ሕይወቱ ያለፈው ተጎጂ በአንጻሩ ሲቪል ግለሰብ መሆኑን አመልክተዋል።

ይህንን ግለሰብ ጨምሮ ተጎድተው ወደ ሆስፒታሉ የተወሰዱ ንጹሃን ዜጎች ቁጥር አራት መሆኑን የሚናገሩት የቢቢሲ ምንጭ፤ ከእነዚህ ውስጥም “አስጊ” በሚባል ደረጃ የተጎዳው ታካሚ የሆስፒታሉ ባልደረባ መሆኑን አብራርተዋል።

የቢቢሲ የሆስፒታል ምንጭ እንደሚያስረዱት፣ ከፍተኛ ጉዳት የደረሰበት የሆስፒታሉ ባልደረባ ለተሻለ ሕክምና አዲስ አበባ ከተማ በሚገኘው የቃጠሎ፣ የአደጋና ድንገተኛ ሆስፒታል (አቤት) ተዛውሯል።

ይህ ግለሰብ እና ቀላል ጉዳት የደረሰባቸው ቀሪዎቹ ንጹሃን ዜጎች የቆሰሉት “በተባራሪ ጥይት” መሆኑንም አክለዋል።

ቢቢሲ በከተማዋ ከሚገኙ ሌሎች የጤና ተቋማት ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት ያደረገው ሙከራ አልተሳካም።

ይሁንና ወደ ሆስፒታል ከተወሰዱ ግለሰቦች ባሻገር ሌሎችም ሰዎች በረቡዕ ዕለቱ የተኩስ ልውውጥ ምክንያት ሕይወታቸው እንዳለፈ ሁለት የከተማዋ ነዋሪዎች ለቢቢሲ ተናግረዋል።

አንድ የከተማዋ ነዋሪ፤ “በተባባሪ ጥይት” ተመትተው ሕይወታቸው ያለፈ ንጹሃን ዜጎች ትናንት የቀብር ሥነ ሥርዓታቸው መከናወኑን ገልጸዋል።

ሌላ የከተማዋ ነዋሪ በበኩላቸው፤ “ከትናንት በስትያ ከሰዓትም የተቀበሩ አሉ። እኔ የማውቃቸው ልጆች መሞታቸውን ሰምቻለሁም፤ አውቄያለሁም። […] ፖሊስ፣ አድማ በታኝ፣ ጥበቃዎችን ጨምሮ [ቀብራቸው የተፈጸመው] ቢያንስ ከአስር በላይ ሰዎች ይሆናሉ” ሲሉ ከፍ ያለ ቁጥር ጠቅሰዋል።

ቢቢሲ ጉዳት ስለደረሰባቸው ሰዎች አጠቃላይ የአሐዝ መረጃ ለማግኘት ወደ ደብረ ብርሃን ከተማ ተቀዳሚ ከንቲባ አቶ በድሉ ያደረገው የስልክ ጥሪ አልተሳካም።

ረቡዕ ዕለት የተካሄደውን የተኩስ ልውውጥ ተከትሎ በከተማዋ ቆሞ የነበረው እንቅስቃሴ በተወሰነ ደረጃ ወደነበረበት እየተመለሰ መሆኑን ሦስት የከተማዋ ነዋሪዎች ተናግረዋል።

የደብረ ብርሃን ከተማ እና አካባቢው ኮማድ ፖስትም ትናንት ባወጣው መግለጫ “የመንግሥት ተቋማት፣ ሱቆች፣ ባንኮች፣ ሆቴሎች እና ሌሎች አገልግሎት ሰጪ ተቋማት” ወደ መደበኛ እንቅስቃሴያቸው መመለሳቸውን አስታውቋል።   ዘገባው የቢቢሲ ነው፡፡

selegna

By selegna

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *