የሶማሊያ ፌደራል መንግሥት ኢትዮጵያ እና ራስ ገዟ ሶማሊላንድ ትናንት የደረሱት ስምምነት ሕጋዊ መሠረተ የሌለው እና ተፈጻሚ ሊሆን የማይችል ነው አለ።

የሶማሊያ መንግሥት የአገሪቱ ካቢኔ ካደረገው አስቸኳይ ስብሰባ በኋላ ባወጣው መግለጫ ኢትዮጵያ የሶማሊያ አካል ከሆነችው ሶማሊላንድ ጋር የደረሰችው ስምምነት ፈጽሞ ተቀባይነት የለውም ብሏል።

ኢትዮጵያ ከሶማሊያ ተገንጥላ ራስ ገዝ ከሆነችው ሶማሊላንድ ጋር የባሕር በር ማግኘት የሚያስችላትን የመግባቢያ ሠነድ ትናንት መፈራረሟ ይታወሳል።

ይህ ስምምንት ኢትዮጵያ በቀይ ባሕር ላይ ለወደብ እና ለጦር ሰፈር ልማት የሚውል 20 ኪሎ ሜትር የባሕር ጠረፍ እንድታገኝ የሚያስችላት ሲሆን በምላሹ ሶማሊላንድ ከኢትዮጵያ አየር መንገድ ድርሻ እንዲሁም እንደ አገር ከአዲስ አበባ እውቅና እንደምታገኝ ተዘግቧል።

ኢትዮጵያ እና ሶማሊላንድ ይህን የጋራ የመግባቢያ ሠነድ ታሪካዊ ሲሉ ቢገልጹትም በሶማሊያ በኩል ጠንካራ ትችት ተሰንዝሮበታል።

ኢትዮጵያ እና ሶማሊላንድ ይህን የመግባቢያ ሠነድ ትናንት በአዲስ አበባ መፈራረማቸውን ይፋ ካደረጉ በኋላ የሶማሊያ መንግሥት ካቢኔ ለአስቸኳይ ስብሰባ ተጠርቷል።

ከካቢኔው አስቸኳይ ስብሰባ በኋላ የሶማሊያ መንግሥት ባለ 9 አንቀጽ የውሳኔ ሃሳብ አስተላልፏል።

የሶማሊያ መንግሥት ሶማሊላንድ የፌደራል መንግሥቱ አንድ አካል መሆኗን አስረግጧል። ስምምነቱንም “በሶማሊያ ነጻነት፣ ሉዓላዊነት፣ የግዛት አንድነት እና የሶማሊያ ፌደራላዊ ሪፐብሊክ ላይ የተቃጣ ጥቃት ነው” ብሎታል።

የሶማሊያ መንግሥት ስምምነቱ ሕጋዊ መሠረተ የሌለው እና ተፈጻሚ ሊሆን አይችልም ያለ ሲሆን የኢትዮጵያ መንግሥት የአገሪቷን ሉዓላዊነት ሊጥስ በሚችል ተግባር ቢሳተፍ ሶማሊያ የትኛውንም አማራጭ ተጠቅማ እራሷን ትከላከላለች ብሏል።

“የሶማሊያ መንግሥት በሕዝቡ ድጋፍ እራሱን ሊከላከል፣ ሊጠብቅ እና የአገሪቱን ሉዓላዊነት፣ የግዛት እና የሕዝብ አንድነት ለመጠበቅ ዝግጁ ነው።”

ከዚህ በተጨማሪም የሶማሊያ መንግሥት የተባበሩት መንግሥታት የጸጥታው ምክር ቤት፣ የአፍሪካ ኅብረት፣ የእስላማዊ ትብብር ድርጅት፣ የአረብ ሊግ፣ የምስራቅ አፍሪካ በየነ መንግሥታት (ኢጋድ) እና ሌሎች ቀጠናዊ እና ዓለም አቀፋ ድርጅቶች ከሶማሊያ ጎን እንዲቆሙ እና ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ሕጎች ተገድባ እንድትቆይ ጫና እንዲያሳድሩ ጥሪ አቅርቧል።

የሶማሊያ መንግሥት የተመድ የጸጥታው ምክር ቤት እና የአፍሪካ ኅብረት በጉዳዩ ላይ በአስቸኳይ ስብሰባ እንዲያደርጉም አሳስቧል።

በመጨረሻም የሶማሊያ መንግሥት የስምምነቱ መፈረምን ተከትሎ በኢትዮጵያ የነበሩትን አምባሳደሩን መጥራቱን አስታውቋል።

“አዲስ ነገር ቢመስልም፤ ሳይጠበቅ የተፈጠረ ነገር አይደለም”

በተያያዘ ዜና የሶማሊያ ፕሬዝዳንት ሐሰን ሼይክ ሞሐሙድ ኢትዮጵያ እና ራስ ገዟ ሶማሊላንድ ትናንት የደረሱት ስምምነት “ሳይጠበቅ የተፈጠረ ነገር አይደለም” የሚል አስተያየት ሰጥተዋል።

“ትናንት ታኅሣሥ 22 በአዲስ አበባ የሆነው፤ አዲስ ነገር ቢመስልም፤ ሳይጠበቅ የተፈጠረ ነገር አይደለም” ብለዋል።

ፕሬዝዳንቱ ዛሬ ለአስቸኳይ ስብሰባ ለተቀመጠው የአገሪቱ ካቢኔ ባደረጉት ንግግር ስምምነቱ ዓለም አቀፍ ሕጎችን እና የተለመዱ አሰራሮችን ስለሚጻረር ተፈጻሚ ሊሆን ሊሆን አይችልም።

ፕሬዝዳንቱ ለሶማሊላንድ መንግሥት እና ሕዝብ ባስተላለፉት መልዕክት “ኢትዮጵያ እውቅና ልትሰጣችሁ አትችልም። ምንም እንኳ ልዩነቶች ቢኖሩንም የሶማሊ ሕዝብ በእናንተ ላይ የጠላትነት ስሜት የለውም” ብለዋል።

ፕሬዝዳንቱ ኢትዮጵያን በተመለከተ ሲናገሩ ደግሞ “ጎረቤታሞች ነን። እንደ የአየር ንብረት ለውጥ ያሉ ፈታኝ ሁኔታዎች ባሉበት ወቅት በሰላም ተቻችለን ለመኖር መጣር አለብን። እንደዚህ ያሉ አንገብጋቢ ጉዳዮችን በሰላማዊ እና በትብብር መንፈስ መቅረብ ይገባል እንጂ በአፍሪካ ቀንድ ውጥረትን ማባባስ ተገቢ አይደለም” ብለዋል።

“ሕዝቡ ይረጋጋ”

የሶማሊያ ጠቅላይ ሚንስትር ሐምዛ አብዲ ባሬ በበኩላቸው የሶማሊያ ሕዝብ እንዲረጋጋ ጥሪ አቅርበዋል።

ጠቅላይ ሚንስትሩ፤ “የሶማሊ ሕዝብ እንዲረጋጋ አሳስባለሁ፤ አንድ ላረጋግጥላችሁ የምፈልገው አገራችንን እንደምንከላከል ነው። የትኛውም መሬታችን፣ የባሕር ወይም የአየር ክልላችን አይጣስም። በየትኛውም ሕጋዊ አማራጭ እንከላከላለን” ብለዋል።

ጠቅላይ ሚንስትር ሐምዛ ጨምረውም “በሰሜንም ይሁን በደቡብ ባለው ሕዝባችን ድጋፍ አገራችንን መከላከል እንደምንችል እርግጠኛ ነኝ” ብለዋል።      ዘገባው የቢቢሲ ነው፡፡

selegna

By selegna

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *