ኢትዮጵያ የባሕር በር ያስገኝላታል የተባለው ስምምነት የፈረመችው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ድርሻን ሰጥታ 20 ኪሎ ሜትር የሚሸፍን የባሕር ጠረፍ ለመቀበል ከስምምነት ደርሳ መሆኑ ተገለጸ።

ብሉምበርግ በዘገባው ኢትዮጵያ በቀይ ባሕር ላይ፣ የባሕር በር የሚያስገኝላትን የመግባቢያ ስምምነት ከራስ ገዟ ሶማሊላንድ ጋር የተፈራረመችው በመጠን ያልተገለጸውን የአየር መንገዱን ድርሻ ለመስጠት ተስማምታ ነው ብሏል።

ኢትዮጵያ ከሶማሊያ ተገንጥላ ራስ ገዝ ከሆነችው ሶማሊላንድ ጋር የባሕር በር ለማግኘት የሚያስችላትን የመግባቢያ ሰነድ ትናንት መፈራረሟ ይታወሳል።

የጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽሕፈት ቤት ስምምነቱን ተከትሎ ባወጣው መግለጫ፤ “የመግባቢያ ሰነዱ ኢትዮጵያ የባሕር በርን በአስተማማኝ ሁኔታ ለመጠቀም ያላትን ፍላጎት ዕውን ለማድረግ መንገዱን ይጠርጋል” ብሏል።

ትናንት በነበረው የመግባቢያ ሰነድ ፊርማ ላይም የጠቅላይ ሚንስትሩ ብሔራዊ ደኅንነት አማካሪ አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን ኢትዮጵያ ለምታገኘው የባሕር በር በምላሹ ለሶማሊላንድ ከቴሌ ወይም ከአየር መንገዱ ድርሻ ልታገኝ እንደምትችል ጠቁመዋል።

አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን በንግግራቸው፤ “. . . በቴሌኮምም ይሁን፤ በአየር መንገድ ጥቅም የሚያስገኙ መሠረተ ልማቶች ድርሻ ለመስጠት የሚያስችል ዕድል አለው [የመግባቢያ ስምምነቱ]” ሲሉ ሶማሊላንድ ከመግባቢያ ሰነዱ ልታገኝ የምትችለውን ጥቅም ጠቁመዋል።

የብሔራዊ ደኅንነት አማካሪው ራስ ገዟ ሶማሊላንድ ጥቅም ከሚያስገኝላት መሠረተ ልማት የምታገኘው ድርሻ ምን ያህል ይሆናል የሚለው እንዲሁም ኢትዮጵያ ለምን ያህል የሊዝ ወቅት ምን ያህል ትከፍላለች የሚለው በዝርዝር ውይይቶች ወደፊት ይወሰናል ብለዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ያለፈው ኅዳር 04/2016 ዓ.ም ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሰጡት ማብራሪያ የባሕር በርን በተመለከተ “ማንንም የመውረር ፍላጎት የለንም” ካሉ በኋላ “በቢዝነስ ሕግ ግን የማያወላዳ ምርጫ እንፈልጋለን” ማለታቸው ይታወሳል።

ጨምረውም የኢትዮጵያ የባሕር በር ፍላጎት “በንግግርና በቢዝነስ ካልተፈታ ምን እንደሚያጋጥም መገመት አይቻልም። ግን ኢትዮጵያ ወደ ኤርትራ፣ ወደ ጅቡቲ፣ ወደ ሶማሊያ፣ ወደ ኬንያ ወይም ወደ ሌላ ጎረቤቶቿ አንድ ጥይት የመተኮስ ፍላጎት የላትም። በሉአላዊነታቸው ላይም ጥያቄ የላትም” ማለታቸው አይዘነጋም።

አያይዘውም ኢትዮጵያ ፋላጎቷን ለማሳካት የኢትዮጵያ አየር መንገድን እና ሕዳሴ ግድብን ጨምሮ ሌሎች አማራጮችን በጋራ ለመጠቀም ዝግጁ መሆኗን አንስተዋል።

ሰጥቶ መቀበል

አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን የኢትዮጵያ መንግሥት ይህን የመግባቢያ ሰነድ ከሶማሊላንድ ጋር የተፈራረመው ሰጥቶ መቀበል በሚል መርህ መሆኑን ተናግረዋል።

አምባሳደሩ ኢትዮጵያ በምላሹ ጦር ሰፈር መገንባት እና ወደብ ማልማት የሚያሰችላትን የባሕር ጠረፍ እንደምታገኝ ተናግረዋል።

አምባሳደር ሬድዋን የመግባቢያ ሰነዱ በ50 ዓመት የሚታደስ የጦር ሠፈር ለመገንባት እና የባሕር ንግድ ለማከናወን ወደብ ማልማት የሚያስችል የባሕር ጠረፍ የሊዝ ስምምነት እንደያዘ ተናግረዋል።

ትናንት በተከናወነው ሥነ ሥርዓት ከጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አሕመድ ጋር የመግባቢያ ሰነዱን የፈረሙት የራስ ገዟ ሶማሊላንድ ፕሬዝዳንት ኢትዮጵያ ለጦር ሰፈር እና ለወደብ ግንባታ 20 ኪሎ ሜትር ስፋት ያለው የባሕር ጠረፋ ቦታን በሊዝ እንምትወስድ ተናግረዋል።

አምባሳደር ሬድዋን ኢትዮጵያ በቀጣይ ወደብ በማልማት ሁለቱን አካባቢዎች የሚያገናኝ የባቡር እና መንገድ ግንባታ እንደሚካሄድ ተናግረዋል።

“በቀጠናው [ባሉ አገራት] ሃብት ከበቂ በላይ ነው። የሁላችንም ሃብት ሲሰባሰብ ከራሳችን ተርፎ ለዓለም ገበያ ሊውል ይችላል። ይህን ለማድረግ በቀጠናው ላይ ያሉ አገራት በሙሉ መተባበር እና አንደኛው የሌላውን ማካካስ ይቻላል” ብለዋል።

ዕውቅና ለሶማሊላንድ

ኢትዮጵያ ጥቅም ከሚያስገኙ መሠረተ ልማቶቿ ለሶማሊላንድ ድርሻ ከመስጠት በተጨማሪ ለሶማሊላንድ የአገርነት ዕውቅና ለመስጠት መስማማቷ እንዲሁ ተመላክቷል።

ሶማሊላንድ እአአ 1991 ላይ ራሷን ከሶማሊያ በመገንጠል ነጻነቷን ብታውጅም ኢትዮጵያን ጨምሮ የትኛውም አገር እስካሁን ዕውቅና ሳይሰጣት ቆይቷል።

ይኹን እንጅ፣ የመግባቢያ ሰነዱ ይህን እንደሚቀይር የሶማሊላንድ ፕሬዝዳንት ሙሴ ቢሂ ትናንት በተካሄደው ሥነ ሥርዓት ላይ ተናግረዋል።

ፕሬዝዳንቱ ኢትዮጵያ “ለሪፐብሊክ ኦፍ ሶማሊላንድ በይፋ ዕውቅና በመስጠት የመጀመሪያዋ አፍሪካዊ አገር ትሆናለች” ብለዋል።

ሶማሊያ እንደ አንድ ግዛቷ ለምትመለከታት ሶማሊላንድ ዕውቅና መስጠት ሊያስቆጣት ይችላል።

ሶማሊላንድ እና ኢትዮጵያ የደረሱትን ስምምነት ተከትሎ የሶማሊያ መንግሥት ዛሬ አስቸኳይ ስብሰባ መቀመጡ ተገልጿል።

ኤርትራ ከሦስት አስርት ዓመታት ጦርነት በኋላ፣ ከኢትዮጵያ በመለየት ነጻ አገር መሆኗን ስታውጅ፣ ኢትዮጵያ ባሕር አልባ አገር ሆና ቆይታለች።

ኢትዮጵያን ከሚያዋስኑ ስድስት አገራት ከደቡብ ሱዳን ውጪ ሁሉም ጎረቤት አገራት ሶማሊያ፣ ኤርትራ፣ ሱዳን እና ኬንያ የባሕር በር ባለቤት ናቸው።

ኢትዮጵያ በየዓመቱ 1.6 ቢሊዮን ዶላር ለወደብ ኪራይ ወጪ በማድረግ ዋነኛ የወጪ ገቢ ምርቷን በጂቡቲ በኩል ስታደርግ ቆይታለች።  ዘገባው የቢቢሲ ነው፡፡

selegna

By selegna

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *