የሶማሊያ ካቢኔ ኢትዮጵያ እና ሶማሊላንድ የመግባቢያ ሰነድ መፈራረማቸውን ተከትሎ ባካሄደው አስቸኳይ ስብሰባ በኢትዮጵያ የሚገኙትን የአገሪቱን አምባሳደር ጠራ።

የሶማሊያ ካቢኔ ዛሬ ታኅሣሥ 23/2016 ዓ. ም. ረፋድ ላይ ያካሄደውን ስብሰባ የመሩት የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ሐምዛ አብዲ ናቸው።

የአገሪቱ ካቢኔ ከዚህ አስቸኳይ ስብሰባ በኋላ ባወጣው መግለጫ ኢትዮጵያ እና ሶማሊላንድ ያደረጉትን ስምምነት ውድቅ አድርጓል።

“በዓለም አቀፍ ሕጎች መሠረት ሶማሊላንድ የሶማሊያ ናት” ያለው የካቢኔው መግለጫ፣ ኢትዮጵያ ከራስ ገዟ ሶማሊላንድ ጋር ያደረገችረውን ስምምነት አውግዟል።

ሶማሊላንድን ጨምሮ የሶማሊያን መሬት “ማንም አንድ ስንዝር እንኳን መንካት አይችልም” ያለው ካቢኔው የሶማሊያን አየር፣ ባሕር እና መሬት “ለመከላከል ዝግጁ” መሆኑን በአጽንኦት አስታውቋል።

ይህም የአፍሪካ ቀንድ መረጋጋትን ይጎዳል ያለው የካቢኔው መግለጫ፣ ትናንት ማምሻውን የተደረገውን የሁለቱን መንግሥታት ስምምነት “ግልጽ የሆነ የሶማሊያ ሉዓላዊነት ላይ የተቃጣ ጥቃት” ሲል ጠርቶታል።

የሶማሊያ ካቢኔን አስቸኳይ ስብሰባ እንዲያካሂድ ብሎም አምባሳደሩ እንዲጠሩ ያደረገው ትናንት ሰኞ ማምሻውን ኢትዮጵያ እና ሶማሊላንድ በአዲስ አበባ ከተማ የተፈራረሙት ስምምነት ተከትሎ ነው።

የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ከስምምነቱ በኋላ ባወጣው መግለጫ፤ “የመግባቢያ ሰነዱ ኢትዮጵያ የባሕር በርን በአስተማማኝ ሁኔታ ለመጠቀም ያላትን ፍላጎት ዕውን ለማድረግ መንገዱን ይጠርጋል” ብሏል።

በስምምነቱ መሠረት ኢትዮጵያ የኢትዮጵያ አየር መንገድን ድርሻ ሰጥታ፣ 20 ኪሎ ሜትር የሚሸፍን የባሕር ጠረፍ ከሶማሊላንድ ትቀበላለች።

ከጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አሕመድ ጋር የመግባቢያ ሰነዱን የፈረሙት የራስ ገዟ ሶማሊላንድ ፕሬዝዳንት ኢትዮጵያ ለጦር ሰፈር እና ለወደብ ግንባታ 20 ኪሎ ሜትር ስፋት ያለው የባሕር ጠረፍ ቦታን በሊዝ እንምትወስድ ተናግረዋል።

የጠቅላይ ሚንስትሩ ብሔራዊ ደኅንነት አማካሪ አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን ሶማሊላንድ ጥቅም ከሚያስገኝላት መሠረተ ልማት የምታገኘው ድርሻ ምን ያህል ይሆናል የሚለው እንዲሁም ኢትዮጵያ ለምን ያህል የሊዝ ወቅት ምን ያህል ትከፍላለች የሚለው በዝርዝር ውይይቶች ወደፊት ይወሰናል ብለዋል።

አምባሳደር ሬድዋን ኢትዮጵያ በቀጣይ ወደብ በማልማት ሁለቱን አካባቢዎች የሚያገናኝ የባቡር እና መንገድ ግንባታ እንደሚካሄድ ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ ከመሠረተ ልማቷ ከምትሰጠው ድርሻ በተጨማሪ ለሶማሊላንድ የአገርነት ዕውቅና እንደምትሰጥ ተገልጿል።

ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ጋር ስምምነቱ ላይ ፊርማቸውን ያኖሩት የሶማሊላንድ ፕሬዝዳንት ሙሴ ቢሂ አብዲ፤ “ኢትዮጵያ ለሪፐብሊክ ኦፍ ሶማሊላንድ በይፋ ዕውቅና በመስጠት የመጀመሪያዋ አፍሪካዊት አገር ትሆናለች” ብለዋል።

ሶማሊላንድ እአአ 1991 ላይ ራሷን ከሶማሊያ በመገንጠል ነጻነቷን ብታውጅም ኢትዮጵያን ጨምሮ የትኛውም አገር እስካሁን ዕውቅና ሳይሰጣት ቆይቷል።

ስምምነቱ ከሶማሊያ ካቢኔ በተጨማሪ የቀድሞው የአገሪቱ ፕሬዝዳንት ሞሐመድ አብዱላሂ ሞሐመድ ፋርማጆንም አስቆጥቷል።

የቀድሞው ፕሬዝዳንት ዛሬ ረፋድ ላይ በኤክስ ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት ስምምነቱን “ለሶማሊያ እና ለመላው አፍሪካ አሳሳቢ ጉዳይ ነው” ሲሉ ገልጸውታል።

አክለውም “ሉዓላዊነትን ማክበርና የግዛት አንድነት ለቀጠናው መረጋጋትና የሁለትዮሽ ስምምነት ቁልፍ ነው” ብለዋል።

አያይዘውም “የሶማሊያ መንግሥት በተገቢው መንገድ ምላሽ ይሰጣል” ሲሉ በአጽንኦት አስፍረዋል። ዘገባው የቢቢሲ ነው፡፡

selegna

By selegna

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *