23 ዓመት ለኖረው ሲሳይ፣ የማንዴላ አገር ፍጹም ተለውጣለች። ከጭቆና ወጥታ ጨቋኝ ሆናለች። ጥቁር ተጸይፋለች።

“ድሮ ግን እንደዚህ አልነበሩም’’ ይላል፤ ደጋግሞ።

የያኔውን እንዲህ ይተርካል።

ያዝኑልን ነበር

“እንደመጣን ጎዳና ላይ በመነገድ ነው የጀመርነው። እናቶች ያዝኑልን ነበር። መልስ ትተውልን ሁሉ ይሄዳሉ። ጉርሻ (ቲፕ) ይሰጡናል። ከየት ነው የመጣችሁት? ይሉናል። ከኢትዮጵያ ስንላቸው ግራ ይገባቸዋል። ኢትዮጵያን አያውቁም።

“አንዳንዶቹ እንዲያውም ኢትዮጵያ እዚያው ደቡብ አፍሪካ ውስጥ የሆነ ቦታ ያለች ነበር የምትመስላቸው። ሩቅ እንደሆነች ስንነግራቸው ይደነቃሉ። እነሱ ራሱ በአፓርታይድ ጊዜ በገዛ አገራቸው ከቦታ ቦታ ለመንቀሳቀስ ፍቃድ ያስፈልጋቸው ስለነበር…።

“ፊደል የቆጠሩት ግን ስለኛ በደንብ ያውቃሉ። ማንዴላ በኢትዮጵያ ፓስፖርት እንደተሰጠው ሁሉ…። ‘እኛን ነጻ ማውጣት ነበረባችሁ’ ይሉናል። በቃ አክብረው ያዋሩናል። ጓደኛ ሊያደርጉን ይፈልጉ ነበር።

“አሁን ያ ሁሉ የለም። አሁን መጤ ፈጽሞ ጠልተዋል። የችግራቸው ምንጭ እኛ እንደሆንን ያስባሉ። በእርግጥ የዋህ ናቸው። የዋህነታቸውን ግን ፖለቲከኞች ተጠቀሙበት። ‘ሥራችሁን የቀሟችሁ እነርሱ ናቸው’ ይሏቸዋል። ያምናሉ። . . . የዋሆች ናቸው።”

የቀበቶ ዘመን-ደጉ ዘመን

ደቡብ አፍሪካ ሲነሳ ሐበሻና ቀበቶ አብረው ይነሳሉ? ለምንድነው?

“ድሮ ሐበሻ በደቡብ አፍሪካ ቀበቶ በመቸርቸር ነበር ሥራ የጀመረው። ከቀበቶ በፊት ጺም መላጫ ነበር የምንቸረችረው።

‘’አንድ ጺም መላጫ ባትሪ አድርገንበት ለሙከራ ከካርቶኑ አውጥተን እናስቀምጣለን። ‘ምንድን ነው ይሄ?’ ይሉናል። ሞክሩት እንላቸዋለን። ይሞክሩታል። ይደነቃሉ፤ ይገዙናል።

ያኔ እንደዛሬው ብዙ ሱቅ አልነበረም። አልፎ አልፎ የፓኪስታኖች ሱቅ ነው የነበረው። እኛ ከዚያ እናወጣና በየገጠሩ እየሄድን እንሸጣለን።

ቀበቶ የሚባለው ነገር ምን መሰለህ? ያው ይዞ ለመሮጥ ስለሚመች ይመስለኛል። ግን ቀበቶ ብቻ አይደለም እኮ። በቃ የመጣውን አዲስ እቃ ሁሉ ነው ይዘን ገበያ እንወጣ ነበር።

በዚያ ላይ ዋጋችን በጣም ርካሽ ነው። ሱቅ ከሚሸጥበት ሰማይና ምድር። እና ደግሞ ምን መሰለህ? እነሱ መግዛት ይወዳሉ። ለምሳሌ ዥንጥላ ቤት እያላቸው መንገድ ላይ አዲስ ዣንጥላ ሲያዩ ይገዛሉ። መልበስ መግዛት የሚወድ ሕዝብ ነው።”

ሰላማዊ ሌቦች

23 ዓመታትን በዚያ የኖረው ሲሳይ የሚወደውን ሰው ሲመርቅ ‘ጀማሪ ሌባ ላይ አይጣልህ’’ በማለት እንደሆነ ይናገራል። በዚያ አገር ያለውን የወንጀል መልክና ቅርጽ እንዲህ ይተርካል።

“በደቡብ አፍሪካ ወንጀል ብርቅ አይደለም። እየተዘረፍክ ነው የምትኖረው። ስትለምደው ትኖርበታለህ። እኔ ብዙ ወንጀል ዐይቻለሁ፣ ሰምቻለሁ። ሁለት ጊዜ ደግሞ ራሴ ገጥሞኛል። እኔ እንዲያውም ወንጀል ከመበርከቱ የተነሳ ‘እሱ እኮ ምንም አላጋጠመውም’ የምባል ሰው ነኝ።

ብዙውን ጊዜ በክላሽ ነው የምትዘረፈው። ዕድለኛ ከሆንክ ያለህን ቶሎ ሰጥተህ ሕይወትህን ታተርፋለህ።

አንዱን ገጠመኝ ብቻ ልንገርህ።

ደርባን አንድ አሮጌ መኪና ለመግዛት ከአንድ ሕንድ ጋ ተነጋግሬ ወደዚያው ሄድኩ። ከባንክ ገንዘብ አውጥቼ መኪና ውስጥ ቁጭ ብያለሁ። መኪና ማቆምያ ውስጥ ነኝ።

የሆነ ልጅ በውስጥ ስፖኪዮ ወደኔ ሲመጣ ይታየኛል። ስፖኪዮ ሊሰርቅ መስሎኝ ‘Go away!’ (‘’ዞር በል’’) ስለው ሽጉጥ ደገነብኝ። አራት ሆነው በሰደፍ- በምን-አሯሯጡኝ።

‘የታል ገንዘቡ? ፍጠን-ፍጠን’ ብለው አዋከቡኝ። ከፍቼ ሰጠኋቸው። በጠራራ ፀሐይ ዘርፈውኝ ሄዱ።

በቅርብ ርቀት ለነበረ ፖሊስ ነገርኩት። ‘’የቱ ጋ? መቼ? ወዴት? እንዴት?’’ እያለ ሊያዘናጋኝ ሞከረ።

ምን መሰለህ፣ ደቡብ አፍሪካ ስትኖር ትለምደዋለህ። ሱቅህ ከመጡ ቆመህ ንብረትህ ሲዘረፍ ታያለህ። ምንም ማድረግ አትችልም።

ጀማሪ ሌባ ካጋጠመህ ነው መጥፎ። ፈሪ ስለሆኑ ይተኩሱብሃል። በዚህ የተነሳ ብዙ ወንድምና እህቶችን አጥተናል። ከዚያ ውጭ ግን ሌቦቹ በአመዛኙ ሰላማዊ ናቸው። እስካልታገልካቸው ድረስ ዘርፈው ብቻ ይሄዳሉ።

በፖሊስ መዘረፍ

ለሁለት ዐሥርታት በደቡብ አፍሪካ የኖረው ሲሳይ ኢትዮጵያዊያን ላይ የሚደርሰው ዘረፋ በቀማኞች ብቻ የሚወሰን አይደለም ይላል።

“የምትዘረፈው በሌቦች ብቻ አይደለም። ፖሊስም ይዘርፍሃል። ሥራህ ቦታ ይመጣሉ፤ ያገኙትን ይወስዳሉ። እንዳለ እቃህን ጭነው ይወስዳሉ። የኔ ነው ካልክ ትታሰራለህ። ስለዚህ በቃ ቆመህ የገዛ ንብረትህ ይዘረፋል፤በፖሊስ።

አንዳንዴ ከጥላቻ ተነስተው ነው የሚዘርፉህ። ‘ለምን መጣሁ’ እስክትል ድረስ ያማርሩሃል። ለመናገር እንኳን ዕድል አይሰጡህም።

ባለቤቴን በቀደም ‘ለታ ‘’You don’t belong here’’ ብለው አንገላቷት። ሕጋዊ ሰነድ አላት። አሁን አሁን ሕጋዊ መሆንም አያድንህም።

አንተን በማንገላታት ገንዘብ መሥራት እንደሚችሉ ስለሚያውቁ ሕጋዊነትህ ብዙም ዋጋ የለውም።

አንተም በቃ ከምታሰር፣ ከምንገላታ ብለህ የጠየቁህን ትከፍላለህ።”

ከጎዳና ንግድ ተነስቶ የሕንጻ ባለቤት መሆን

ሲሳይ በዚህ ሁሉ ፈተና ውስጥ ደቡብ አፍሪካ የብዙ ኢትዮጵያውያንን ሕይወት እንደለወጠች አይክድም።

“በደቡብ አፍሪካ ሁሉም ታሪክ መጥፎ አይደለም። የብዙ ሐበሾች ሕይወት በበጎ ተለውጧል። ከጎዳና ንግድ ተነስተው ትልቅ ሃብት ያፈሩ በርካታ ናቸው።

ጂፒ ሰፈር ብቻ ከ10 ሕንጻ በላይ አለ፤ የሐበሾች ንብረት የሆነ። አነስተኛ ሞል ያላቸው ሐበሾች አሉ። አገር ቤት ገብተው ንብረት ያፈሩ ብዙ ናቸው።

አውሮፓና አሜሪካ ሄደው ነገር ግን ተምልሰው መጥተው ሠርተው የተለወጡ ብዙ ናቸው።

በዚያው ልክ ደግሞ ሕይወት አይሞላም።

በከፍተኛ ወንጀል ውስጥ የተሰማሩም አሉ። ቁጥራቸው ግን በጣም ትንሽ ነው።

የገዛ ወገኖቻቸውን አሳፍኖ ገንዘብ መጠየቅ ምናምን፣ እንደዚህ ነገር ውስጥ የገቡ ሰዎች አሉ። በዚህ የተነሳ ሕይወታቸው የጠፉ ወንድሞቻችን እህቶቻችን አሉ። ግን በጣም ጥቂት ናቸው።”

ሐበሻ ወደ ደቡብ አፍሪካ መሰደድ የጀመረው እንዴት ነው?

አቶ ዮርዳኖስ አልማዝ ሰይፉ በጉዳዩ ላይ ሁለት ግሩም መጻሕፍትን ጽፈዋል። ጥናት ላይ የተመሠረቱ የምርምር ሥራዎች ናቸው።

ሐበሾች ወደ ደቡብ አፍሪካ ስደት የጀመሩበት አጋጣሚ የተፈጠረው ‘በታሪካዊ ግጥምጥሞሽ’ ነው ይላሉ።

“በፈረንጆቹ 90ዎቹ መባቻ በኢትዮጵያም በደቡብ አፍሪካም የሥርዓት ለውጥ ነበር። እዚያ አፓርታይድ ሥርዓት ተንኮታኮተ። እዚህ የደርግ ሥርዓት ተገረሰሰ።

እዚያ ገዢው ፓርቲ ኤኤንሲ ‘ANC’ በሩን ለጥቁሮች ከፈተ። እዚህ ደግሞ በደርግ መውደቅ የስደት በር ተከፈተ።

በአፓርታይድ ሥርዓት ጊዜ፣ አይደለም ከሌላ አገር ጥቁር ሊገባ፣ የአገሬው ሰው ራሱ ከክፍለ አገር ወደ ከተማ ለመግባት የይለፍ ወረቀት ያስፈልገው ነበር።

ያኔ የትግሉ ዋና ዋና አቀጣጣዮች ትግሉን በውጭ አገራት ይመሩ ነበር። ከአፍሪካዊያን ጋር አጋር ነበሩ። ከኢትዮጵያ ጋርም እንዲሁ።

እነ ኦሊቨር ታምቦ፣ ዋልተር ሲሱሉ፣ ማንዴላ ሥልጣን ላይ ሲወጡ ለስደተኛ የሚመች ፖሊሲ ቀየሱ።

የይለፍ ወረቀትም ቆመ። ጥቁሮችና ክልሶችም እንደልብ መንቀሳቀስ ጀመሩ።

በተቀራራቢ ወቅት ኢትዮጵያ ውስጥ ደርግ ወድቆ ኢህአዴግ ሲመጣ መሸኛ ደብዳቤ ቀረ። ከአገር የመውጫ ቪዛ ቀረ። በደርግ ዘመን ከአገር መውጣት የአገር ክህደት ነበር። በኢህአዴግ ግን ከአገር መውጣት ቀላል ሆነ።

ይህ ግጥምጥሞሽ ስደትን አስጀመረ።

ከደርግ መውደቅ በኋላ ወታደሮች ወደ ሦስተኛ አገር ለመሰደድ ጎረቤት አገር መሄድ ጀምሩ።

ብሔራዊ ግዴታ ሸሽተው ኬንያና ሱዳን የነበሩ ኢትዮጵያዊያን ደግሞ ቀደም ብለው ነበሩ። ከነዚህ ጎረቤት አገራት ሆነው አሜሪካ፣ አውሮፓና አውስትራሊያ ጥገኝነት ያመለክቱ ነበር።

የደቡባ አፍሪካ መንግሥት ስደተኞችን የሚቀበል አዎንታዊ ሁኔታ በሚዘረጋበት ጊዜ ከኬንያ ወደ ደቡብ አፍሪካ ጉዞ ተጀመረ። ምናልባትም ወደ ደቡብ አፍሪካ የመጡት የመጀመርያዎቹ ሐበሾች ወደ ሦስተኛ አገር ለመሄድ ይጠባበቁ የነበሩ ናቸው።

ቀደምት ከሚባሉት ስደተኞች መጀመርያ የሰፈሩት ጆበርግ ከተማ ማዕከል ውስጥ ነበር። አሁን ያቺ ማዕከል ጂፒ ተብላ የኢትዮጵያውያን መንደር ሆናለች።

በአፓርታይድ ጊዜ ጥቁሮች እንቅስቃሴ ለማድረግ ይቸገሩ ነበር። ነጻ ሲወጡ፣ ከገጠር ወደ ከተማ እንደልብ መንቀሳቀስ ሲጀምሩ፣ ሐበሾች ደግሞ ተሰድደው ንግድ ሲጀምሩ ጊዜው ተገጣጠመ። ገበያው ደራ።

በከተማ እምብርት ሃብት ንብረት የነበራቸው ነጭ ነጋዴዎች በነጻነት ማግስት ስጋት ገብቷቸው ነበር። የለውጡን ጦስ በመፍራት ሥራዎቻቸውን እየተዉ፣ ሕንጻዎቻቸን ጥለው ወደ ሌሎች ቦታዎች መስፈር ጀመሩ።

እነሱ በለቀቁት ቦታ ስደተኛው ገባበት። ሱቅ ከፈተበት። ነግዶ ማትረፍ ተቻለ። ንግዱ የደራውም ከዚያ በኋላ ነው።

ወደ ደቡብ አፍሪካ የሚሰደዱት ለምን በብዛት ‘ከደቡብ’ ሆኑ?

አቶ ዮርዳኖስ ጥናት ላይ በተመሠረተው መጽሐፋቸው ዳጎስ ያለ ቦታ ሰጥተው ይህን ጉዳይ መርምረዋል። የጥናታቸውን ጨመቅ በአጭሩ እንዲህ ያብራራሉ።

“ወደ ደቡብ አፍሪካ ስደት ሲጀመር በብዛት ከአዲስ አበባና መሰል ከተሞች ነበር። በሂደት ግን ስብጥሩ እየተቀየረ መጣ። በተለይም ከደቡብ ኢትዮጵያ ወደ ደቡብ አፍሪካ የሚሰደዱ እየበዙ መጡ። ለዚህ የተለያዩ ምክንያቶች አሉ።

አንዱ በ1992 ዓ/ም የተደረገው የኢትዮጵያ ምርጫ ነው።

ደቡብ ክልል ሆሳእናና ዱራሜ አካባቢ በፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ የሚመራ ፓርቲ ነበር።

ያ ፓርቲ ኢህአዴን እንዳሸነፈ ነበር የሚከራከረው። ኢህአዴግ ደግሞ አላሸነፋችሁም አለ። ነገሩ እየከረረ ሲመጣ የፓርቲው ደጋፊዎች አካባቢውን እየለቀቁ ሽሽት ጀመሩ፤ ወደ ደቡብ አፍሪካ።

የአጋጣሚ ጉዳይ ሆኖ በዚያው ሰሞን አንድ ከዚያ አካባቢ ተወላጅ የሆኑ ሰው አምባሳደር ሆነው ወደ ደቡብ አፍሪካ ሄዱ። አምባሳደሩ ለጥቂት ልጆች የሥራ ዕድል ፈጥረው ሊሆን ይችላል። ብዙ ወጣቶች ግን ለስደት ተበረታቱ፤ ችግር ቢደርስብን እንኳን ‘የኛ ሰው ነው- ይረዳናል’ በሚል ሊሆን ይችላል።

በዚያ በዚያ ከደቡብ ወደ ደቡብ የጀመረው ስደት እየተጠናከረ ሄዶ በደላሎች የሚዘወር ትልቅ ቢዝነስ ሆነ።

ከተሜ ቀመስ ስደተኛው ወደ ገጠር ቀመስ ስደተኛ ተቀየረ። ዱራሜና ሆሳእና ብዙ ልጆቻቸው ሄዱ። ቀድመው የተሰደዱ ወንዶች ሠርተው ብር ሲያገኙና ለትዳር ዝግጁ ሲሆኑ ደግሞ ሴቶችን ማምጣት ጀመሩ። ”

ሐበሾች በደቡብ አፍሪካ ሕጋዊ ናቸው?

በብዛት በኢ-መደበኛ መንገድ ወደ ደቡብ አፍሪካ የሚገቡት ኢትዮጵያውያን ድንበር ካለፉ በኋላ ወደ ስደተኛ ጣቢያ ሄዶ ማመልከት ይጠበቅባቸዋል።

ችግሩ አገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትር ለስደተኞች ‘ተቀብለናል-ወይም-ከልክለናል’ የሚል ምላሽ አይሰጡም። የጥገኝነት የመጠየቂያ ፈቃድ ወረቀት (Asylum seeker permit) ነው የሚያድሉት።

ይህ ወረቀት ቢበዛ ለ6 ወር ወይም ከዚያም ላነሰ ጊዜ የሚያገለግልና በየጊዜው መታደስ ያለበት ነው።

የአገር ውስጥ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ከፍተኛ ያልተጠናቀቀ የዶሴ ክምችት ስላለበት የስደተኛን ማመልከቻ ለመጨረስ የአቅምም የፍላጎት ውስንነት አለበት። ስለዚህ ስደተኛው ይህን ወረቀት በተደጋጋሚ እያደሰ ከመቆየት ውጭ አማራጭ አይኖረውም።

ከዓመታት በኋላ ይህ ወረቀት ወደ ስደተኛ መታወቂያ ወረቀት ይቀየራል። ይህ ማለት በዚያ አገር በስደተኝነት ተቀባይነት ማግኘት ማለት ነው።

የቋሚ ነዋሪነትን ማግኘት ግን ረዥም ዓመታትን የሚወስድ ሂደት ነው።

አቶ ዮርዳኖስ “እነዚህ ወረቀቶች የኢትዮጵያውያንን የሥራና ኑሮ ሁኔታ በመወሰን ረገድ ቁልፍ ሚና አላቸው” ይላሉ።

አንድ የጥገኝነት መጠየቂያ ወረቀት የያዘና አንድ ቋሚ የመኖርያ ፈቃድ ያለው እኩል ሠርቶ የመበልጸግ ዕድል የላቸውም።

መኖርያ ፈቃድ ያላቸው የባንክ ሒሳብ መክፈት፣ የሕንጻ ውል ኪራይ መፈራረም፣ ቻይናና ዱባይ ሄዶ እቃ የማምጣት፣ በሽርክና የመሥራት ዕድል ይኖራቸዋል። ወደ አገር ቤት ደርሶ የመምጣት ዕድልም አላቸው።

የስደተኛ መጠየቂያ ወረቀት ያላቸው ግን ይህን ማድረግ አይችሉም።

“ለዚህ ነው ወረቀቱ ኑሮና የንግድ ውጤታማነትህን ይወስናል የሚባለው።”

በእርግጥ የስደተኝነት መጠየቂያ ወረቀት ያላቸው ሁለት መብት ያገኛሉ፤ የመማርና የመሥራት።

ኢትዮጵያውያን ግን በብዛት ወደ ትምህርት አይሄዱም። ቀጥታ ወደ ንግድ ሥራ ነው የሚገቡት።

ሐበሾች በመደበኛ ኢኮኖሚ ተቀጥረው አይሠሩም።

ብዙ ኢትዮጵያዊያን አስፈላጊው ወረቀት ስለሌላቸው ብቻ ዕድገታቸው ተወስኖ የሚቀርበት አጋጣሚ ብዙ ነው። ከጥቃቅን ሥራ ወጥተው ወደ መደበኛ ኢኮኖሚ ለመግባት ይቸገራሉ።

ቀድመው ወደ ደቡብ አፍሪካ የገቡና አስፈላጊውን ሰነድ የያዙ ግን ሕይወታቸውን ለውጠዋል። ሱፐርማርኬት የከፈቱ፣ ሕንጻ የገነቡ አሉ።

“በተቃራኒው 20 ዓመት ኖረው አሁንም የስደተኝነት መጠየቂያ ወረቀት እያደሱ የሚኖሩ አሉ። አሜሪካና ካናዳ ወይም ሌላ የአውሮፓ አገር ቢሆኑ ኖሮ ሙሉ ዜግነት የሚያገኙበት ዕድሜ ነው ይሄ።”

አገሬው ሐበሾችን እንዴት ያያቸዋል? እነሱስ አገሬውን እንዴት ያዩታል?

አቶ ዮርዳኖስ በተለይ ሐበሾች ከደቡብ አፍሪካዊያን ጋር ያለመሰናሰል (Integration) የባሕልና የኑሮ ዘይቤ አለመጣጣምም የፈጠረው ነው ይላሉ።

በኢትዮጵያውያን በኩል በቅኝ ካለመገዛት ጋር ተያይዞ ሊሆን ይችላል ራስን ከፍ አድርጎ የማየት ሁኔታ አለ።

የሥነ ልቦና የበላይነትን ይበልጥ የሚፈጥርላቸው ደግሞ ሠርቶ መለወጣቸው ነው። ይህ በራሱ ችግር አይደለም። ችግር የሚሆነው ሌላውን ዝቅ አድርጎ ማየት ሲከተል ነው።

“በእርግጥ ሠርቶ መለወጥ ሲመጣ የተሻልክ እንደሆንክ ይሰማሃል። ከዚህ ጋ ተያይዞ የአገሬው ሰው ወደታች የማየት ነገር የለም አልልም።”

በተቃራኒው ደቡብ አፍሪካዊያን ሐበሾችን በተመሳሳይ ዝቅ አድርገው መመልከታቸው አልቀረም። መጤ ስደተኞች ናቸው በሚል ነው አመለካከቱ የሚመነጨው። ‘’ቆሬ ቆሬ’’ ይሏቸዋል። መጤዎች ማለት ነው።

ከዚህ ሌላ ንጸሕና አትጠብቁም፥ የተደባለቀ ነገር ትሸጣላችሁ፣ መኪና በሥርዓት አታቆሙም በሚል ቅሬታ ይቀርባል።

ከዚህ ውጭ ግን ሐበሾች ከሞላ ጎደል የሚታወቁት በታታሪ ሠራተኝነታቸው እንደሆነ አጥኚው አቶ ዮርዳኖስ ለቢቢሲ አስረድተዋል።

ሐበሾችና የቋንቋ ፈተና

በደቡብ አፍሪካ ከማኅበረሰቡ ጋር በቀላሉ ለመቀላቀል አንድ ጋሬጣ የሆነው ቋንቋ ነው። ሌሎች ከምዕራብ አፍሪካና ከደቡባዊ አፍሪካ የሚመጡ ስደተኞች በዚህ ረገድ ብልጫ ያገኛሉ።

ብዙ ኢትዮጵያውያን ግን ይቸገራሉ። ተበደልኩ ብሎ አቤት ለማለት ሰሚ የለም። ሰሚ ቢኖርም ቋንቋ የለም።

በእርግጥ ቋንቋ አንድ ጋሬጣ ሆኖ ይነሳል እንጂ ኢትዮጵያውያንም ከማኅበረሰቡ ጋር የመቀላቀል ጉጉት ብዙም የላቸውም።

ይህ የሆነው በሁለት ምክንያት ሊሆን ይችላል ይላሉ አቶ ዮርዳኖስ።

አንደኛው ሐበሾች ትኩረት የሚያደርጉት ሥራቸው ላይ ብቻ መሆኑ ነው። ‘ለአገሬው ባሕላዊና ማኅበራዊ ኩነቶች ትኩረታቸው እምብዛምም ነው።’

ሁለተኛው ጉዳይ በባሕል፣ በምግብ ምርጫ፣ በአኗኗር ዘይቤ፣ በሚዝናኑበት ቦታ አገሬውን አይመስሉም።

በዚህ ላይ ቋንቋ ሲጨመርበት የሁለት ዓለም ሰዎች ያደርጋቸዋል።

ከደቡብ አፍሪካውያን ጋ ተገናኝቶ ለማውራት፣ የባሕል ልውውጥ ለማድረግ አንድ እንቅፋት ቋንቋ ነው።

ለገበያ ያህል አይቸግራቸውም። ብዙዎቹ ዝቅ ያለ የትምህርት ደረጃ ቢኖራቸውም ለንግድ የሚሆኑ ቃላትን ያውቃሉ።

ባሕልና የአገሬውን ሥነ ልቦና ለመረዳት ግን ይፈተናሉ።

የመብት ጥሰት ሲደርስባቸው ከፍትህ አካላት ጋር መብትን ለማስከበር በቂ ቋንቋ ክህሎት የለም። ሌሎች ናይጄሪያን የመሰሉ ስደተኞች በዚህ ረገድ ችግር አይገጥማቸውም።

ብዙዎቹ አስፈላጊ ሰነድና ፍቃድ ኖሯቸው ሕጋዊ ሥራ እየሰሩ ቋንቋ ባለመቻላቸው እንግልት ይደርስባቸዋል።

ከአገሬው ጋ ብቻ አይደለም ፈተናው።

አሁን አሁን ትዳር መሥርተው፣ ልጅ አፍርተው ወደ ትምህርት ቤት የሚሰደዱ ሐበሾች ከገዛ ቤተሰብ ጋ ለመግባባትም የሚፈተኑበት አጋጣሚ አለ።

አንዳንዴ ልጅና ወላጅ መግባባት ይቸገራሉ። እንግሊዝኛ የቤተሰብ መዋቅርንም እየፈተነ ነው።

መጤ ጥላቻው ሐበሻ ላይ ይበረታል?

ለሲሳይ ደቡብ አፍሪካዊያን ፍጹም ተለውጣበታለች። እንደዚህ አልነበሩም እኮ ይላል ደጋግሞ።

ዜኖፎቢክ (መጤ ጠል) የሚለውን ጥቅል ስም አይወደውም።

‘አሁን ዜኖፎቢክ አይደለም ያለው። አፍሮፎቢክ ነው’’ ይላል።

ሲሳይ ይህን የሚለው ያለ ምክንያት አይደለም። ፓኪስታኖችን ጨምሮ በርካታ ጥቁር ያልሆኑ ‘መጤዎች’ በደቡብ አፍሪካ አሉ። ‘ማንም ውጡልን ብሏቸው ግን አያወቅም።’

እርሱ እንደታዘበው ጥላቸው ያነጣጠረው በጥቁር ላይ ብቻ ነው።

“ያሳዝናል-ከነጭ ጭቆና እንዲወጡ በረዷቸው ጥቁር ወንድሞቻቸው ነው የተነሱት።”

ነገሩ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ለምን አስፈሪ ሆነ? ለሚለው የቢቢሲ ጥያቄ ሲመልስ ‘ግለኝነትና ራስ ወዳድነት’ እየበዛ መምጣቱን አንዱ ምክንያት አድርጎ ያነሳል። ዋናው ጥላቻ አራጋቢዎች ግን ፖለቲከኞች ናቸው ይላል።

አሁን ለምን ይበልጥ አስፈሪ ሆነ?

በእርግጥ ደቡብ አፍሪካ ምርጫ ሲመጣ ይሄ ችግር የመከሰቱ ነገር አዲስ አይደለም። አሁን ግን ነገሩ ይበልጥ አስፈሪ ሆኗል።

‘ቢቢሲ አፍሪካ አይ’ የተሰኘው የምርመራ ዘገባ ከወራት በፊት ባሰራጨው አንድ ጥንቅር በደቡብ አፍሪካ ራሱን ዶዶላ ብሎ የሚጠራ ቡድን ‘’መጤዎችን ከነሕይወታቸው በእሳት ለማቀጣጠል በአደባባይ ሲቀሰቅስ የሚያሳይ ቪዲዮ አውጥቶ ነበር።

ከቅርብ ሳምንታት በፊት በማኅበራዊ ሚዲያ ይዘዋወር የነበረ አንድ ተንቀሳቃሽ ምሥል ሁለት ኢትዮጵያውያን በደቡብ አፍሪካ አንድ ገጠራማ አካባቢ በሚመስል ሥፍራ በከፍተኛ ሁኔታ ሲዋከቡ ያሳያል። ‘አገራችንን ለቃችሁ ውጡ ይሏቸዋል’ ደጋግመው።

ሁለቱ ኢትዮጵያውያን ነገሩ ወደ ደቦ ጥቃት እንዳይሸጋገር በመስጋት ይመስላል ሰዎቹን ለማረጋጋት የተቻላቸውን ሲያደርጉ ይታያል።

የደቡብ አፍሪካ ጥቁሮች የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት ጥያቄ እየበረታ መጥቷል። ብዙ ወጣቶች ከነጮች ነጻነት ቢያገኙም ከድህነት ግን ነጻ ሊሆኑ አልቻሉም።

ስለዚህ ፖለቲከኞችን ያስጨንቃሉ። ፖለቲከኞቹ ደግሞ ስደተኞች ላይ ጣታቸውን ይቀስራሉ።

‘ሥራችሁን የወሰዱባችሁ መጤዎች ናቸው’ ይሏቸዋል።

አንዳንድ የደቡብ አፍሪካ ከፍተኛ ባለሥልጣናት ሳይቀሩ በግልጽ መናገር ጀምረዋል ይላል ሲሳይ። ‘ስደተኛ ታክቶናል (We are sick and tired of foreigners) ይሉ ጀምረዋል።

ቁጣቸ ሲገነፍል የአገሬው ወጣቶች እጃቸውን የሚያነሱት በጥቁር ወንድሞቻቸው እንዳይሆን ፍርሃት አለ። በተለይ ኢትዮጵያውያን ለደቦ ጥቃት ተጋላጭ ናቸው።

ብዙዎች ከከተማ ወጣ ብለው በሚገኙ መንደሮች (ታውንሺፕ) ነው የሚነግዱት። በነዚህ ሰፈሮች የሚኖሩት ደግሞ ክልሶችና ጥቁሮች ናቸው። ኢትዮጵያዊያኑ በቀላሉ ይለያሉ። አይበለውና ይህ በየጓዳው የሚጎነጎነው የ’እናጠፋችኋለን’ ዛቻ አደባባይ ሲወጣ በቀላሉ ለደቦ ጥቃት ሊጋለጥ ይችላል።

ጥቃቱ አሁን አሁን በርትቶ ነው ያለው። አንዳንዶች መጪውን በመፍራት ቤተሰባቸውን በጊዜ ወደ ኢትዮጵያ እየላኩ እንደሆነ ሲሳይ ይናገራል። ንብረታቸው ተዘርፎ ባዶ እጃቸውን የቀሩ ደግሞ ተቀጥረው መሥራት ጀምረዋል።

‘እንዲያውም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ሐበሻ እየተመረጠ ይታሰራል’ ይላል ሲሳይ።

የኢትዮጵያውያን ስቃይ እንዴት ያብቃ? ምንስ ይደረግ?

አቶ ዮርዳኖስ መፍትሄው በስደተኛ ላይ ያለውን ተረክ ከሥር መሠረቱ መቀየር ነው ይላሉ። ምን ማለታቸው ነው?

በደቡብ አፍሪካ ስደተኞች የሚታዩበት መንገድ የተንሸዋረረ ሆኗል። ይህ የሆነው ደግሞ በብልሹ ፖለቲከኞች የተጣመመ ትርክት ነው።

ጎልቶ የሚሰማው ትርክት ስደተኞች ሥራችንን ቀሙን የሚል ነው። ይህ ግን ቅጥፈት እንደሆነ አቶ ዮርዳኖስ ያስረዳሉ።

በደቡብ አፍሪካ አሁን የሥራ አጥ ቁጥር እስከ 40% ደርሷል። የስደተኛው ቁጥር ተደምሮ ግን 4% ነው።

እንዴት 4% ስደተኛ የ40 % ሥራ አጥ ቦታን ሊወስድ ይችላል? ብለው ይጠይቃሉ።

መሬት ላይ ያለው እውነታ ሌላ ነው። ስደተኞች የራሳቸውን ሥራ ነው የሚጀምሩት። የሚነጥቁት ነገር የለም። አይደለም ከአገሬው ሥራ ሊነጥቁ፤ ለሌሎች ሥራ እየፈጠሩ ነው ያሉት ሲሉ ያስረዳሉ አቶ ዮርዳኖስ።

‘’ለምሳሌ ዚምባብዌ እንጀራ ጋጋሪዎች አሉ። ማላዊያን ለሐበሾች በሱቅ ረዳትነት ይሠራሉ። ብዙ የአገሬው ሰዎችም እንዲሁ።’’

ሁለተኛው የሚነሳው ወቀሳ ወንጀል ነው። ስደተኞች ወንጀል አስፋፉ ብለው ይከሳሉ። በአብዛኛው ወንጀሎች የሚፈጸሙት ግን በአገሬው እንደሆነ አቶ ዮርዳኖስ ያብራራሉ።

በእርግጥ ተረኩ ለፖለቲከኞች ጠቃሚ ነው። እንዲቀየር አይፈልጉም። ‘አፍሪካዊያን ስደተኞች አዎንታዊ ሚና እንዳላቸውን ሥራም እንደማይነጥቁ ማስረዳት ያሻል።

በኢትዮጵያን ላይ አገሬው የሚያነሳቸው ትንንሽ ቅሬታዎች እንዳሉም አልሸሸጉም፣ አቶ ዮርዳኖስ።

አንዱ ከቆሻሻ አወጋገድ ጋ የሚነሳ ወቀሳ ነው። ሌላው ሴቶችን እንዲጸንሱ አድርገው ይጠፋሉ የሚል ቅሬታ ይሰማል። የተሰረቀ ስልክና ላፕቶፕ ይሸጣሉ ተብለው ይታማሉ።

እነዚህ ትንንሽ ጉዳይ ይምሰሉ እንጂ ቢስተካከሉ አገሬው ሐበሾችን የሚመለከትበትን መንገድ በተወሰነ መንገድ ለመቀየር ያስችላሉ የሚል አስተያየት አላቸው።

ሲሳይ በበኩሉ ሚዲያዎች ችግር ሲፈጠር ብቻ ነው የሚዘግቡት፤ አደጋውን ቀድመው አይተው ሽፋን አይሰጡም ሲል ይወቅሳል።

ሐበሾች የሚታዩበት መንገድ በዘመን እየተለወጠ መምጣቱን ያወሳና ‘ራስ ወዳድነት’ አንዱ ምክንያት እንደሆነ ያብራራል።

“ድሮ እንደዚህ አልነበሩም ብታይ። አገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትር ተሰልፈን ሲያዩን – ‘ለምን ትሰለፋላችሁ -ኑ መታወቂያ ውሰዱ’ ይሉን ነበር።

ድሮ ጥቁር ወንድሞቻቸው ሃብት እንድንይዝ ይፈልጉ ነበር። ድሮ የነጭ ፍራቻና ጥላቻ ነበረባቸው፤ እኛን ያቀርቡ ነበር። አሁን ግን በፖለቲከኞች የሚነገራቸው ነገር ያስፈራል። ጠሉን። ስስት በዛ። የምዕራቡን የሕይወት ዘይቤ እየያዙ መጡ። መጪው ምርጫ ያስፈራናል…” ይላል ሲሳይ።

ቢቢሲ በደቡብ አፍሪካ ኤምባሲ በኩል ምን እየተሠራ ይሆን በሚል ሐሳብ ለማካተት ያደረገው ተደጋጋሚ ሙከራ አልሰመረም።   ዘገባው የቢቢሲ ነው፡፡

selegna

By selegna

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *