በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ የገበታ ለትውልድ ፕሮጀክት ከይዞታቸው የሚነሱ በደቡብ ወሎ ዞን ሎጎ ሐይቅ ዙሪያ የሚገኙ አርሶ አደሮች “የካሳ ክፍያ ሳይተላለፍልን እና ቅሬታችን ሳይሰማ ይዞታችን እየታረሰ ነው” ሲሉ ለቢቢሲ ተናገሩ።

የሐይቅ ከተማ አስተዳደር በበኩሉ ከአካባቢው ለሚነሱ 231 አርሶ አደሮች የተመደበው 235 ሚሊዮን ብር  እንደተላለፈለትና ገንዘቡን ለተነሺዎቹ ገቢ እንደሚያደርግ ገልጿል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ባለፉት ዓመታት “ገበታ ለሸገር”፣ “ገበታ ለሀገር” እና “ገበታ ለትውልድ” የተሰኙ የተለያዩ ፕሮጀክቶች ይፋ አድርገዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በተለያዩ ክልሎች እና በአዲስ አበባ የቱሪስት መዳረሻ ይሆናሉ የተባሉ አካባቢዎች ላይ የመዝናኛ ስፍራ ግንባታዎችን ሲያከናውኑ ቆይተዋል።

በአማራ ክልል ያሉ ሁለት ቦታዎችም በእነዚህ ፕሮጀክቶች ስር እንዲገነቡ ተመርጠዋል።

ቀዳሚው በገበታ ለሀገር ስር የተካተተው እና በጣና ሐይቅ ምዕራባዊ ዳርቻ ላይ የሚገነባው የጎርጎራ ፕሮጀክት ነው።

በማዕከላዊ ጎንደር ዞን በምዕራብ ደንቢያ ወረዳ የሚገነው ይህ ፕሮጀክት በመጠናቀቅ ላይ እንደሚገኝ መንግሥት ማስታወቁ ይታወሳል።

በአማራ ክልል የሚገኘው ሌላኛው ፕሮጀክት ደግሞ “ገበታ ለትውልድ” ስር የሚገኘው የሎጎ ሐይቅ ፕሮጀክት ነው።

በደቡብ ወሎ ዞን ተሁለደሬ ወረዳ ከሐይቅ ከተማ ሦስት ኪሎ ሜትር ገደማ ርቀት ላይ የሚገኘው ይህ ፕሮጀክት፤ በ13.6 ሄክታር መሬት ላይ የሚያርፍ እንደሆነ የሐይቅ ከተማ ከንቲባ አቶ ከድር መሀመድ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

አቶ ከድር እንደሚገልጹት በሎጎ ሐይቅ ዳርቻ ላይ የሚገነባው ይህ ፕሮጀክት ሊጀመር በዝግጅት ላይ ነው።

የሐይቅ ከተማ አስተዳደር ለዚህ ፕሮጀክት ግንባታ የሚውል “ነጻ መሬት”  እንዲያዘጋጅ ኃላፊነት እንደተሰጠው የሚናገሩት ከንቲባው፤ ፕሮጀክቱ እስካሁን ያልተጀመረው በፕሮጀክቱ ምክንያት ከይዞታቸው ለሚነሱ አርሶ አደሮች ካሳ ለመክፈል ጥናት እየተደረገ ስለነበር መሆኑን አስረድተዋል።

በፌደራል መንግሥት ለሚገነባው ይህ ፕሮጀክት ከይዞታቸው ለሚነሱ ግለሰቦች ካሳ የመክፈል ኃላፊነት በክልሉ መንግስት ላይ መውደቁንም አስረድተዋል።

አቶ ከድር፤ “[በዚህ ፕሮጀክት ምክንያት ለሚነሱ] ለአርሶ አደሮች ዘላቂ ካሳ መስጠት አስፈላጊ ስለሆነ መመሪያን መሰረት ባደረገ መንገድ ጥናቱ ተጠንቶ በጀቱ ጸድቋል” ሲሉ የካሳ በጀቱ መጽደቁን አስረድተዋል።

የአማራ ክልል መመስተዳደር ምክር ቤት ይህንን በጀት ያጸደቀው ቅዳሜ ታህሳስ 13፤ 2016 ዓ.ም ባደረገው ስብሰባ ላይ ነበር።

በዚህ ስብሰባ ላይ የጸደቀው የካሳ በጀት 235 ሚሊዮን ብር ገደማ እንደሆነ የአማራ ክልል መሬት ቢሮ ኃላፊ አቶ ሲሳይ ዳምጤ ለቢቢሲ ገልጸዋል።

ይህ በጀት የተያዘው በፕሮጀክቱ ምክንያት በአካባቢው ለሚነሱ 231 አርሶ አደሮች እና ሎጅ መሆኑን የሚያስረዱት አቶ ሲሳይ፤ ከበጀቱ ውስጥ 25 ሚሊዮን ብሩ ለሎጅ ክፍያ እንደሚውልም አብራርተዋል።

የቢሮ ኃላፊው፤ “[አርሶ አደሮቹ] በሚሰጣቸው ካሳ መልሰው እንዲቋቋሙ ነው የታሰበው። በወሰዱት ካሳ ከግብርና ውጪ ሊሳተፉ ይችላሉ። በኢንተርፕራይዝ ተደራጅተው ለመቋቋም በሚያደርጉት እንቅስቃሴ የእኛ ቢሮም የሚመለከታቸው ቢሮዎችም ድጋፍ ያደርጋሉ። እንጂ ምትክ መሬት [ለመስጠት አልተወሰነም]። ምትክ መሬት የሚሰጠው ካሳ ባይሰጣቸው ነበር” ሲሉ ከቦታው የሚነሱ አርሶ አደሮች የሚያገኙት የገንዘብ ክፍያ ብቻ መሆኑን ገልጸዋል።

የካሳ ክፍያው ሲሰላ ከአርሶ አደሮቹ የመሬት ይዞታ ስፋት ባሻገር በመሬቱ ላይ የሚገኘው ምርትም ከግምት ውስጥ እንደገባ አቶ ሲሳይ አክለዋል።

ከክልሉ መሬት ቢሮ ኃላፊ ጋር ተመሳሳይነት ያለው ሀሳብ የሚያንጸባርቁት የሐይቅ ከተማ ከንቲባ አቶ ከድር በበኩላቸው፤ ካሳው የተዘጋጀው የአርሶ አደሮቹን “ጥቅም በማይነካ” በኩል መሆኑን ተናግረዋል።

የክልሉ ባለስልጣናት ይህንን ቢሉም ቢቢሲ ያነጋገራቸው ሦስት ከመሬት ይዞታቸው የሚነሱ የአካባቢው አርሶ አደሮች እና ሁለት የሎጅ ባለቤቶች ለይዞታቸው በካሳ መልክ እንደሚከፈላቸው የተነገራቸው ገንዘብ “አነስተኛ” መሆኑን ገልጸዋል።

አርሶ አደሮቹ እንደሚያስረዱት በተለይም በይዞታቸው ላይ ለሚገኘው ምርት የተያዘው በጀት ከምርቱ ዋጋ ጋር የሚመጣጠን አይደለም።

በ550 ካሬ ሜትር ገደማ መሬት ላይ አቮካዶ ማልማታቸውን የሚናገሩት አንድ አርሶ አደር፤ ለይዞታው እና በመሬቱ ላይ ለሚገኘው ፍራፍሬ የተወሰነላቸው የካሳ ገንዘብ 926 ሺህ ብር መሆኑን ለቢቢሲ ገልጸዋል።

አርሶ አደሩ፤ “ይሄንን አቮካዶ ሳለማ ብዙ መስዋዕትነት ከፍያለሁ። አቮካዶውን ያለማሁበትን ጊዜ በሙሉ ሌላ ስራ ብሰራ [ኖሮ] 900 ሺህ ብር አይደለም ሌላ [የበለጠ] ገንዘብ አገኝ ነበር” ሲሉ በተወሰነላቸው የካሳ ግምት ደስተኛ አለመሆናቸውም ገልጸዋል።

አርሶ አደሩ ይህንን ገንዘብ ይዘው በቀጣይ ምን ማድረግ እንደሚችሉ እርግጠኛ አለመሆናቸውንም አክለዋል።

በሶስት ሺህ ካሬ ሜትር ገደማ ስፋት ባለው መሬት ላይ ጤፍ እና አትክልት የሚያመርቱ አንድ ሌላ አርሶ አደርም ተመሳሳይ ሀሳብ አንስተዋል።

በመሬቱ ላይ በዓመት ሶስት ጊዜ እንደሚያመርቱ ለቢቢሲ የተናገሩት እኚህ አርሶ አደር የተወሰነላቸው የ1.3 ሚሊዮን ብር ካሳ በመሬቱ ላይ ከሚገኘው ምርት አንጸር አነስተኛ መሆኑን ገልጸዋል።

ተነሺዎቹ ለይዞታቸውን የተወሰነውን የካሳ ግምት የሚገልጽ ደብዳቤ የተሰጣቸው ረቡዕ ታህሳስ 17፤ 2016 ዓ.ም ነው።

በዚህ ደብዳቤ ላይ “በልማት ምክንያት ከቦታችሁ የምትነሱ አርሶ አደሮች ደብዳቤው ከተጻፈበት ቀን ጀምሮ [መሬቱን] እንድታስረክቡ በጥብቅ እናሳስባለን” የሚል ትዕዛዝ መቀመጡን ሁለት ተነሺዎች ለቢቢሲ አረጋግጠዋል።

ነገር ግን እስካሁን ድረስ በደብዳቤው ላይ የተቀመጠው ገንዘብ እንዳልተሰጣቸው አራት ተነሺዎች ገልጸዋል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ አርሶ አደሮቹ በተወሰነላቸው የካሳ መጠን ላይ “ቅሬታ የማግኘት እድል ሳያገኙ” ትናንት አርብ መሬታቸው “በቡልዶዘር መታረስ” እንደጀመረ ለቢቢሲ ገልጸዋል።

በዚሁ ፕሮጀክት ምክንያት ተነሺ የሆኑ በአካባቢው የሚገኙ አንድ የሎጅ ባለቤትም ይህንኑ መመልከታቸውን ለቢቢሲ አረጋግጠዋል።

ስለ አርሶ አደሮቹ ቅሬታ ከቢቢሲ ጥያቄ የቀረበላቸው የሐይቅ ከተማ ከንቲባ አቶ ከድር ለካሳ ክፍያ የጸደቀው ገንዘብ እስካሁን ድረስ ለአርሶ አደሮቹ አለመተላለፉን አረጋግጠዋል።

ጉዳዩን በሚመለከት ቢቢሲ ጥያቄ ያቀረበለት የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት “የገበታ ፕሮጄክቶች የመሬት ጉዳይ የሚመለከታቸው ክልሎች ራሳቸው ናቸው” የሚል ምላሽ ሰጥቷል።

የሐይቅ ከተማ ከንቲባ በበኩላቸው የክልሉ መንግሥት የጸደቀውን ገንዘብ ወደ ከተማ አስተዳደሩ እንዳስተላለፈ አርሶ አደሮቹ በመረጡት ባንክ ገንዘቡ ገቢ እንደሚደረግላቸውም ገልጸዋል።

ለፕሮጀክቱ ግንባታ የሚሆኑ ማሽኖች ወደ አካባቢው እየገቡ መሆኑን ያረጋገጡት የሐይቅ ከተማ ከንቲባ አቶ ከድር፤ የአርሶ አደሮቹን “መሬታችን እየታረሰ ነው” የሚለውን ቅሬታ ግን  አጣጥለውታል።

“[ማሽኑ የገባው] ለመጋዘን እና ለጥበቃ የሚሆኑ ቦታዎችን ለመስራት ነው እንጂ መደበኛ በሆነ መንገድ ወደ ስራ አልገባንም። ዛሬ [አርብ] ማሽን የገባው ቅድመ ዝግጅት ስራዎችን ለመስራት የሚያስችል አንዳንድ ስራዎች ለመስራት ነው” ብለዋል።

አርሶ አደሮቹ የተወሰነላቸው የካሳ ገንዘብ ላይ ያላቸውን ቅሬታ ከትናንት አርብ ጀምሮ ማቅረብ እንደጀመሩ ከንቲባው አቶ ከድር ተናግረዋል።

የከተማ አስተዳደሩ ይህንን ቅሬታ ለመቀበል ያዘጋጀው ጽህፈት ቤት ጉዳዩን እንደሚመለከተውም ገልጸዋል።    ዘገባው የቢቢሲ ነው፡፡

selegna

By selegna

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *