በአማራ ክልል በፋኖ ታጣቂዎች እና በመከላከያ ሠራዊት መካከል የተቀሰቀሰውን ውጊያ ተከትሎ የኢንተርኔት (በይነ መረብ) አገልግሎት ከተቋረጠ ከአምስት ወራት በላይ ተቆጥረዋል።

ገዥ እና ሻጭን አቆራርጧል።

ተማሪና ተመራማሪን ከእውቀት ምንጭ አርቋል።

ሥራ ፈላጊዎችን ሥራ ከሚያነፍንፉባቸው ድረ ገጾች ጋር አለያይቷል። ዘመኑ በሚፈቅደው መሠረት ድረ ገጾችን በመጠቀም የሥራ ማመልከቻ ማስገባትም የማይታሰብ ሆኗል።

ነዋሪዎችን ከመረጃ አርቋል።ግጭቱን ተከትሎ በክልሉ የሚፈፀሙ የመብት ጥሰቶችንም እንዳዳፈነ ይነገራል።

በአገልግሎቱ ላይ ተመስርተው ሥራ የሚሰሩትንም ሥራ አልባ አድርጓል።

የጎንደር ከተማ ነዋሪው ዋለልኝ የአገልግሎቱ መቋረጥ “ሕይወቴን ወደ ኋላ መልሶታል።” ይላል።

ዋለልኝ ሕይወቱን ይመራ የነበረው የኢንተርኔት ካፌ ከፍቶ በሚያገኘው ገቢ ነበር።

በከተማዋ ከሐምሌ 26፣2015 ዓ.ም ጀምሮ ኢንተርኔት እንደተቋረጠ የሚናገረው ወጣቱ፣ ያለ ኢንተርኔት መስራት ስለማይችል ሥራውን ለማቆም ፣ ሠራተኞቹንም ለመበተን መገደዱን ይገልጻል።

ዋለልኝ እንደሚለው ለሁለት ዓመት ገደማ እርሱንና ቤተሰቦቹን ሲያስተዳድርበት በነበረው በዚህ ሥራው ከወጪ ቀሪ በወር ወደ 5 ሺህ ብር ገደማ ያገኝ ነበር።

በኢንፎርሜሽን ሲስተም በመጀመሪያ ዲግሪ ለተመረቀችና ሥራ አጥ ለነበረች ሌላ ወጣትም የሥራ ዕድል ፈጥሮ ነበር። አሁን ላይ እርሷንም ከሥራ አሰናብቶ፣ የተከራየውን ቤት ለቅቆ ወጥቷል።

ሆኖም አንድ ቀን ወደ ሥራዬ እመለሳለሁ የሚል ተስፋ አለው።

የባህር ዳር ከተማ ነዋሪ የሆነው ጌታቸውም ከዋለልኝ የተለየ እጣ አልገጠመውም። እርሱም ኢንተርኔትን መሠረት አድርጎ በሚሰራው ሥራ ነበር ቤተሰቡን የሚያስተዳድረው።

“ለአገሬ የውጭ ምንዛሬ አስገባ ነበር”

ጌታቸው እንደሚለው በዚህ ሥራው በወር ሦስት ሺህ ዶላር ገደማ ያገኝ ነበር።አሁን ላይ እጁ ከነጠፈ ወራት ተቆጥረዋል።

“በድረ ገጾች በምሰራው ሥራ ከእኔ አልፎ ለአገሪቷም የውጭ ምንዛሬ አስገኝ ነበር” የሚለው ጌታቸው፤ አሁን ላይ ለሠራተኞቹ ደመወዝ የሚከፍለው ይቅርና የራሱም ሕይወት እንደተናጋበት ይናገራል።

አገልግሎቱ ቶሎ ሊመለስ ይችላል በሚል ሲጠባበቅ ቢቆይም የተለወጠ ነገር ባለመኖሩ በሥሩ ቀጥሮ ሲያሰራቸው የነበሩ ሦስት ሠራተኞቹን ለማሰናበት ተገዷል።

“ሥራ ፈጥረን በመሥራታችን መንግሥት ሊደግፈን እና ሊያበረታታን ይገባ ነበር” የሚለው ጌታቸው፣ እሱን ጨምሮ ሌሎች በአገልግሎቱ ላይ ተመስርተው ኑሯቸውን የመሰረቱ የክልሉ ነዋሪዎች ለችግር መዳረጋቸውን ይናገራል።

ጌታቸው ኢንተርኔትን መሠረት አድርጎ ከሚሰራው ሥራ በሚያገኘው ገቢ ሕይወቱን ከመምራት ባለፈም፣ “ባለፉት ሁለት ሦስት ዓመታት ውስጥ ለአገሬ 100 ሺህ ዶላር የውጭ ምንዛሬ አስገኝቻለሁ” ይላል።

አሁን ላይ በርካታ ወጣቶች እየተሰማሩበት ያለው የዲጂታል ሚዲያ ዘርፍ እንደሆነ በማንሳትም፣ መንግሥት ያሉትን አማራጮች እየዘጋ በሄደ ቁጥር የሥራ አጦችን ቁጥር ከመጨመሩ ባሻገር ወንጀልን ሊያበረታታ ይችላል የሚል ስጋት እንዳለውም ገልጿል።

የኢንተርኔት ፍልሰት

በርካታ የቱሪስት መዳረሻዎች ያሉት ክልሉ፣ ከጸጥታ ችግሩ ባሻገር የኢንተርኔት አገልግሎት አለመኖሩ የጎብኝዎችን እግር አሳጥሮበታል።

በሆቴል እና ቱሪዝም ዘርፍ የተሰማሩት ከእንግዶቻቸው ጋር በቀላሉ መልዕክት የሚለዋወጡበት አማራጭ የለም። ምንም እንኳን የተወሰኑ ባለ ኮከብ ሆቴሎች የኢንተርኔት አገልግሎት የማግኘት እድል ቢሰጣቸውም፣ ብዙዎቹ ግን የላቸውም።

ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ በጎንደር የሚገኝ የአንድ ሆቴል ሥራ አስኪያጅ ለቢቢሲ ሲናገሩ፣ “ የኮቪድ ወረርሽኝ ከነበረበት ወቅት በባሰ ሁኔታ ጭር ብለናል” ብለዋል።

እርሳቸው እንደሚሉት ከውጭ ደንበኞቻቸው ጋር ኢሜይል ለመላላክ አማራጮች የሌሉ ሲሆን ሻይ ቡና እያሉ የሚያነቡ፣ ጥናትና ምርምራቸውን የሚሰሩ ሰዎችም ሆቴላቸውን ተመራጭ ማድረግ አቁመዋል።

በዚህ የተነሳ ከ100 በላይ ሰራተኞች ያሉትን ሆቴል ለመዝጋት ጫፍ መድረሳቸውን ገልጸው ነበር።

በሌላ በኩል አንዳንዶች ኢንተርኔት ፍለጋ ወደ መዲናዋ ጨምሮ ወደ ሌሎች አካባቢዎች እየፈለሱ ነው።

ጌታቸው ወደ አዲስ አበባ እና ሌሎች አካባቢዎች የተፈናቀሉ ጓደኞች አሉት።

ከእነዚህ ጓደኞቹ መካከል በሕጋዊ መንገድ በቤቲንግ ( ስፖርታዊ ውርርድ) ተሰማርተው ግብር እየከፈሉ ሲሰሩ የነበሩ እንደሚገኙበት ይናገራል።

የክልሉና የፌደራሉ መንግሥት ክልሉ ወደ ቀድሞው ሰላሙ እየተመለሰ እንደሆነ በተደጋጋሚ እየገለጹ ቢሆንም፣አሁንም በተለያዩ አካባቢዎች ውጊያዎች እንዳሉ የሚነገር ሲሆን የኢንተርኔት አገልግሎቱም እንደተቋረጠ ነው።

“ መንግሥት እንደሚለው ክልሉ ሰላም ከሆነ ለምን ኢንተርኔት አይለቀቅም?” ሲልም ጌታቸው ይጠይቃል።

‘የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን ማዳፈን’

ቢቢሲ ያነጋገርናቸው ነዋሪዎች በክልሉ ለወራት በዘለቀው ግጭት የተፈፀሙት የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ከተነገረው በላይ እንደሆነ ይናገራሉ።

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ጥቅምት 19/2016 ዓ.ም ባወጣው ዝርዝር መግለጫም መድፈርን፣ ከሕግ ውጭ የተፈፀሙ ግድያዎችንና የድሮን ጥቃቶችን ጨምሮ በክልሉ መጠነ ሰፊ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች መፈፀማቸውን መግለጹ ይታወሳል።

በኢንተርኔት መዘጋት ምክንያት መገናኛ ብዙኃንና የሰብዓዊ መብት ድርጅቶች ከክልሉ ወቅታዊ መረጃዎችን ለማግኘትም አዳጋች ሆኖባቸዋል።

የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች ኢንተርኔት መዝጋት እና የግንኙነት መስመሮችን ማቋረጥ መንግሥታት ጭቆና የሚያካሂዱበት መሳሪያ ነው ይላሉ።

አክሰስ ናው የተባለው የዲጂታል መብት ተሟጋች በሰራው ጥናት እንዳመለከተው መንግሥታት የኢንተርኔት አሊያም የቴሌ ኮሚዩኒኬሽን ባልቦላዎችን የሚያጠፉት ግጭቶች ሲኖሩ፣ በምርጫ ወቅት፣ በሕዝባዊ ተቃውሞዎች ወቅት እንዲሁም ፖለቲካዊ አለመረጋጋት ሲኖር ነው።

ተሟጋች ቡድኑ መስከረም ወር ላይ ባወጣው ሪፖርት ላይም በኢትዮጵያ ከአውሮፓውያኑ 2016 ጀምሮ በአገሪቷ በተከሰቱ ግጭቶች ፣ጥቃቶች እና ፖለቲካዊ አለመረጋጋቶች ወቅት ቢያንስ ለ26 ጊዜ ኢንተርኔት መቋረጡን ገልጿል።

በአማራ ክልል ኢንተርኔት ሲቋረጥም በአንድ ዓመት [በአውሮፓውያኑ 2023] ውስጥ ለሁለተኛ ጊዜ መሆኑን ድርጅቱ ገልጿል።

በመሆኑም መንግሥት በግጭት ወቅት የሰብዓዊ መብትን የሚጥሰውንና የመረጃ ፍሰትን የሚዘጋውን ኢንተርኔት ማቋረጥ እንዲያቆምና በክልሉ የኢንተርኔት አገልግሎትን እንዲመልስ ጠይቋል።

“በአስቸኳይ ጊዜ ወቅት ኢንተርኔት መዝጋት ሃሳብን በነጻነት የመግለጽና መረጃ የማግኘት መብትን በመገደብ በክልሉ የሚኖረውን ሕዝብ የከፋ አደጋ ላይ ጥሏል” ብሏል።

ከዚህም ባሻገር በሰሜኑ የእርስ በርስ ጦርነት ወቅት በትግራይ እንደታየው የኢንተርኔት መዘጋት የሰብዓዊ መብት ጥሰት የሚፈፅሙ ወንጀለኞችን ከተጠያቂነት እንዲሸሹ፣ ነዋሪዎችም ጠቃሚ የሕይወት አድን መረጃዎችን እንዳያገኙ ያደርጋቸዋል ሲልም አስጠንቅቋል።

በሰብዓዊ መብቶች ፣ዲሞክራሲ እና በፖለቲካ ነጻነቶች ዙሪያ ጥናቶችን የሚያካሂደው ፍሪደም ሃውስ የተሰኘው ድርጅት በተጠናቀቀው የአውሮፓውያኑ ዓመት ባወጣው ሪፖርት ላይ እንዳሰፈረው በአገሪቷ በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ቢያንስ ሦስት ጊዜ ኢንተርኔት ተቋርጧል።

ድርጅቱ በሪፖርቱ ከግንቦት 24፣ 2014 ዓ.ም. እስከ ግንቦት 23፣ 2015 ዓ.ም ባለው ጊዜ ውስጥ ኢንተርኔት የተቋረጠባቸውን ክስተቶችን ነቅሷል።

  • በፌደራል ኃይሎች እና መንግሥት ሸኔ ሲል በሽብርተኝት በፈረጀው የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት መካከል የተከሰተውን ግጭት ተከትሎ በምዕራብ ኦሮሚያ፣ ቄለም ወለጋ ሰኔ 2014 ዓ.ም የኢንተርኔት እና ስልክ አገልግሎት ተቋርጧል።
  • በፌደራል ኃይሎች እና በአማራ ክልል ኃይሎች መካከል የተከሰተውን ውጥረት ተከትሎ መጋቢት 2015 ዓ.ም በበርካታ የክልሉ አካባቢዎች የሞባይል ዳታ ተዘግቷል።
  • ጥር 2015 ዓ.ም. በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን አባቶች መካከል የተፈጠረውን ክፍፍል በማስመልከት የተጠራውን ፀረ መንግሥት ተቃውሞ ተከትሎ የማህበራዊ ድረ ገጾቹ ቲክቶክ፣ ቴሌግራም፣ ፌስቡክ ፣ ዩቲዩብ አገልግሎቶች ተገድበዋል።

በድርጅቱ የሪፖርት ጊዜ ባይሸፈንም በአማራ ክልል በፋኖ ታጣቂዎች እና በፌደራል መንግሥቱ መካከል የተከሰተውን ግጭት ተከትሎም ከሐምሌ 26/ 2015 ዓ.ም ጀምሮ ኢንተርኔት እንደተቋረጠ ነው።

‘ከዲጂታል ኢትዮጵያ 2025’ በተጻራሪ

የተባበሩት መንግሥታት ኢንተርኔትን የማግኘት መብት ሰብዓዊ መብት ነው ብሎ የደነገገው እንደ አውሮፓውያኑ በ2016 ነው። ነገር ግን ሁሉም የዓለማችን መሪዎች የዚህ ሃሳብ ደጋፊዎች ወይም አቀንቃኞች አይደሉም።

እንደ አውሮፓውያኑ በ2019 ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ኢንተርኔት “ውሃ ወይንም አየር አይደለም” በማለት የኢንተርኔት መቋረጥ የአገር መረጋጋትን ለማረጋጋጥ አስፈላጊ የሚሆንበት ጊዜ እንዳለ ተናግረው ነበር።

ይህ ንግግራቸው የተሰማውም መንግሥታቸው በአውሮፓውያኑ 2025 ለማሳካት ያቀደውንና ሰኔ፣ 2012 ዓ.ም. በሚኒስትሮች ምክር ቤት የጸደቀ ዲጂታል ስትራቴጂ ይፋ ካደረገ በኋላ ነበር።

ስትራቴጂው በዋናነት የዲጂታል መሠረተ ልማትን በመገንባትና በማስፋት የአገሪቷን ምጣኔ ሐብታዊ እድገት ማፋጠንን ዓላማ ያደረገ ነው።

በስትራቴጂ ከተቀመጡት ግቦች መካከል የቱሪዝም ኢንደስትሪውን ዲጂታላይዝ ማድረግ ፣በይነ መረብን ከመጠቀም እና ዲጂታል ክፍያን ከመቀበል አንስቶ ሌሎች የዲጂታል ቴክኖሎጂዎችን አጠቃቀምን ማጎልበት፣ የሥራ ዕድል መፍጠር እና የውጭ ምንዛሬ ግኝትን ማሳደግ የሚሉት ይገኙበታል።

የጠቅላይ ሚኒስትሩ ንግግር ከዚህ ጋር በተጻራሪ የቆመ ሲሆን፣በሰብዓዊ መብት እና በዲጂታል መብት ተሟጋቾችም ጠንካራ ትችትን አስተናግዷል።

እንደ ኢትዮ ቴሌኮም የባለፈው ዓመት ሪፖርት ከሆነ በኢትዮጵያ 33.9 ሚሊዮን የኢንተርኔትና እና ዳታ ተጠቃሚዎች አሉ።

አገሪቷ ካላት የሕዝብ ብዛት አንጻር የኢንተርኔት ተደራሽነት ላይ ብዙ የሚቀራት ቢሆንም፣ያላትን በመዝጋት ከአፍሪካ አገራት ቁንጮዋ እንደሆነች ተሟጋች ቡድኖች ይገልጻሉ።

ፍሪደም ሃውስ የተሰኘው ድርጅት በተጠናቀቀው የአውሮፓውያኑ ዓመት ባወጣው ሪፖርት፣ ኢትዮጵያን ጨምሮ በዓለም ላይ ካሉ 4.9 ቢሊዮን የኢንተርኔት አገልግሎት ማግኘት ከሚችሉ ሰዎች መካከል 46 በመቶ የሚሆኑት የሚኖሩት ባለሥልጣናት በፖለቲካዊ ምክንያቶች ኢንተርኔት በሚያጠፉባቸው አገራት መሆኑን ገልጿል።

ድርጅቱ ባለፉት 13 ተከታታይ ዓመታት የኢንተርኔት ነጻነት እየቀነሰ መሆኑንም በሪፖርቱ አመልክቷል።

* በዚህ ዘገባ ውስጥ ያነጋገርናቸው ግለሰቦች ለደኅንነታቸው ሲባል ስማቸው እንዲለወጥ ተደርጓል።    ዘገባው የቢቢሲ ነው፡፡

selegna

By selegna

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *