የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝደንት ጌታቸው ረዳ የፌዴራል መንግሥቱና ዓለም አቀፉ ማሕበረሰብ በክልሉ የተከሰተውን ድርቅ ለመግታት እጃቸውን እንዲዘረጉ ጠየቁ።

አቶ ጌታቸው በማሕበራዊ ሚድያ ገፃቸው ባሰራጩት መግለጫ በክልሉ ያለው ድርቅ እጅግ አሳሳቢ ደረጃ መድረሱን ጠቅሰዋል።

“በትግራይ ረሃብ እና ሞት እያንዣበበ ነው” ሲሉ የገለጡት ፕሬዝደንቱ ከ1977 በኋላ ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ እጅግ የከፋ ድርቅ መከሰቱን ተናግረዋል።

ፕሬዝደንቱ አክለው አሁን የተከሰተው ድርቅና በትግራይ የነበረው ደም አፋሳሽ ጦርነት ተደማምረው ከፍተኛ አደጋ ሊያደርሱ እንደሚችሉ ጠቁመዋል።

የትግራይ ኢኮኖሚ መቃወስ፤ የክልሉ መሠረት ልማቶች በተለይ የጤና ተቋማት መውደማቸው እና በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ከቤት ንብረታቸው መፈናቀላቸው የትግራይ ክልል ነዋሪዎችን ለከፍ ችግር ማጋለጡን አቶ ጌታቸውን በመግለጫቸው አውስተዋል።

“ስለዚህ ጊዜያዊ አስተዳደሩ የፌዴራል መንግሥትና ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ በትግራይ እያንዣበበ ያለውን ረሃብና ሞት ለመታደግ ሕጋዊ እና ሞራላዊ ግዴታቸውን ሊወጡ ይገባል” ብለዋል።

“ረሃብ ድምፅ አልባ ገዳይ መሣሪያ ነው” የሚሉት አቶ ጌታቸው የፌዴራል መንግሥቱና ዓለም አቀፉ ማሕበረሰብ “ይህን ገዳይ መሣሪያ ለማጥፋት” የበኩላቸውን አድርገዋል ሲሉ ያክላሉ።

“አሁን ደግሞ እያንዣበበ ያለውን ሰብዓዊ ቀውስ ለመግታት የበኩላቸውን ሊወጡ ይገባል” ሲሉ ጥሪያቸውን አቅርበዋል።

ፕሬዝደንቱ በመግለጫቸው ማዕከላዊው መንግሥቱም ሆነ ሌሎች አካላት አፋጣኝ ምላሽ መስጠት እንዳለባቸው አስምረዋል።

የተጠበቀ ዝናብ ሳይዘንብ መቅረቱ፣ የአንበጣ ወረርሽኝ፣ ሰብዓዊ እርዳታ ለተወሰነ ጊዜ ያክል ተቋርጦ መቆየቱ አሁን ለተከሰተው ሰብዓዊ ቀውስ ምክንያት መሆኑን የጠቀሱት አቶ ጌታቸው እርዳታው በተወሰነ መልኩ ቢመለስም በቂ አለመሆኑን ጠቅሰዋል።

የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ይህን ሰብዓዊ ቀውስ ለመቀልበስ የበኩሉን ድርሻ እየተወጣ መቆየቱን የገለጡት ፕሬዝደንቱ ነገር ግን ሁኔታው ከጊዜያዊ አስተዳደሩ አቅም ውጭ መሆኑን አሳውቀዋል።

ጊዜያዊ አስተዳደሩ ከወሰዳቸው እርምጃዎች መካከል ሰብዓዊ ቀውሱን ለመግታት 50 ሚሊዮን ብር መመደብ አንዱ መሆኑን በመግለጫቸው ያነሱት ፕሬዝደንቱ ይህ የገንዘብ መጠን ከችግሩ አኳያ አነስተኛ መሆኑን ገልጠዋል።

“ከ77ቱ የከፋ ነው”

የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር በድርቁ የተጎዱ ነዋሪዎችን ለመርዳት ግብረ ኃይል ማቋቋሙ ይታወሳል።

ቢቢሲ ከዚህ ቀደም ያናገራቸው የትግራይ ክልል የአደጋ መከላከያ እና ዝግጁነት ኮሚሽነር ገብረሕይወት ገ/እግዚአብሔር ድርቁ በአምስት የትግራይ ክልል ዞኖች መሰቱን ተናግረው ነበር።

ኮሚሽነሩ “በትግራይ የከፋው ድርቅ የተከሰተው በ1951 እና በ1977 ነበር። አሁን ያጋጠመን ከዚህም በላይ ነው። በኅዳር ወር ብቻ ከ400 በላይ ሰዎች በላይ በረሃብ ምክንያት ሕይወታቸው አልፏል” ሲሉ ተናግረው ነበር።

የክልሉ ባለሥልጣናት እንደሚሉት ከሆነ በአሁኑ ወቅት ከ2 ሚሊዮን የማያንሱ የክልሉ ነዋሪዎች ለረሃብ አደጋ ተጋልጠዋል።

ሕወሓትና የፌደራል መንግሥቱ ለሁለት ዓመታት ያደረጉትን ደም አፋሳሽ ጦርነት በሰላም ስምምነት ቢቋጩም ክልሉ በተፈጥሯዊ እና ሰው ሰራሽ ችግሮች ከገባበት ሰብዓዊ ቀውስ መውጣት አልቻለም።

በመላ አገሪቱ ለተረጂዎች የሚቀርብ የምግብ እርዳታ ላይ መጠነ ሰፊ ዝርፊያ ተፈጽሟል መባሉን ተከትሎ የዓለም ምግብ ፕሮግራም እና የአሜሪካ መንግሥት የልማት ተራድኦ ድርጅት (ዩኤስኤአይዲ) የእርዳታ ሥራቸውን ለወራት አቋርጠው መቆየታቸው ይታወሳል።

የተራድኦ ድርጅቶቹ የእርዳታ አቅርቦት ባቋረጡበት ወቅት የእርዳታ ምግብ የተከማቸባቸው መጋዝኖች በክልሉ ውስጥ እያሉ ነዋሪዎች ግን በረሃብ መሞታቸውን የትግራይ ክልል ባለሥልጣናት ይናገራሉ።   ዘገባው የቢቢሲ ነው፡፡

selegna

By selegna

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *