በሐዋሳ በሚገኘው የፓነሲያ ሆስፒታል ከአንዲት ሴት ከ2 ሺህ በላይ የሐሞት ከረጢት ጠጠሮች መውጣቱን በቀዶ ሕክምናው ላይ የተሳተፉት የሕክምና ባለሙያ ለቢቢሲ ገለፁ።

የ40 ዓመት ዕድሜ ካላት ከዚህች ግለሰብ 2ሺህ 94 የሐሞት ከረጢት ጠጠሮች በቀዶ ህክምና መውጣቱንም የፓነሲያ ሆስፒታል የቀዶ ህክምና ስፔሻሊስት የሆኑት ዶ/ር ፀጋዬ ቸቦ ለቢቢሲ ገልጸዋል።

ዶ/ር ፀጋዬ በኢትዮጵያ እንዲህ ከፍተኛ ቁጥር ያለው የሐሞት ጠጠሮች ከአንድ ሰው መውጣቱ እስካሁን ድረስ አለመመዝገቡን ጨምረው ተናግረዋል።

እንደ ዶ/ር ፀጋዬ ከሆነ ይህ “በአፍሪካ አህጉር ደረጃ በቁጥር ብዛት የመጀመሪያ ተብሎ ሊመዘገብ ይችላል።” ብለዋል

ከዚህ ቀደም በኢትዮጵያም 146 የሐሞት ጠጠሮች ከአንድ ሰው ላይ መወገዱ ሲመዘገብ፤ በግብጽ እና በደቡብ አፍሪካ ደግሞ አንድ ሺህ ያህል የሐሞት ጠጠሮች መውጣታቸው በሕክምና ሳይንስ ጆርናል ላይ ታትመው ማንበባቸውን ዶ/ር ፀጋዬ ከቢቢሲ ጋር በነበራቸው ቆይታ ወቅት አብራርተዋል።

እስከዛሬ ያልተመዘገበ ነው የተባለለት ከ2,094 በላይ ቁጥር ያለው የሀሞት ከረጢት ጠጠር (Symptomatic Multiple Cholelithiasis) ለ2 ሰዓታት ከ30 ደቂቃዎች በተደረገው ቀዶ ህክምና በተሳካ ሁኔታ ማስወገድ መቻሉንም አክለው ገልጸዋል።

እስካሁን የተለመደው ከአንድ ሰው የሐሞት ከረጢት ውስጥ እስከ መቶ ጠጠሮች መወገዳቸውን እንደሆነ የሕክምና ባለሙያው ጨምረው ገልጸዋል።

የሀሞት ከረጢት ጠጠሮች በቀዶ ህክምና ቡድን የተቆጠሩ ሲሆን ጠጠሮቹን ለመቁጠር ከ45 ደቂቃ በላይ መፍጀቱም በሀኪም የቴሌግራም ገፅ ላይ የሰፈረው መረጃ ያስረዳል።

ስማቸው ያልተገለጸው ታካሚዋ የሐሞት ጠጠሮቹ ከተወገደላቸው ከሁለት ቀናት በኋላ ወደ ቤታቸው መመለሳቸው ታውቋል።

ታካሚዋ የተደረገላቸው ሕክምና ውስብስብ የሚያደርጉ ተጓዳኝ ችግሮች የነበሩባቸው ነበሩ የሚሉት ዶ/ር ጸጋዬ ከሁለት ዓመት በፊት በይርጋለም ሆስፒታል የእንቅርት ካንሰር ታምመው ቀዶ ሕክምና ተደርጎላቸው የነበረ ሲሆን የዛሬ ሁለት ዓመት ድጋሚ ካንሰሩ በመታየቱ በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል የቀዶ ሕክምና ተደርጎላቸው ነበር ሲሉ አብራርተዋል።

የታካሚዋ ቀዶ ህክምና ከባድና ውስብስብ ያደረገው በተለያዩ ጊዜያት በተለያዩ ሆስፒታሎች ሶስት ጊዜ (3x) የእንቅርት ዕጢ/ካንሰር ቀዶ ህክምና የተደረገላቸው መሆኑ ብቻ አለመሆኑን ዶ/ር ፀጋዬ ይናገራሉ።

ከቀዶ ህክምናው በኋላ በታካሚዋ ላይ የነበረባቸው ተጓዳኝ የጉሮሮ ነርቭ ጉዳት፣ የድምፅ ለውጥ/የድምፅ ኃይል መቀነስ እና አልፎ አልፎ የነበረባቸው የአተነፋፈስ ችግሮች የድህረ- ቀዶ ህክምናው ፅኑ እንክብካቤ እና እርዳታ ውስብስብነትን ይጨምራሉ ይላሉ።

የሐሞት ጠጠር እንዴት ይከሰታል?

የሐሞት ከረጢት በቀኝ በኩል በላይኛው የሆዳችን ክፍል ከጉበት ስር ተለጥፋ የምትገኝ አነስተኛ ኮሮጆ መሰል አካል ነች።

አገልግሎቷም በጉበት ውስጥ የሚመረተውንና ለቅባታማ ምግቦች ሥርዓተ ልመት አስፈላጊ የሆነውን ሀሞት የተሰኘ ውህድ ማጠራቀም ብሎም በውስጡ ያለውን የውሃ መጠን በመቀነስ የጨዋማ ንጥረ ነገሮችን (Bile salts) ይዘት ከፍ ማድረግ ነው።

የሐሞት ከረጢት ጠጠር ከሚከሰትባቸው ምክንያቶች ዋነኛው በሰውነት ውስጥ በከፍተኛ ሁኔታ ተከማችቶ የሚቀመጥ ስብ ወይንም ውፍረት መሆኑን ባለሙያው ያብራራሉ።

ሌላው ደግሞ ሴቶች ከወንዶች በበለጠ ለሐሞት ከረጢት ጠጠር የበለጠ ተጋላጭ መሆናቸውንም ይናገራሉ።

ከባለሙያዎች ውጪ የሚወሰዱ መድሃኒቶች ለረዥም ጊዜ የሚወሰዱ ከሆነ ይህም የሐሞት ከረጢት ጠጠር የመከሰት እድሉን ያሰፋዋል።

ሌላው በአጭር ጊዜ ከፍተኛ የሆነ ክብደት መቀነስ፣ በተለይም ደግሞ በበባለሙያ ያልተደገፈ ከሆነ የሐሞት ከረጢት ጠጠር ሊያስከትል ይችላል።

ከአመጋገብ ጋር በተገናኘም ቅባት የበዛባቸው ምግቦችን አዘውትሮ መመገብ፣ ሐሞት ከረጢት ጠጠር በሰውነት ውስጥ እንዲከሰት ሊያደርግ ይችላል።

የሐሞት ጠጠር ምልክቶች

በአብዛኛው ጊዜ ቅባታማ ምግቦችን ከተመገቡ በኋላ የሚከሰት ለረዥም ሰዓት የሚቆይ የሆድ ህመም ካለ የሐሞት ጠጠር ምልክቶች ሊሆኑ ይችላል ይላሉ ዶ/ር ፀጋዬ።

በሆድ የላይኛው ቀኝ ክፍል ድንገተኛ የመውጋትና የማቃጠል ህመም ፣ በቀኝ ትከሻ ላይና በትከሻ መሳቢያዎች መካከል የጀርባ ህመም፣ የሆድ መነፋት ስሜት እና ምግብ ያለመፈጨት ችግሮች ካለም ይህ የሀሞት ከረጢት ጠጠር ህመም ( Symptomatic Cholelithiasis) ምልክት ሊሆን ስለሚችል በአፋጣኝ ወደ ሕክምና ተቋም መሄድ እንደሚያስፈልግ የሕክምና ባለሙያው ይመክራሉ።   ዘገባው የቢቢሲ ነው፡፡

selegna

By selegna

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *