በሳምንታት ልዩነት ውስጥ ሁለት ሚኒስትር ዲኤታዎቹን በሹም ሽር እና በኩብለላ ላጣው የሰላም ሚኒስቴር ሁለት አዲስ አመራሮች ተሾሙለት።

በጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ሹመት ያገኙት አዲሶቹ ሚኒስትር ዲኤታዎች ዶ/ር ከይረዲን ተዘራ እና አቶ ቸሩጌታ ገነነ እንደሆኑ ቢቢሲ ከተሿሚዎቹ አረጋግጧል።

የጠቅላይ ሚኒስትር አብይ መንግስት ወደ ስልጣን መምጣት ተከትሎ የፌደራል መንግስት አዲስ አስፈጻሚ አካል ሆኖ የተቋቋመውን የሰላም ሚኒስቴር፤ በሚኒስትር ዲኤታነት ሲመሩ የነበሩት አቶ ታዬ ደንደአ ከኃላፊነት የተነሱት በተያዘው ወር መጀመሪያ ነበር።

ከመስከረም 2014 ዓ.ም. ጀምሮ በዚህ ኃላፊነት ላይ የነበሩት አቶ ታዬ፤ በጠቅላይ ሚኒስትሩ ከስልጣን በተነሱ በማግስቱ በቁጥጥር ስር መዋላቸው ይታወሳል።

የአቶ ታዬን እስር አስመልክቶ የፀጥታ እና ደኅንነት የጋራ ግብረ ኃይል ባወጣው መግለጫ የቀድሞው ሚኒስትር ዲኤታ፤ መንግሥት “ሸኔ” እያለ ከሚጠራው የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት አመራሮች ጋር ግንኙነት በመፍጠር መንግሥትን ለመጣል ሲያሴሩ ነበር ሲል ወንጅሏል።

አቶ ታዬ ከስልጣን በተነሱበት ሳምንት ለስብሰባ ወደ ምስራቅ አፍሪካ ያቀኑት ሌላኛው የሰላም ሚኒስቴር ሚኒስትር ዲኤታ ዶ/ር ስዩም መስፍን ደግሞ እስካሁን ወደ አገር አለመመለሳቸውን አንድ የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ምንጭ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ዶ/ር ስዩም፤ የመጨረሻ ስብሰባቸው በኬንያ እንደነበር የገለጹት እኚሁ ምንጭ፤ “ከኬንያ ወደ ኢትዮጵያ ይመለሳሉ ተብሎ ይጠበቅ ነበር” ሲሉ ሚኒስትር ዲኤታው ወደ ስራ ገበታቸው አለመመለሳቸውን አስረድተዋል።

ዶ/ር ስዩም በትላንትናው ዕለት በፌስቡክ ገጻቸው ላይ ባሰፈሩት ጽሁፍ ከኃላፊነት መልቀቃቸውን የሚያመለክት መልዕክት አጋርተዋል። በዚህ ጽሁፋቸው ብልጽግና ፓርቲ እና መንግስትን “ቁመናው የወረደ፣ የመንግስታዊ ባህሪ ያልተላበሰ፣ ከህዝብ የተነጠለና የተጠላ” ሲሉ ተችተዋል።

ዶ/ር ስዩም አክለውም፤ “እንደ አንድ የመንግስት አካል ሆኘ በቆየሁባቸው ጊዜያት በህዝብ ላይ ለደረሰው ጉዳትና በደል ይቅርታ እጠይቃለሁ” ሲሉ በአሁኑ ሰዓት በመንግሥት ኃላፊነት ላይ አለመሆናቸውን አመልክተዋል።

አቶ ብናልፍ አንዱአለም በሚኒስትርነት የሚመሩት ሰላም ሚኒስቴር፤ የተለያዩ ዘርፎችን የሚመሩ ሁለት ሚኒስትር ዲኤታዎች አሉት። ዶ/ር ስዩም በሚኒስትር ዲኤታነት ይመሩ የነበሩት የፌዴራሊዝምና ግጭት አስተዳደር ዘርፍን ነው።

አቶ ታዬ ደግሞ የሰላም ግንባታ እና ብሔራዊ መግባባት ዘርፍን ይመሩ የነበሩ ሲሆን አሁን በቦታቸው አቶ ቸሩጌታ ገነነ ሚኒስትር ዴኤታ ሆነው ተሾመዋል። አቶ ቸሩ፤ በጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ኃላፊነቱ ላይ የተሾሙት አቶ ታዬ ከስልጣን በተነሱበት ታህሳስ 1፤ 2016 ዓ.ም መሆኑን ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ከትላንት በስቲያ ሰኞ ታህሳስ 15 ደግሞ ዶ/ር ከይረዲን ተዘራ የሰላም ሚኒስቴር ሚኒስትር ዲኤታ ሆነው በጠቅላይ ሚኒስትሩ ተሾመዋል። ሁለተኛ ሚኒስትር ዲኤታ ሆነው ተሾሙት ዶ/ር ከይረዲን፤ ከትላንት በስቲያ የሹመት ደብዳቤ እንደደረሳቸው ለቢቢሲ ገልጸዋል።

እስካሁን ድረስ ወደ አዲሱ መስሪያ ቤታቸው አለመሄዳቸውን የተናገሩት ዶ/ር ከይረዲን፤ በዚህም ምክንያት የትኛውን የሰላም ሚኒስቴር ዘርፍ እንደሚመሩ አለማወቃቸውን አስረድተዋል። በሚኒስቴሩ ሁለት የሚኒስትር ዲኤታ ዘርፎች መኖራቸውን የሚያስታውሱት የመስሪያ ቤቱ የቢቢሲ ምንጭ፤ አዲስ ሚኒስትር ዲኤታ መሾሙ የዶ/ር ስዩምን ከኃላፊነት መነሳት እንደሚያመለክት ገልጸዋል።

አዲሶቹ ተሿሚዎች እነማን ናቸው?

የአንትሮፖሎጂ ምሁር የሆኑት አዲሱ ሚኒስትር ዲኤታ ዶ/ር ከይረዲን፤ በስድስተኛው ሀገራዊ ምርጫ ብልጽግና ፓርቲን ወክለው በአዲስ አበባ ከተማ የተመረጡ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል ናቸው።

ዶ/ር ከይረዲን፤ በምክር ቤቱ የጤና፣ ማህበራዊ ልማት፣ ባህል እና ስፖርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ምክትል ሰብሳቢ የነበሩ ሲሆን በዛሬው ዕለት ይህንን ኃላፊነታቸውን ማስረከባቸውን ለቢቢሲ ተናግረዋል። በተጨማሪም የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት የቦርድ አባል ናቸው።

አዲሱ ተሿሚ፤ በታሪክ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን ከዲላ ዩኒቨርስቲ ያገኙት በ1997 ዓ.ም. ነው። በ2004 ዓ.ም. ደግሞ በሶሻል አንትሮፖሎጂ ሁለተኛ ዲግሪያቸውን ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ አግኝተዋል።

ዶ/ር ከይረዲን፤ በሶሻል አንትሮፖሎጂ ሶስተኛ ዲግሪያቸውን ለመስራት ወደ ጀርመኑ ባይሮይት ዩኒቨርስቲ ያቀኑ ሲሆን በ2010 ዓ.ም ትምህርታቸውን አጠናቅቀዋል። ዶ/ር ከይረዲን የሶስተኛ ዲግሪ ጥናት በግጭት አፈታት ላይ ያተኮረ ነው።

የሌላኛው አዲስ የሰላም ሚኒስቴር ሚኒስትር ዲኤታ አቶ ቸሩጌታ ገነነ የትምህርት ዝግጅት በፖለቲካ ሳይንስ ላይ ያተኮረ ነው።

አዲሱ ሚኒስትር ዲኤታ በዚሁ የትምህርት ዘርፍ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን ያገኙት በ2007 ዓ.ም ነው። ከሶስት ዓመት በኋላ ደግሞ ከዚያው ዩኒቨርስቲ በየውጭ ግንኙነት እና ዲፕሎማሲ ትምህርት ሁለተኛ ዲግሪያቸውን ይዘዋል።

በኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር (ኢንሳ) እንዲሁም በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት በባለሙያነት አገልግለዋል።

አዲሱ ሚኒስትር ዲኤታ ለመጀመሪያ ጊዜ ከፍተኛ ስልጣን ያገኙት እስካሁን ድረስ ሲሰሩበት የነበረውን የትምህርት እና ስልጠና ባለስልጣን መስሪያ ቤትን ሲቀላቀሉ ነው።

አቶ ቸሩጌታ፤ በባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ውስጥ የኢንስፔክሽን እና የትምህርት ማረጋገጫ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ነበሩ። አቶ ቸሩጌታ፤ በአሁኑ ጊዜ በሰላም ሚኒስቴር ሚኒስትር ዲኤታ ስራ መጀመራቸውን ለቢቢሲ ገልጸዋል።  ዘገባው የቢቢሲ ነው፡፡

selegna

By selegna

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *