ኢትዮጵያ በዓለም ገበያ ለሸጠችው የአንድ ቢሊዮን ዶላር ቦንድ ወለድን በቀነ ገደቡ መክፈል ባለመቻሏ ዕዳቸውን መክፈል ካልቻሉ አገራት ተርታ ተመደበች።

ሮይተርስ የዜና ወኪል ኢትዮጵያ ትናንት ሰኞ ታኅሳስ 15/ 2016 ዓ.ም. መክፈል የነበረባትን የ33 ሚሊዮን ዶላር ባለመክፈሏ ዕዳዋን መክፈል ያልቻለች ሶስተኛዋ የአፍሪካ አገር መሆኗን አስነብቧል።

ከአስር ዓመት በፊት በታኅሣሥ 2007 ዓ.ም. የ1 ቢሊዮን ዶላር የቦንድ ሽያጭ አድርጋ ላገኘችው ብድር የወለድ መክፈያ ጊዜያው ከሁለት ሳምንት በፊት ታኅሣሥ 1/2016 ዓ.ም. ነበር። ከመክፈያ ጊዜው ቀነ ገደብ በኋላ የነበረው የ14 ቀናት የእፎይታ ጊዜም እንዲሁ ተጠናቀቐል። ሆኖም መንግስት ወለዱን እንደማይከፍል ማስታወቁ ይታወሳል።

በገንዘብ ሚኒስቴር የማሻሻያ ከፍተኛ አማካሪ የሆኑት ሂንዣት ሻሚል፤ ክፍያው አለመፈጸሙን እና የሚከፈል አለመሆኑንም ማረጋገጣቸውን ብሉምበርግ ዛሬ ማለዳ ዘግቧል።

ይህን ተከትሎ ኢትዮጵያ ዕዳቸውን መክፈል የማይችሉ (Sovereign default ውስጥ ከገቡት) ሁለት የአፍሪካ አገራት ጎራ እንደምትሰለፍ ሮይተርስ ዘግቧል። ዕዳቸውን መክፈል የማይችሉ የተባሉት ሁለት የአፍሪካ አገራት ጋና እና ዛምቢያ ናቸው።

የመንግስት ሹማምንት ኢትዮጵያ ዕዳዋን የማትከፍለው፤ ሁሉንም አበዳሪዎች “በእኩል ለማስተናገድ” በሚል መሆኑን በተደጋጋሚ ይናገራሉ።

የፕላን እና ልማት ሚኒስትሯ ዶ/ር ፍጹም አሰፋ ከሶስት ቀናት በፊት ለመንግስት ቅርበት ካለው ፋና ቴሌቭዢን ጋር በነበራቸው ቆይታ፤ “ኢትዮጵያ የዩሮ ቦንድ ወለድንያልከፈለችው የውጭ ምንዛሬ ዕጥረት ችግር ስላለባት አይደለም” ሰሉ ተደምጠዋል።

ሚኒስትሯ አክለውም “በዓመት በርካታ ቢሊዮን ዶላሮች ከውጭ ለምናስገባው ዕቃ የምንከፍል ሀገር ነን ስለዚህ 30 ሚሊዮን ዶላር [ገደማ] ገንዘብ ተቸግረን አይደለም ያልከፈልነው ኢትዮጵያ እንዲያውም ብድሯን በጣም በመክፈል የምትታወቅ አገር ናት በችግር ውስጥም ቢሆን” ሲሉ አብራርተዋል።

ኢትዮጵያ የ33 ሚሊዮን ዶላር ወለድ ያልከፈለችው “ሁሉም አበዳሪ እና ተበዳሪ ተመሳሳይ አይነት አያያዝ ነው ሊያዝ የሚገባው” በሚል ምክንያት መሆኑን ዶ/ር ፍጹም ጠቁመዋል።

ይህ የሚኒስትሯ ምላሽ ከአስር ቀናት በፊት በወጣው የገንዘብ ሚኒስቴር መግለጫም ተስተጋብቷል። ሚኒስቴሩ በመግለጫው ኢትዮጵያ ወለዱን ያልከፈለችው ሁሉንም አበዳሪዎች “በእኩል ለማስተናገድ” በሚል እንጂ የውጭ ምንዛሬ እጥረት ኖሮባት አለመሆኑን አስታውቆ ነበር።

ኢትዮጵያ የብድር እፎይታ ለማግኘት በቡድን 20 የጋራ ማዕቀፍ በኩል የዕዳ ሽግሽግ ለማድረግ ውይይት ማካሄድ ከጀመረች ሰነባብታለች። ባለፈው ኅዳር ወር ላይ በቻይና እና በፈረንሳይ በሚመራው የፓሪስ ክለብ አማካኝነት የዕዳ ሽግሽግ ስምምነት ላይ ደርሳለች።

ይህን ስምምነት ያስታወሰው የንዘብ ሚኒስቴር መግለጫ፤ “የቦንድ ገዢዎችን ጨምሮ ሌሎች አበዳሪዎችም ተመሳሳይ አይነት የብድር ክፍያ ማስተካከያ ውስጥ እንዲገቡ በማድረግ [ከሁሉም አበዳሪዎች ጋር በሚኖር ግንኙነት ላይ] ወጥነት እና እኩልነትን ለማረጋገጥ” እንደሚፈልግ አስታውቋል።

ከአስር ዓመት በፊት ከቦንድ ሽያጭ የተገኘው ብድር የ6.625 % ዓመታዊ ወለድ የሚከፈልበት ሲሆን፣ የወለድ መጠን ዓመታዊ ይሁን እንጂ የአከፋፈል ሂደቱ በዓመት ሁለት ጊዜ ወይም በየስድስት ወሩ የሚፈጸም ነው።

የኢትዮጵያ መንገስት ይህ የ6.625 % ወደ 5.5 % ዝቅ እንዲደረግለት ይሻል። ከዚህ በተጨማሪም የዋናውን የብድር መክፈያ ጊዜ ከመጪው 2017 ዓ.ም. በአራት ዓመት ከመንፈቅ እንዲገፋለትም ጠይቋል።

በዚህ መካከል የኢትዮጵያ ዕዳዋን መክፈል አለመቻል ከሌሎች አበዳሪዎቿ ጋር የሚኖራትን ግንኙነት እንደሚጎዳው ቢቢሲ ከዚህ በፊት ያነጋገራቸው ሁለት የምጣኔ ሃብት ባለሙያዎች ተናግረዋል።

ነገር ግን የኢትዮጵያ ብድር ለመክፈል አለመቻል ሌሎች ድርድሮችን በመጉዳት ብቻ አያበቃም።

የገንዘብ አስተዳደር ባለሙያው ዶ/ር አብዱልመናን መሐመድ ከሁለት ሳምንት በፊት ከቢቢሲ ጋር ባደረጉት ቆይታ ይከሰታል የሚሉትን ዳፋ እንዲህ ሲሉ ያብራሩታል፤ “ከአይኤምኤፍ እናገኛለን ብለን ተስፋ የምናደረግው ገንዘብ ካለ በጣም ሊንጓተት ይችላል። ኢንቨስትሮች ካሉበት አገራት ጋር ያለውን ግንኙነት በተወሰነ ሊያሻክርው ይችላል። የሚሰጡት እርዳታ ላይም ተጽእኖ ሊኖረው ይችላል።”

ዶ/ር አብዱልመናን አክለውም ከእርዳታ መጓተት ጋር በተያያዘ መንግሥት የሚኖርበትን የበጀት ጉድለት ለመሙላት ገንዘብ ወደማትም ሊገባ እንደሚቸል ግምታቸውን ያስቀምጣሉ። ይህ በበኩሉ በአገሪቱ ያለውን ከባድ “የዋጋ ግሽበት ሊያባብሰው ይችላል” ይላሉ።

ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁት ሌላ ባለሙያም እንዲሁ ከሁለት ሳምንት በፊት ከቢቢሲ ጋር በነበራቸው ቆይታ “የኢትዮጵያ ብድር ለመክፈል አለመቻል፤ የወጪ እና ገቢ ንግድ ላይ ብዙ ጫና ይኖረዋል” በማለት ውጤቱ መጠነ ሰፊ መሆኑን ያስቀምጣሉ።

የኢትዮጵያን ምጣኔ ኃብት በቅርብ የሚከታተሉት ባለሙያው አክለውም፤ “ብዙ የመተማመኛ ሰነዶች ተቀባይነት ያጣሉ። ወደፊት እንደዚህ እናደርጋለን፣ ክፍያ እንፈጽማለን፣ መተማመኛ እንሰጣለን፣ ወደፊት ለምከፍለው ክፍያ ዛሬ ላይ አገልግሎት እናግኝ ዛሬ ላይ ዕቃ ይላክ ተበሎ የሚደረጉ የክፍያ ሰነዶች በአጠቃላይ እምነት ያጣሉ። ስለዚህ እሱ ትልቅ ኪሳራ ነው፞።”

ይህ በበኩሉ የግል ኩባንያዎችን የንግድ ሥራቸውን በአግባቡ ማከናወን እንዳይችሉ ሊያደርጋቸው ከፍ ሲልም ሠራተኛ እንዲቀንሱ ሊያስገድዳቸው እንደሚችል ባለሙያው ጨመረው ጠቁመዋል።

“ዕቃዎችን በገበያ ውስጥ ማግኘት አለመቻል” እና “የዕቃዎች ዋጋ በጣም መናር” በተመሳሳይ ሊከሰት የሚችል ሌላኛው ጉዳይ መሆኑን ባለሙያው ገልጸዋል።

እንደ ምጣኔ ኃብት ባለሙያዎቹ ማብራሪያ የአገሪቱ ኢንቨስትመንትም በኢትዮጵያ መንግሥት ዕዳን አለመክፈል ምክንያት የሚጎዳው ሌላኛው ዘርፍ ነው።

የምጣኔ ኃብት ባለሙያው ይህን ሲያብራሩ፤ “ኢንቨስተሮች በኢኮኖሚው ላይ ማታመን ያጣሉ፤ ስለዚህ ወደፊት ኢንቨስት አድርጌ ገንዘቤን አገኛለሁ የሚል ኢንቨስተር ማግኘት ከባድ ሊሆን ይችላል። ያሉ ኢንቨስተሮች የመስፋፊያ ዕቅዳቸውን ሊሰርዙ ይችላሉ። ወደፊት ኢንቨስት እናደርጋለን ብለው ያሰቡ ሰዎችም ፕሮጀክቶቻቸውን የመሰረዝ እርምጃ ሊወስዱ ይችላሉ። ከዚያ በመለስም ኢትዮጵያ እንደ ኢኮኖሚ ተወዳዳሪ መሆን ያቅታታል” ይላሉ።   ዘገባው የቢቢሲ ነው፡፡

selegna

By selegna

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *