ጥቅምት 2016 ዓ.ም፤ የላስታዋ ላሊበላ ውጥረት ላይ ነበረች።

ወጣቶቿ “ፋኖን ትደግፋላችሁ” በሚል በገፍ ተይዘው በኮምቦልቻ እየታሰሩ ነው። የከተማውን ጥግ ጥግ የከበበ ታጣቂ ኃይል አለ። በሌላ ጎን ደግሞ ከባድ መሳሪያ ተክሎ ጆሮውን ከፍቶ መከላከያ ሰራዊት በተጠንቀቅ ይጠባበቃል።

ከቅዳሜ ጥቅምት 24 2016 ዓ.ም ጀምሮ በሰሜን ወሎዋ ላሊበላ ዙሪያ በፋኖ ታጣቂ ኃይሎች እና በመከላከያ ሰራዊት መካከል በከባድ መሳሪያ የታገዘ ውጊያ ተደርጓል።

በፋኖ ታጣቂዎችና በመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች መካከል ግጭቱ ባለፈው ዓመት ሐምሌ ወር ሲጀመር በትሩ ከበረታባችው አካባቢዎች ውስጥ ላሊበላ አንዷ ናት። ከተማዋ በሐምሌ ወር መጨረሻ ለቀናት በፋኖ ቁጥጥር ስርም ነበረች።

ነገር ግን ጥቅምት 28 እና 29 2016 ዓ.ም ለታሪካዊቷ ላሊበላ ጥቁር ቀናት ሆኑ። በሁለቱ ኃይሎች መካከል ውጊያው ለቀናት ዘልቆ ረቡዕ ጥቅምት 28 2016 ዓ.ም ፋኖ ከተማዋን ቢቆጣጠርም በማግስቱ ጥሎ ወጥቷል።

በሁለቱ ቀናት በከተማዋ የተፈጠረውን ሁነት የአይን እማኞች “በደል፣ ግፍ፣ እልቂት” ሲሉ ይገልጹታል።

ከተማዋን ጥቅምት 28 2016 ዓ.ም ከቀኑ ስምንት ሰዓት አካባቢ የተቆጣጠረው ፋኖ ‘በአሰሳ’ ያገኛቸውን 15 የሚሆኑ የፖሊስና ሚሊሻ አባላትን መግደሉን የአይን እማኞች ለቢቢሲ ተናግረዋል።

በውጊያው ከፊት ሆነው ተሰልፈው ነበር የተባሉት የፖሊስና ሚሊሻ አባላቱ ፋኖ ከተማዋን መቆጣጠሩን ተከትሎ ከላሊበላ 11 ውቅር አብያተ ክርስቲያናት አንዱ በሆነው ቤተ አባ ሊባኖስ እና በሰዎች ቤት ተጠልለው እንደነበር እማኞቹ ገልጸዋል።

“ተኩሱ ከተጀመረ በኋላ [የፋኖ ታጣቂዎች] ሰርገው ወደ መሀል ከተማ ስለገቡ፤ ጦርነቱም እየከፋ ሲመጣ በመጨረሻ ከከተማ ለመውጣት ሳይሆን ቤተ ክርስቲያኗን ለመጠጋት ወደ ቤተ ክርስትያን ገቡ። ሴቶቹ የአካባቢው ኅብረተሰብ የተለያየ ልብስ በመስጠት ከሞት ታደጋቸው። እነዛኞቹ ከነ ልብሳቸው [የደንብ ልብስ] ስለተገኙ ቢያንስ ስምንት ዘጠኝ ይሆኑ ነበር ይዘዋቸው [ፖሊስ ጣቢያ] ሄዱ። እዛው ፖሊስ ጣቢያ በታሰሩበት ነው [የገደሏቸው]” ሲሉ ለደህንነታቸው ሲሉ ስማቸው እንዳይገለጽ የጠየቁ የአይን እማኝ ተናግረዋል።

ሌላ ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁ የላሊበላ ነዋሪ ከቤተ ክርስትያን ከተወሰዱት 10 የአካባቢው የፖሊስና ሚሊሻ አባላት ውስጥ የላስታ ወረዳ ፖሊስ አዛዥን ጨምሮ ዘጠኙ ተገድለዋል ብለዋል።

አባላቱ ከቤተ ክርስትያን ከተጠለሉበት ተወስደው መገደላቸውን የኃይማኖት አባቶችና ማህበረሰቡ እንዳወገዙትም ተናግረዋል።

“መጥተው በመስቀል ምለው ከወሰዱ በኋላ በመረሸናቸው የአካባቢውን ሰው እጅግ አስቆጥቷል” ቢሉም ታጣቂው “ሽፍታ” በመሆኑና “ስልጠና ባለመውሰዱ የሚያስወቅሰው ነገር ያለ አይመስለኝም” ብለዋል።

የፋኖ ታጣቂዎች በአካባቢው ሲንቀሳቀሱ ለፖሊስና ሚሊሻዎች “እርስ በእርሳችን አንጠፋፋ” በሚል ማስጠንቀቂያ ማድረሳቸውን ነዋሪዎች ጠቅሰዋል።

ለጸጥታ አባላቱ ከፋኖ ተደጋጋሚ የማስጠንቀቂያ መልዕክት ይደርሳቸው ነበር የሚሉት ሌላ እማኝ፣ ጥቅምት 28 2016 ዓ.ም የተገደሉ የጸጥታ ኃይሎች ቁጥር 15 ሳይደርስ አይቀርም ብለዋል።

ከዚህ ቀደም ቢቢሲ ያናገራቸው የፋኖ አመራሮች የመንግሥት የስራ ኃላፊዎች ግድያን በተመለከተ የማስጠንቀቂያ መልዕክት እንደሚያደርሱ ገልጸው “በቀጥታ የጦርነቱ አካል እስከሆኑ ድረስ መሳሪያ ከያዘው ወታደር አንለያቸውም” ብለው ነበር።

የፖሊስ አባላቱ ቤት ለቤትና ከቤተ ክርስትያን “ተለቃቅመው” በከተማዋ አደባባይ አካባቢ በሚገኝ ፖሊስ ጣቢያ መገደላቸውን ተናግረዋል።

ሐሙስ ለጥቅምት 29 2016 ዓ.ም አጥቢያ፣ የፋኖ ታጣቂዎች ከተማዋን ለቅቀው መውጣታቸውን ተከትሎ ዳግም ላሊበላን የተቆጣጠረው መከላከያ ሰራዊትም “በበቀል ተነሳስቶ” ንጹሃን ላይ ግድያ ፈጽሟል በሚል በነዋሪዎች ይከሰሳል።

የሟች ቤተሰቦችና የአይን እማኞች ለቢቢሲ እንደተናገሩት መከላከያ ጥቅምት 29 2016 ዓ.ም ከተማዋን ዳግም ከያዘ በኋላ ከዝርፊያ ጀምሮ፤ በጦርነቱ ተሳትፎ በሌላቸው ንጹሃን ላይ እስር፣ ድብደባና ግድያ መፈጸሙን ተናግረዋል።

ባለቤታቸውና ልጃቸው በመከላከያ ሰራዊት “ተረሽነውብኛል” ያሉ እናት፣ ሌላ የቤተሰብ አባላቸው ላይ ተመሳሳይ እጣ እንዳይደርሳቸው በመስጋት ለመገናኛ ብዙኀን ከመናገር ተቆጥበዋል።

በእንባ ታጅበው “ምን ሊፈይድልኝ” ሲሉ አለመናገርን የመረጡት እናት፣ ለሚዲያ ተናገራችሁ ተብለው የተገደሉ ሁለት ሰዎችን በመጥቀስ በስጋት አለመናገርን መርጠዋል።

‘የአራት ዓመት ልጄ አባቷ መቼ እንደሚመጣ ትጠይቃለች’

በጉልበት ስራ ላይ ተሰማርተው የነበሩት አቶ አበበ [ስማቸው የተቀየረ] በመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች በላሊበላ ከተገደሉት መካከል ናቸው።

ለደህንነታቸው በመስጋት ማንነታቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁ የአቶ አበበ ባለቤት የሁለት ልጆች እናት ናቸው።

የአራት ዓመት ልጃቸውን ለማምጣት የወጡት ባለቤታቸው፣ በራቸው ላይ በመከላከያ በቁጥጥር ስር ከዋሉ በኋላ እንደተረሸኑ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ከጎረቤታቸው ጋር በመከላከያ ሰራዊት “ቁጥጥር ስር የዋሉት” ሟች፣ ሀሙስ ጥቅምት 29 2016 ዓ.ም በሰራዊቱ ከተወሰዱ በኋላ ቤተሰባቸው ያሉበትን ቦታ ለማወቅ ያደረገው ጥረት አለመሳካቱን ገልጸዋል።

“ከቤት ልጅቷ ወጥታበት ሊያመጣ ሲል ነው [የተያዘው]። ይዘውት ሲወጡ የአራት ዓመት ልጄ እያለቀሰች ነበር። ጎረቤታችንንም ይዘውት ሄዱ። ሁለቱም የቀን ሰራተኛ ናቸው። ሁለቱንም ይዘዋቸው ሄዱ። እኛ እየተከተልን እሪ [እያልን] ምን ፈልጋችሁ ነው ብንላቸው ሊሰሙን አልቻሉም። ተከትለናቸው ብንሄድም መፍትሄ አጣን። አርብ ምሳ ይዘን ያሉበትን አሳዩን ብለን ቻይና ካምፕ [የመከላከያ ሰራዊት ካምፕ] ብንሄድ ‘አናውቅም እንደዚህ አይነት ሰው፤ እስረኛም የለም’ አሉን” ይላሉ።

አቶ አበበና ጎረቤታቸው “ተረሽነው” ጥልቀት በሌለው መቃብር ካምፕ ውስጥ መቀበራቸውን በሰው እንደተረዱም ተናግረዋል። በቁጥጥር በዋሉበት ቀን እጃቸውን ወደ ኋላ ታስረው (የፍጥኝ) ተገድለዋል የተባሉት ሁለቱ ግለሰቦች “በውለታ” አስከሬናቸው ከተቀበሩበት ተቆፍሮ ቅዳሜ (ህዳር አንድ) ለቤተሰብ መሰጠቱ ታውቋል።

ቀብራቸውም በዚሁ ቀን በድጋሚ ተፈጽሟል።

“አገር የእነሱን ስራ ስለሚያውቅ ሁሉም ህዝብ ነው ያለቀሰው። ወይ የፋኖ ምንነት የላቸው፤ ወይ ምን አላሉ፤ በቃ ቀናቸው ነው ብለን ነው። እጃቸው ቢኖርበት [እንደሚገደሉ] እንጠረጥር ነበር። ጠይቀው ይመልሷቸዋል እንጂ እንደዚህ ያደርጓቸዋል ብለን አላሰብንም። ሙሉ ከተማው ነው ያለቀሰው። ምክንያቱም ‘ወይ ታጥቀው በሞቱ፤ ወይ ፋኖ ሆነው በሞቱ፤ ያለስራቸው’ እየተባለ ነበር” ብለዋል።

በባለቤታቸው ስራ እንደሚተዳደሩ የሚናገሩት የአቶ አበበ ባለቤት ቀጣይ የቤተሰባቸውን ህይወት ለፈጣሪ ከመስጠት ውጭ ሌላ መንገድ አይታያቸውም።

“እንደዚህ ያደረገን ፈጣሪ፤ እሱ ያውቅልናል” ይላሉ በቁጭት።

ከአባቷ እቅፍ የተነጠለችው የአራት ዓመት ልጃቸው የአባቷን የመመለሻ ቀን እየጠየቀች ነው።

“ከሁሉም በላይ የእሷ ነው የከበደኝ። በነጋ ቁጥር ትጠይቃለች። ‘ምናለ የወሰዱት ሰዎች ቢያመጡት’ ትላለች። ምንም አልመልስላትም፤ ስራ ሄዷል ስላት እንኳ አታምነኝም። ሁልጊዜ ትጠይቃለች፤ የልጅን ጥያቄ መመለስ ከባድ ነው” ይላሉ።

ሌላ የከተማዋ ነዋሪ ሁለት የቅርብ ዘመዶቻቸውን ጨምሮ እርሳቸው የሚያውቋቸው አራት ሰዎች በመከላከያ ሰራዊት እንደተገደሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

“ፋኖ ናችሁ፤ ፋኖን ትደግፋላችሁ በሚል ከቤታቸው እየተጎተቱ የተገደሉ፤ የተረሸኑ ንጹሃን አሉ። እኔ እንኳ በትክክል የማውቃቸው አራት ንጹሃን የሆኑ ልጆች ናቸው። አንደኛው ወንድሙ ፖሊስ የነበረ ‘የት ነው ያለኸው እያለ፤ ተረፍክ ወይ’ እያለ እየተደዋወለ [እያለ] ስልኩን ቀምተው ካምፓቸው እስከ ጓደኛው ወስደው ደብድበው ገደሏቸው። ሁለቱ ደግሞ የኔ ቅርብ ቤተሰብ ናቸው። ከቤታቸው ጎትተው [ወንድማማቾችን] ነው የረሸኗቸው” ብለዋል።

ሌሎች ሦስት የቤተሰባቸው አባላትም ተይዘው ሊገደሉ ሲሉ የሚያውቃቸው ሰው በመገኘቱ መትረፋቸውንም የአይን እማኙ ተናግረዋል።

በመከላከያ ሰራዊት ከ10 እስከ 15 የሚደርሱ ንጹሃን ሳይገደሉ አይቀርም የሚሉት ሌላው ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ የላሊበላ ነዋሪ፤ በጦርነቱ ተሳትፎ የሌላቸው ሰዎች “የእሳት እራት” መሆናቸውን አመልክተዋል።

“ስልክ የሚያወራ ከተገኘ መረጃ እየሰጠ ነው በሚል ይገደላል” ያሉት አንድ ነዋሪ ያረጋገጧቸው አራት ሰዎች መገደላቸውን ተናግረዋል።

ቢቢሲ ይህን ዘገባ ለማዘጋጀት በርካታ የአይን እማኞችና የተጎጂ ቤተሰቦችን ቢያናግርም “ስልካችን ይጠለፋል፣ መረጃ ሰጣችሁ ተብለን ችግር ይገጥመናል፣ ያሰጋናል” በሚል ፍራቻ በላሊበላ የተፈጸመውን በፈቃደኛነት ከመናገር ወደ ኋላ ብለዋል።

“ቂም በቀል ነበር”

የፋኖ ታጣቂዎች ከተማዋን ለቀው በወጡ በሰዓታት ውስጥ ከተማዋን የያዘው መከላከያ ሰራዊት ዝርፊያ፣ ድብደባና ግድያ በመፈጸም ነዋሪዎች ክስ አቅርበውበታል።

“ወንድ የተባለን ከቤት እያስወጡ፤ ሽማግሌ የለ፣ ወጣት፣ ከአስራ ምናምን በላይ እድሜ ያለውን አውጥተው ኮብል ስቶን ላይ አምበርክከው ገርፈው፤ እዛው እንዳትንቀሳቀሱ ብለዋቸው ጥለዋቸው ሄዱ። ጸሐይ ሲቆላቸው ውሎ ወደ ማታ አካባቢ ነው ወደ ቤታቸው ገባን ያሉትና፤ እዚህ ቅዱስ ቦታ ላይ እንደዚህ ከሆነ ሌላ ቦታ ላይ ምን አይነት ግፍ ይፈጸማል የሚለውን ለመገመት የሚያዳግት አይደለም” ብለዋል።

“. . . ያገኙትን [ፋኖን] ትደግፋላችሁ በሚል በቀል ነው። በድንገት ያገኟቸውን ነው ከቤት አውጥተው የገደሏቸው” በማለት የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት በቂም በቀል ተነሳስቶ ንጹሃንን ገድሏል ሲሉ አንድ ነዋሪ በወቅቱ የተፈጸመውን ገልጸዋል።

“ብስጭት ይታይባቸው ነበር” ያሉ ሌላ የአይን እማኝ፤ ይህን ብስጭታቸውንም ህዝቡ ላይ ይወጣሉ ሲሉ አሁንም እርምጃዎች መቀጠሉን ያስረዳሉ።

“ይሄ ቄስ ነው ትናንት ያስገደለን” በሚል ከቤተ ክርስትያን ተወስደው በፋኖ ለተገደሉ ፖሊሶች በቀል በአንድ የኃይማኖት አባትና ሁለት ጥበቃዎች ላይ ከባድ ድብደባ መፈጸሙን ደግሞ ሌላ እማኝ ገልጸዋል።

“ቄሰ ገበዙን አንገታቸው ላይ ቆመው ደብደቧቸው። ጥበቃዎቹ ቄሱን ሲደበድቡ እየተተኮሰባቸው አመለጡ። ቄሱ ጆሯቸውን ታመው እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ከጆሯቸው ደም ይፈሳል።”

በከተማዋ የተወሰኑ የንግድ ተቋማት መዘረፋቸውንም ነዋሪዎች ተናግረዋል።

“መኪና አስጠግተው ነው የተወሰኑ ሱቆችን የዘረፏቸው፤ ወርቅ ቤት፣ ሱፐር ማርኬት፣ ቡቲክ ጭነው ዘረፉባቸው። እርስ በእርሳቸው አንዴ ሚሊሻ ነው፤ አንዴ ፖሊስ ነው፤ አንዴ መከላከያ ነው ይባባላሉ፤ መልስ የሚሰጥ ጠፋ። ዞሮ ዞሮ የመንግሥት ኃይል ነው የዘረፈው” በማለትም አክለዋል።

ፍትህ? ተጠያቂነት?

“ያለምክንያትና ያለስራቸው” በመከላከያ ሰራዊት ተገድለዋል የተባሉት የእነ አቶ አበበ [ስማቸው የተቀየረ] ቤተሰቦች ስለ ድርጊቱ መንግሥት እንዲያውቅ እንፈልጋለን ይላሉ።

የላሊበላ ነዋሪዎችም በከተማዋ ስለተፈጸሙ ግፎች ፍትህና ተጠያቂነትን ይሻሉ።

“ተጠያቂነት ያስፈልጋል። አንድ መንግሥት ነን ከሚል አካል የማይጠበቅ [ነው]። ጥፋት ያጠፉ ሰዎች በገለልተኛ አካል ተጣርቶ የተበደሉት ፍትህ ቢያገኙ ደስ ይለኛል” ሲሉ አንድ ነዋሪ ተናግረዋል።

“መንግሥት እንዲህ ሽፍታ ሆኖ፤ ይህን ያህል መአት ሲያወርድብን ሌላ ሰብዓዊ መብት ተሟጋች የሚሏቸው ገብተው ተጣርቶ፤ በዚህ እጃቸው ያለበት፤ የተሳተፉ ኃይሎች ተጠያቂ እንዲሆኑልን እንፈልጋለን። ጊዜ ሊወስድ ይችላል፤ [ግን] ተጠያቂነት ወደ ፊት አይቀርም” ሲሉ አንድ ነዋሪ ፍትህ ማግኘት የጊዜ ጉዳይ ነው ይላሉ።

ቢቢሲ ላሊበላ ላይ ስለተፈጸሙ ግድያዎችና ጥሰቶች የጠየቀው የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ጉዳዩን “እየተከታተለና እየመረመረ” መሆኑን ተናግሯል።

“ኢሰመኮ ጉዳዩን በትኩረት እየተመለከተው ነው። ምርመራዎችን እያደረገና ከሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት ጋር አዳዲስ ሁነቶችን በቅርበት እየተከታተለ ነው” ሲል አስተያየት ሰጥቷል።

ቢቢሲ ላሊበላ ላይ ተፈጸሙ ስለተባሉ ግድያዎች ከመንግስት አስተያየት ለማግኘት ያደረገው ጥረት አልተሳካም።

‘ላሊበላ ማቅ እንደለበሰች ነው’

በየዓመቱ ታሕሳስ 29 የሚከበረው የገና በዓል በላሊበላ እጅጉን ይደምቃል።

ከተማዋ በዚህ ወቅት እንግዶቿን ለመቀበል ዝግጅቷን የምታገባድድበት ወቅት ነበር።

አሁን ግን ላሊበላ ጥቁር ልብሷን መግፈፍ እንዳልቻለች ነዋሪዎቿ ይናገራሉ።

ላሊበላ ተወልደው ያደጉ አንድ የሀይማኖት አባት በከተማዋ ጥቅምት 28 እና 29 2016 ዓ.ም የተፈጸመውን ድርጊት “ዘግናኝ ነው” ይሉታል።

“ሙሉ ሕዝቡ እኮ ጥቁር ነው የለበሰው። ያሳደጉን፣ አብረውን የነበሩ ሰዎች፣ አብረውን ያደጉ ወንድሞቻችን፣ ጓደኞቻችን፣ በእድሜ የሚበልጡን፣ የምንበልጣቸው ሲለዩን ለመኖር ተስፋ አለመኖሩን ነው ያየነው። ሰው በልቶ ጠጥቶ ከቤተሰቡ ጋር ተወያይቶ መኖር ይችል ነበር። ልጆቻቸውን ፈሰስ አድርገው ነው የሄዱት” በማለት የነበረውን ሁኔታ ይገልጹታል።

የከተማዋ ሀዘን መንግሥትን ትደግፋላችሁ እና ፋኖን ትደግፋላችሁ በሚል የሞቱት ሰዎች የአካባቢው ተወላጆች በመሆናቸው መበርታቱን ሌላ ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ ነዋሪ ተናግረዋል።

“ሀዘን በሀዘን ነው የነበረው። ፖሊስም ብትይው ፋኖም ብትይው የአንድ አካባቢ ልጆች ናቸው። አባት ሚሊሻ ነው፤ ልጁ ፋኖ ሆኖ የሞተ አለ። እና ድብልቅልቅ ያለ ስሜት ነው። ከዛም የሞተው ከዚህም የሞተው አንድ አይነት ነው። ባለፈውም 15 ኪ.ሜ አካባቢ መንግሥት በድሮን የመታቸው አሉ፤ የሞቱትም የላሊበላ ልጆች ናቸው። በጣም አስቸጋሪ ነው። አሁንም [ላሊበላ] ሀዘን ላይ እንዳለች ነው የሚሰማኝ” ብለዋል።

“ግፉ ብዙ ነው። እግዚአብሔር ምህረቱን ካላከልን በምንም ሚዛን ጉዳቱ ይሄ ነው ብለሽ በዚህ ደረጃ ልትይው አትችይም። ግፉ ብዙ ነው። ክፋቱም ብዙ ነው” ሲሉ ሌላ ነዋሪ ተናግረዋል።

“. . .የከተማው ሰው ጥቁር ልብስ ለብሶ ነው የሚታይው። ‘ታሞ ሞተብህ ወይስ በዘመኑ በሽታ [ጦርነት] ሞተብህ?’ እስከመባል እየደረሰ ነው” በማለት የማኅበረሰቡን ሀዘን ይገልጻሉ።

የላሊበላ ከተማ ነዋሪዎች ሀዘን ለገና በዓል የሚደረገው ዝግጅት ላይ ጥላውን ማጥላቱን ቢቢሲ ያነጋገራቸው ነዋሪዎች ይናገራሉ።

“ዳቦ የሚሸጠው፣ ቆሎ የሚሸጠው፣ ሆቴል የሚያከራየው፣ ጋይድ የሚያደርገው [የሚያስጎበኘው] በተስፋ ዓመቱን የሚንቀሳቀስበት ነው፤ የሚዘጋጅበት ሰዓት ነበር። የዘንድሮው ግን በዚህ ከቀጠለ እንግዳ መምጣት አለመምጣቱ አስጊ ነው የሚሆነው” ሲሉ መንገዶች መዘጋታቸው ጠቅሰው ሁኔታው “አሳዛኝ” እንደሆነ ተናግረዋል።

“እንደ ራሴ በዓሉን አከብራለሁ ብዬ አላስብም። ውስጤ ጥሩ አይደለም። በከተማዋ በዓሉ ይከበራል የሚል የለኝም። ሆቴሎችም እንደተዘጋጉ ነው። ቱሪስትም ምንም የለም። ስለዚህ በዓሉ ይከበራል የሚል [እምነት] የለኝም። አንደኛ ከተማው የጦርነት አውድማ እስከሚመስል ድረስ አሁንም መከላከያ ከከተማው አናት ላይ ምሽግ መሽጎ ባለበት፤ ከከተማው መግቢያ ላይ ምሽግ መሽጎ ባለበት በዓል ማክበር እንደራሴ በጣም የቀዘቀዘ ስሜት ነው ያለኝ። ህዝቡም እንደዛ ይመስለኛል” ብለዋል።

ላሊበላ ምንም እንኳ “ሀይማኖታዊ ቅዱስ ስፍራ” ብትሆንም ለገና በዓል ግን በተለየ ሁኔታ ጎብኝዎችና አማኞች የሚጎርፉባት ከተማ ናት።

የከተማዋ ምጣኔ ሀብትም ቱሪዝም ነው።

“የኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓል ስለሆነ፤ በለቅሶም ሆነን ቢሆን የግድ እናከብረዋለን” የሚሉት አንድ ለቤተ ክርስትያን ቀረብ ያሉ ነዋሪ፤ በከተማዋ ገናን ለማክበር ከሞላ ጎደል ዝግጅት እየተደረገ እንደሆነ ተናግረዋል።

የላሊበላ ከተማ አስተዳደር በዓሉን “በድምቀት ለማክበር” እየተዘጋጀሁ ነው ያለ ሲሆን፤ ለታዳሚዎችም “በዓሉን አብረን እናክብር” ሲል ጥሪ አቅርቧል።  ዘገባው የቢቢሲ ነው፡፡

selegna

By selegna

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *