ከተለያዩ የወለጋ ዞኖቾች ተፈናቅለው በሰሜን ወሎ እንዲሁም በደቡብ ወሎ መጠለያ ጣቢያዎች ተጠልለው የሚገኙ ተፈናቃዮች ያለፈቃዳችን ጥቃት ሸሽተን ወደመጣንበት አካባቢ እንድንመለስ ተገደናል ሲሉ ለቢቢሲ ገለጹ።

የክልሉ አደጋ መከላከልና ዝግጁነት አመራሮች በበኩላቸው ተፈናቃዮች በግዳጅ እንዲመለሱ እንደማይደረግና የሚመለሱት ሰዎች ሰላማዊ ወደሆኑ የወለጋ አካባቢዎች እንደሆነ ለቢቢሲ ገልጸዋል።

የክልሉ አመራሮች ይህን ይበሉ እንጂ በገራዶ፣ ደጋን፣ ጃሪ፣ ኩታበር፣ ሐይቅና ሌሎችም መጠለያዎች ውስጥ ያሉ ተፈናቃዮች ለቢቢሲ እንደተናገሩት ተፈናቃዮች ለደኅንነታቸው ዋስትና ወደማያገኙበት አካባቢዎች እንዲመለሱ እየተገደዱ መሆኑን ነው።

ቢቢሲ ያነጋገራቸው በመጠለያ ጣቢያዎቹ ውስጥ የሚገኙት ተፈናቃዮች “ወደ ምዕራብ ኦሮሚያ አካባቢዎች ለመመለስ ፍላጎት ባይኖረንም በጥቂት ቀናት ውስጥ ወደ ቀያችን እንደምንመለስ ተነግሮናል” ይላሉ።

ቢቢሲ በዚህ ዘገባ ላይ ያነጋገራቸውን ሰዎች ማንነት ለመጠቅ ሲባል ስማቸውን፣ ተፈናቅለው የመጡበትን እንዲሁም አሁን ተጠልለው የሚገኙበትን ቦታ ከመጥቀስ ተቆጥቧል።

“የመጣችሁበት ቦታ አሁን ሰላም አለ፤ ትሄዳላችሁ ተባልን። ጉዟችን የፊታችን ሰኞ (ታኅሣስ 15 2016 ዓ.ም.) ከሰዓት እንደሆነ ተነግሮናል። መመለስ እንፈልጋለን ግን ሰላም የለም። ሰላም አለ የሚሉት የውሸት ነው። እኛ እኮ እዛ ከቀሩ ወገኖቻችን መረጃ ቀን በቀን እናገኛለን። እራሳቸውን እየጠበቁ እና እየተከላከሉ ነው የሚኖሩት” ብለዋል አንድ ተፈናቃይ።

ይህ ተፈናቃይ እንደሚሉት ተፈናቅለው የመጡበት የምዕራብ ኦሮሚያ አካባቢ ሰላም ከራቀው ሦስት ዓመታት ማለፉን ይናገራሉ።

“በዛ ያሉ ሰዎች ገበያ ከወጡ፣ ሕክምና ካገኙ ሦስት ዓመት አልፏቸዋል። ከወረዳው አስተዳደር ጋር ምንም አይነት ግንኙነት የላቸውም” በማለት የአካባቢውን ሁኔታ ይገልጻሉ።

ተፈናቃዮቹ እንደሚሉት ከነገ በስቲያ ሰኞ ወደ ቀደመ መኖሪያቸው የማይመለሱ ከሆነ አሁን ከሚኖሩበት መጠለያ ጣቢያ በግዳጅ እንዲወጡ እንደሚደረጉ መሆኑን ተናግረዋል።

“እዚህ ረሃብ ነው። እዛ ብንሄድ ደግሞ ሞት ነው” የሚጠብቀን የሚሉት ተፈናቃይ ደግሞ አሁን ተጠልለው ባሉት ጣቢያ የዕርዳታ ምግብ ለመጨረሻ ግዜ የተሰጣቸው ባለፈው ዓመት መጨረሻ ነሐሴ 2015 ዓ.ም. መሆኑን ይናገራሉ።

“እዛ ያሉ (ምዕራብ ኦሮሚያ) ሰዎች ጋር ስንደውል በስጋት ነው የሚኖሩት። ወፍጮ እንኳ የለም፤ በድንጋይ እየፈጩ ነው ሕይወታቸውን እያቆዩ ያሉት። አሻቦ እና በርበሬ ካገኙ ስንት ዓመት አለፋቸው” ይላሉ።

ወደቀያቸው መመለስ ቢፈልጉም ያ እንዲሆን የሚሹት ግን ሰላም ሲሰፍን ብቻ እንደሆነ ነዋሪዎቹ ይናገራሉ።

“ስንት ወላጆቻችን፤ ሕጻናቶቻችን እና ሴቶች አልቀውብን አሁንም እንዴት ሰላም ወደሌለበት ቦታ እንሄዳለን?” ብለን ስንጠይቅ ከታኅሳስ 15 እስከ 17 መጠለያውን ካለቀቃችሁ የሚመለከተው አካል መጥቶ ያስወጣችኋል” ብለውናል በማለት ሌላ ተፈናቃይ ደግሞ ከአካባቢው አስተዳደር ጋር ያደረጉትን ውይይት ይገልጻሉ።

የደቡብ ወሎ ዞን የአደጋ መከላከል እና ምግብ ዋስትና የቅድመ ማስጠንቀቂያና ምላሽ ቡድን መሪ አቶ መሐመድ ሰይድ ዝግጁነት ነዋሪዎች የሚመለሱት ሰላም ወደሰፈነባቸው ቦታዎች እንደሆነና ጫና ያደረገም አካል እንደሌለ ይናገራሉ።

ተፈናቃዮች በአሁኑ ወቅት ተጠልለው የሚገኙባቸው ቦታዎች እንደ ትምህርት ቤት ያሉ መሠረተ ልማቶች ስለሆኑ “መሠረተ ልማቶቹ የልማት ቦታዎች ስለነበሩ ለልማት የሚፈለጉ ከሆነ ተፈናቃዮች በዛ ቦታ ላይቀመጡ ይችላሉ” ብለዋል።

አቶ መሐመድ ተፈናቃዮችን ወደመጡበት መመለስ የማይፈልጉ ከሆነ ወደ ማኅብረሰቡ መቀላቀል ይችላሉ ብለዋል።

መጠለያዎቹ ለልማት የሚፈለጉ ከሆነ “ወደ ማኅብረሰቡ ሊቀላቀሉ ወይም ወደሌላ መጠለያ ሊተላለፉ ይችላሉ። ለመመለስ ፍቃደኛ ያልሆኑት ምክንያት ደግሞ ይጣራል” ብለዋል።

የአማራ ክልል አደጋ መከላከል እና ምግብ ዋስትና ፕሮግራም ማስተባበሪያ ኮሚሽን ኮሚሽነር ተስፋሁን ባያብል በበኩላቸው ነዋሪዎች የሚመለሱበት ቀን እንዳልተቆረጠ ገልጸው ሊመለሱ የሚችሉባቸው ሁኔታዎችን እንዲህ ገልጸዋል።

“በአስገዳጅ መመለስ የለም። ነገር ግን አሁን የሚኖሩበት መጠለያ ዘላቂነት የለውም። ሰላሙ አስተማማኝ በሆነበት እና መሠረተ ልማት ወዳለበት ቦታ ኮሚቴ ሄዶ ካረጋገጠ በኋላ ይመለሳሉ” ካሉ በኋላ ተፈናቃዮችን ለመመለስ የታቀደባቸውን ቦታዎች ዝርዝረዋል።

እንደ አቶ ተስፋሁን ከሆነ በኦሮሚያ ሰላም ስላላቸው ይመለሱባቸዋል ያሏቸው ዞኖች፤ ምስራቅ ወለጋ፣ ምዕራብ ወለጋ፣ ሆሮ ጉዱሩ ወለጋ እና ምዕራብ ሸዋ ናቸው።

አቶ ተስፋሁን በአሁኑ ወቅት ተፈናቃዮችን በግዴታ የመመለስ ሂደት እንደሌለ እና ገና ተፈናቃዮችን ለመመለስ ውይይት እየተካሄደ መሆኑን ለቢቢሲ ተናግረዋል።  ዘገባው የቢቢሲ ነው፡፡

selegna

By selegna

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *