በጂማ ከተማ አዌይቱ መንደራ ቀበሌ ነዋሪ የሆኑ ሁለት ታዳጊዎች ከጠፉ ከቀናት በኋላ በውሃ ጉድጓድ ውስጥ አስከሬናቸው መገኘቱን የከተማዋ ፖሊስ እና ቤተሰቦቻቸው ለቢቢሲ ተናገሩ።

የ11 እና የ12 ዓመት ዕድሜ ያላቸው ታዳጊዎቹ አማኑኤል ቅባቱ እና ምኞት ኪዳኔ ከቤት ጠፍተው ሲፈለጉ ቆይተው አስከሬናቸው በሶስተኛው ቀን መገኘቱን በጂማ ከተማ ፖሊስ መምርያ የኮሙኑኬሽን ኃላፊ ኢንስፔክተር ገዛኸኝ አውጋቸው ለቢቢሲ ተናግረዋል።

የሁለቱ ታዳጊ ሕጻናት አስከሬን ከቀናት ፍለጋ በኋላ በሰጦ ሳማራ ቀበሌ ድንጋይ ለማውጣት በተቆፈረ እና ውሃ በሞላው ስፍራ መገኘቱን ፖሊስ ገልጿል።

በተያያዘም የአማኑኤል ቅባቱ እናት የልጃቸውን ሞት ሰምተው በድንጋጤ ታሕሳስ 11 / 2016ዓ.ም ጂማ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ከገቡ በኋላ መሞታቸውን ቢቢሲ ከቤተሰብ አባላት ጠይቆ መረዳት ችሏል። እናትየው ከደም ግፊት ችግር እንደነበራቸው ቢቢሲ ከቤተሰብ አባላት ሰምቷል።

ሁለቱ ታዳጊ ሕጻናት ጓደኛሞች መሆናቸውን የሚናገሩት የቤተሰብ አባላት በጋራ ወጥተው ሳይመለሱ መቅረታቸውን ለቢበሲ አረጋግጧል።

ስለ ሕጻናቱ አሟሟት ቤተሰብ እና ፖሊስ ምን አለ?

ሁለቱ ታዳጊዎች አማኑኤል ቅባቱ እና ምኞት ኪዳኔ ጎረቤታሞች ሲሆኑ ሁል ጊዜ በጋራ ይጫወቱ እና አብረው መዋልን ያዘወትሩ እንደነበር ቤተሰብ ይናገራል።

አማኑኤል የ4ኛክፍል ምኞት ደግሞ 5ኛ ክፍል ተማሪ ናቸው።

ታዳጊዎቹ ከቤት ወጥተው መጥፋታቸው የታወቀው እሁድ ታሕሳስ 7፣ 2016 ዓ.ም ነበር።

በዚያች ቀንም እስከ እኩለ ቀን ድረስ አብረው ሲጫወቱ እንደነበር የአማኑኤል አባት አቶ ቅባቱ ሲባኒ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

“ሌላ ጊዜ ግፋ ቢል ማታ 1 ሰዓት ወደ ቤት ይመለሱ ነበር” የሚሉት አቶ ቅባቱ በዚያችን ዕለት ግን እስከ ምሽቱ 1፡40 ደቂቃ ድረስ ጠብቀው ስላልተመለሱ ፍለጋ መውጣታቸውን ይናገራሉ።

“ብዙ ጊዜ አብረው ቤተ ክርስትያን ይሄዱ ነበር። እዚያም ሄድን ፈልገን ልናገኛቸው አልቻልንም” ብለዋል።

በመቀጠልም “እኩለ ለሊት ላይ ራቅ ወዳለ ወደ ሌላ ቤተ ክርስትያ የተኛውን ሰው ሁሉ ቀስቅሰን ብንፈልግም ማግኘት አልቻልንም” ይላሉ።

በነገታውም ሰኞ ታሕሳስ 8/ 2016 ለጂማ ከተማ ፖሊስ ኮሚሽን ማመልከታቸውን ይናገራሉ።

በጂማ ከተማ ፖሊስ መምርያ ወረዳ 2 ተገኝተው ካመለከቱ በኋላ፣ ለሁለት ቀናት ፍንጭ ጠፍቶ በፍለጋ ሲባዝኑ መቆየታቸውን ጨምረው ተናግረዋል።

ማክሰኞ ዕለት ታሕሳስ 9/ 2016 ዓ.ም፣ ፖሊስ ከኅብረተሰቡ በደረሰው ጥቆማ መሰረት የሁለቱ ታዳጊዎች አስከሬን በጂማ ከተማ ሰጦ ሰማሮ ቀበሌ በሚገኝ ወንዝ ውሃ ውስጥ መገኘቱን አስረድተዋል።

አስከሬኑ ከውሃ ውስጥ ከወጣ በኋላ የታዳጊ ሕጻናቱ መሆኑ መረጋገጡን ኢንስፔክተር ገዛኸኝ አውጋቸው ለቢቢሲ ገልጸዋል።

የሁለቱ ታዳጊዎች አስከሬን የተገኘበት ስፍራ ለግንባታ የሚሆን ድንጋይ የሚወጣበት ሲሆን፣ ውሃ ሞልቶት እንደነበር ጨምረው ገልጸዋል።

ይኹን እንጂ ከመኖርያ ቤታቸው በግምት ቢያንስ አንድ ሰዓት እንደሚርቅ ኢንስፔክተሩ ጨምረው ተናግረዋል።

ከታዳጊዎቹ ሞት ጋር ተያይዞ “ኩላሊታቸው እና አይናቸው ወጥቷል” ተብሎ በስፋት በማህበራዊ ሚዲያዎች ሲወራ ቆይቷል።

ቢቢሲ የሆስፒታል መረጃ ማግኘት ባይችልም ኢንስፔክተር ገዛኸኝ ግን፣ መረጃው ሐሰት መሆኑን ተናግረው “አስከሬናቸው ላይ ምንም ዓይነት ቁስል” አለመገኘቱን ለቢቢሲ አረጋግጠዋል።

ይህ ሐሰተኛ ወሬ በሰፊው በመሰራጨቱ ቤተሰቡ አስከሬኑን በሚገባ አይቶ የቀብር ስርዓታቸው እንዲፈጸም መደረጉንም አክለው ተናግረዋል።

ፖሊስ ከታዳጊዎቹ ሞት ጋር በተያያዘ የአሟሟታቸው ምክንያት ላይ ምርመራ እያካሄደ መሆኑን አክለው ተናግረዋል።

በተጨማሪም የሆስፒታል ምርመራ ውጤት እንደደረሰ ለኅብረተሰቡ ይፋ አንደሚያደርጉም ገልጸዋል።   ዘገባው የቢቢሲ ነው፡፡

selegna

By selegna

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *