የቀድሞው የሶማሌ ክልል ፕሬዝዳንት አብዲ መሐመድ ዑመር (አብዲ ኢሌ) ያቀረቧቸው የመከላከያ ምስክሮች በፖሊስ እስር እና ድብደባ እየደረሰባቸው መሆኑን ለፍርድ ቤት ተናገሩ።

ዐቃቤ ሕግ በበኩሉ ክሳቸው ተቋርጦ የነበሩት አንዲት የአቶ አብዲ ምስክርን ክስ እንደገና እንደሚቀጥል ለችሎት ገልጿል።

አምስት የአቶ አብዲ ምስክሮች ከሶስት ቀናት በፊት ማክሰኞ ታኅሳስ 9፤ 2016 ዓ.ም. ከችሎት ሲወጡ በፖሊስ ቁጥጥር ስር መዋላቸውን አብዲ መሐመድ ለፍርድ ቤት ተናግረዋል።

በፖሊስ ቁጥጥር ስር ዋሉ ከተባሉት አምስት ምስክሮች መካከል አራቱ ባለፈው ማክሰኞ የምስክርነት ቃላቸውን ለመስጠት በችሎት ፊት ቃለ መሃላ የፈጸሙ መሆናቸውን ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው እና የፍርድ ሂደቱን የሚከታተሉ አንድ ግለሰብ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

አቶ አብዲ መሐመድ ባለፈው ዓመት ነሐሴ ወር ላይ ነበር የቀረበባቸውን ክስ እንዲከላከሉ በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 1ኛ የጸረ ሽብር እና ሕገ መንግሥታዊ ችሎት ብይን የተሰጠው።

የሶማሌ ክልልን ለስምንት ዓመታት የመሩት አቶ አብዲ፤ ዐቃቤ ሕግ ያቀረበባቸው እና እንዲከላከሉ በችሎት የተበየነው ክስ “የጦር መሳሪያ ይዞ ማመጽ፥ ወይም የእርስ በርስ ጦርነት በማነሳሳት በመንግሥት ላይ የሚደረግ ወንጀልን” ፈጽመዋል የሚል ነው።

ይህን ተከትሎ አቶ አብዲ መሐመድ 128 የመከላከያ ምስክሮችን ለፍርድ ቤት አስመዝግበዋል። ባለፈው ወር ሕዳር 3፤ 2016 ዓ.ም. ምስክሮች መሰማት የተጀመሩ ሲሆን እስከ ማክሰኞ ድረስ 23 ምስክሮች ተሰምተዋል።

ማክሰኞ ዕለት 23ኛዋ የመከላከያ ምስክር ከተሰሙ በኋላ በዕለቱ ቃለ መሃላ የፈጸሙ ቀሪ ምስክሮችን ለመስማት ጉዳይ በይደር ለረቡዕ ታኅሳስ 10 መቀጠሩን የችሎት ውሎውን የሚከታተሉት ግለሰብ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

የፍርድ ሂደቱን የሚከታተሉት ግለሰብ፤ “ምስክሮቹ ቃለ መሃላ ፈጽመው ችሎት ፊት ቀርበው ስማቸውን እና ተራቸው ተመዝግቦ [ምስክር አሰማሙን] በይደር ለመቀጠል ከታዘዘ በኋላ ነው ይሄ የገጠመው” ሲሉ ምስክሮቹ የታሰሩበትን አኳዃን ለቢቢሲ አስረድተዋል።

“ምስክሮች ችሎት ፊት ቀርበው ቃለ መሃላ ፈጽመው ከወጡ በኋላ የታሰሩ ያሉ በመሆናቸው ድብደባም እየተፈጸመባቸው ነው” የሚል አቤቱታ ለፍርድ ቤቱ ቀርቧል።

በፖሊስ ታሰሩ ከተባሉት ምስክሮች መካከል አንደኛዋ ከዚህ በፊት ከአቶ አብዲ መሐመድ ጋር በአንድ መዝገብ ክስ ቀርቦባቸው የነበረ ቢሆንም ከሶስት ዓመት ከስምንት ወር በፊት ክሳቸው ተቋርጦ ነበር። ከክሳቸው መቋረጥ በኋላ የአቶ አብዲ መሐመድ ምስክር ሆነው የተመዘገቡት ግለሰቧ ካለፈው ማክሰኞ ጀምሮ በእስር ላይ እንደሚገኙ ግለሰቡ አክለዋል።

ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ግለሰብ እንደሚሉት የምስክሯን እስር ሲያስረዱ፤ “በ2012 ዓ.ም. የካቲት ላይ ክሳቸው ተቋርጦ ነበር። በዚህ መዝገብ መከላከያ ምስክር ሆነው መጥተው ከመሰከሩ በኋላ ነው የታሰሩት። ዐቃቤ ሕግም ክሳቸውን እንቀጥላላን የሚል አቤቱታ ያቀረበው በ11 [ታኅሳስ] ነው” ብለዋል።

ፍርድ ቤቱ ካለፈው ማክሰኞ በኋላ የምስክሮችን ቃል ለመስማት ቀጠሮ ይዞ የነበረ ቢሆንም፤ “ከዚህ ጋር በተያያዘ ምክንያት እስካሁን ችሎት ፊት አልቀረቡም” ሲሉ ግለሰቡ ተናግረዋል።

አቶ አብዲ መሐመድ የምስክሮቻቸውን መታሰር ለፍርድ ቤት በአቤቱታ መልክ ካቀረቡ በኋላ፤ “የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን እና የፌደራል ፖሊስ ምላሽ እንዲሰጡ እና የታሰሩም ካሉ ይዟቸው እንዲቀርቡ” በችሎቱ ትዕዛዝ ተሰጥቶ ነበር። ፍርድ ቤቱ ተቋማቱ ምላሽ እንዲሰጡ ያዘዘው ለትላንት ቢሆንም ትላንት ምላሹ ባለመቅረቡ ለዛሬ ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል።

የአዲስ አበባ ፖሊስ ዛሬ ለፍርድ ቤቱ በሰጠው ምላሽ፤ “እኛ [አዲስ አበባ ፖሊስ] ጋር የታሰረ ማንም እስረኛ የለም፤ 23ኛ ምስክርም በፌደራል ፖሊስ በኩል የታሰሩ የውሰት እስረኛ ናቸው” ብሏል።

ዛሬ አርብ ረፋድ ላይ በነበረው የችሎት ውሎም 23ኛ ምስክር በፌደራል ፖሊስ ታጅበው ችሎት መቅረባቸውን ጉዳዩን በችሎት የተከታተሉት ግለሰብ ለቢቢሲ ተናግረዋል። ግለሰቡ አክለውም “23ኛ ምስክር ታሰረው መቆየታቸውን እና በፖሊስ ታጅበው መቅረባውን በችሎት ተረጋግጧል” ብለዋል።

በፖሊስ ታጅበው ችሎት የቀረቡት ምስክር ባለፈው ሳምንት ማክሰኞ የገጠማቸውን ሁኔታ ለችሎት ማስረዳታቸውን ግለሰቡ አክለዋል።

ከምስክሯ ቃል በተጨማሪ ዐቃቤ ሕግ ክሱን እቀጥላለሁ ማለቱ ግራ ቀኙን አከራክሯል።

የአቶ አብዲ መሐመድ ጠበቆች “ክሱን እንቀጥላለን የሚለው ውሳኔ ሕገ መንግሥቱን የሚጥስ ነው ስለዚህ ውድቅ ሊደረግ ይገባል። የመከላከል መብታችን ሊጣበብ አይገባም” ሲሉ ተሟግተዋል።

ጠበቆቹ አክለውም ተከሳሹ አቶ አብዲ መሐመድ በሕገ መንግሥቱ መሠረት ራሳቸውን የመከላከል መብት እንዳላቸው አንስተዋል።

የኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት የተከሰሱ ሰዎችን መብት በሚዘረዝርበት አንቀጽ የተከሰሱ ሰዎች፤ “ለመከላከል የሚያስችላቸውን ማስረጃ የማቅረብ ወይም የማስቀረብ እንዲሁም ምስክሮቻቸው ቀርበው እንዲሰሙላቸው የመጠየቅ መብት አላቸው” ሲል ይደነግጋል።

የተከሳሹ አቶ አብዲ ኢሌ ጠበቆችም ይህንኑ የሕገ መንግሥት ድንጋጌ በማንሳት ተከራክረዋል። የተከሳሽን የመከላከል መብት መሠረት በማድረግ በቀረበው ክርክር ግራ ቀኝ መርምሮ ትዕዛዝ ለመስጠት ፍርድ ቤት ለመጪው ሳምንት ማክሰኞ ታኅሳስ 16፤ 2016 ዓ.ም. ቀጠሮ ሰጥቷል።

አቶ አብዲ ኢሌ በሶማሌ ክልል ጅግጅጋ ከተማ ተከስቶ በነበረው ግጭት ምክንያት በቁጥጥር ስር የዋሉት ከአምስት ዓመታት ገደማ በፊት በነሐሴ 2010 ዓ.ም. ነበር። አቶ አብዲ መሐመድ በቁጥጥር ስር ከመዋላቸው በፊት በክልሉ ምክር ቤት ያለመከሰስ መብታቸው የተነሳው በዚያው ወርሃ ነሐሴ ነው።   ዘገባው የቢቢሲ ነው፡፡

selegna

By selegna

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *