የአፍሪካ ልማት ባንክ ዓለም አቀፍ ሠራተኞቹን ከኢትዮጵያ ሊያስወጣ መሆኑን ምንጮች ለሮይተርስ የዜና ወኪል ተናገሩ።

የአፍሪካ ልማት ባንክ ዓለም አቀፍ ሠራተኞቹን ከኢትዮጵያ ሊያስወጣ መሆኑ የተነገረው ከዚህ ቀደም ባንኩ “የዲፕሎማሲያዊ መብት ጥሰት” ብሎ በገለጸው ክስተት ሁለት ሠራተኞቹ በአገሪቱ የፀጥታ ኃይሎች ታስረው አካላዊ ጥቃት ከደረሰባቸው በኋላ ነው።

አህጉራዊው የገንዘብ ተቋም ጥቅምት 2016 ዓ.ም. አጋማሽ ላይ ሁለት ሠራተኞቹ በአዲስ አበባ “ከሕግ ውጪ” ታስረው አካላዊ ጥቃት እንደተፈጸመባቸው አስታውቆ ነበር።

የአፍሪካ ልማት ባንክ ጥቅምት 20/2016 ዓ.ም. ሠራተኞቹ በቁጥጥር ስር እንደዋሉ ጉዳዩን ለጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ካሳወቀ በኋላ በፍጥነት እንደተፈቱም ገልጾ ነበር።

“መቀመጫቸውን በአዲስ አበባ ያደረጉት ሁለት የአፍሪካ ልማት ባንክ ግሩፕ ባልደረቦች ያለ ይፋዊ ማብራሪያ በፀጥታ ኃይሎች፣ በሕገ-ወጥ መንገድ ተይዘው አካላዊ ጥቃት ደርሶባቸው ለሰዓታት ታስረዋል” ይላል ባንኩ ኅዳር ወር ላይ ያወጣው መግለጫ።

ባንኩ ክስተቱን ለአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ካሳወቀ በኋላ ሠራተኞቹ በፍጥነት መለቀቃቸውን እና ክስተቱም በዝርዝር እንደሚመረመር ጠቅላይ ሚኒስትሩ ቃል መግባታቸውን ባንኩ በመግለጫው ገልጾ ነበር።

ይኹን እንጂ ይህን እስር እና አካላዊ ጥቃት መነሻ በማድረግ ባንኩ ዓለም አቀፍ ሠራተኞቹን ከአገሪቱ እንደሚያስወጣ ሮይተርስ ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸውን ምንጮች ጠቅሶ ዘግቧል።

ሁለት የሮይተርስ ምንጮች ዓለም አቀፍ ሠራተኞቹ ከአገር የሚወጡበትን የጊዜ ሰሌዳም ሆነ ሠራተኞቹ ከአገሪቱ መውጣታቸው ባንኩ በኢትዮጵያ ባለው ሥራ ላይ ስለሚኖረው ተጽእኖ የሚያውቁት ነገር እንደሌለ ተናግረዋል።

ባንኩ ሕዳር ወር ላይ ባወጣው መግለጫው ታስረው እንግልት ደረሰባቸው ያላቸውን የባንኩን ሠራተኞች ማንነት፣ የሥራ ድርሻ እና ክስተቱ ያጋጠመበትን ሁኔታ በተመለከተ ያለው ነገር የለም።

የአፍሪካ ልማት ባንክ ከኢትዮጵያ ቁልፍ የፋይናንስ አጋሮች መካከል አንዱ ሲሆን፣ የባንኩ ፕሬዝዳንት አኪንውሚ አዴሲና በቅርቡ ወደ አዲስ አበባ በመጡ ወቅት በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ደማቅ አቀባበል ተደርጎላቸው ነበር።

ባለፈው መስከረም 2016 ዓ.ም. ባንኩ በኢትዮጵያ የኃይል አቅርቦት ላይ ማሻሻያ ለማድረግ የ100 ሚሊዮን ዶላር በጀት ማጽደቁ ይታወሳል።  ዘገባው የቢቢሲ ነው፡፡

selegna

By selegna

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *